ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ማግኘት የነበረባትን የባህር በር ሳታገኝ እንዲሁም በተመሳሳይ ኤርትራ ስትሄድ ለመውጪያም ሆነ ለመግቢያ ይጠቅማት የነበረን የባህር በር ሳታገኝ መቅረቷ ልብ ያደማል።
የፖለቲካ ሳይንስን በቅጡ የሚገነዘቡ ምሁራን የራስ ዱሜራን ጉዳይ ወደ አደባባይ ይዘውት ቢመጡ እንዴት ጥሩ ነበር ምክንያቱም መልካም ሀሳቦች ሲጠራቀሙ ሀገር ያጸናልና!
በጅቡቲ ላይ ወሳኝ ጥያቄ ማንሳት የሚያስችሉ ታሪካዊ አጋጣሚዎች የነበሩት ደርግ እና በኤርትራ መገንጠል ዋነኛ አጋፋሪ የነበረው ኢሕአዴግ ቢያንስ የራስ ዱሜራን ጉዳይ ሊያዳፍኑት አይገባም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የባህር በር ጉዳይን ወደ አደባባይ ይዘው ሲመጡ፣ በኋላም ከሶማሌ ላንድ ጋር ውል ሲታሰር ሁሉ ብዙ ሰዎች ጉዳዩን ከአሰብ ጋር አያይዘው ሲናገሩ ይስተዋል ነበር። የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ብዙ ውዝግቦች አስነስቶ አጀንዳ መሆኑ በራሱ በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው፤ ነገር ግን ቶሎ ነገር የሚገባው የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ የአሰብ ወደብን እንዳልተጠየቀ ባያጣውም፣ ጉዳዩ የራስ ዱሜራ አጀንዳ እንዳለበት ወዲያውኑ ስለመረዳቱ ምልክቶች አሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጨዋታ ህጉን በጊዜ አሰናስኖ ከተጫወተ ኢትዮጵያ ያለምንም መስዋዕትነት በግማሽ ቀን ከነ ሙሉ ክብሩና ጥቅማጥቅሙ ጋር የባህር በር ባለቤት ትሆናለች – ራስ ዱሜራ የሷ ይሆናልና!
ምናልባት ጨዋታው ከሮ እየተካሄደ ያለበትን ሜዳ ላልገባው ሀገር ወዳድ ወገን ለማብራራት ያህል፦ የራስ ዱሜራ ሃሩር ቀጣና በኤርትራ፣ በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ የሚዋሰን ነው። በዚህ ግዛት ጉዳይ ቅኝ ገዥዎች የነበሩት ፈረንሳይ እና ጣሊያን በ1892 አካባቢ የላይኛውን ራስ ዱሜራ ጣሊያን የታቹን ደግሞ ፈረንሳይ ሊወስዱት ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን በተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና አላገኘም፣ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ራስ ዱሜራ የማርያም መንገድ ነው!
ራስ ዱሜራ ቀይባህርን በ1.5 ኪሎ ሜትር የሚነካ፣ በጂቡቲና በኤርትራ መካከል በግምት 20 ኪሎ ሜትር የሚወጠር በየትኛውም ሉዐላዊ ሀገር ያልተመዘገበ፣ የማንም ያልሆነ ፈሪ መሬት ነው ።
ጅቡቲና ኤርትራ በምድሩ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ቢኖራቸውም በአለማቀፍ ደረጃ ለሁለቱም አልተወሰነም። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የጨዋታ ህግጋቱን በአግባቡ እስከተጫወተች ድረስ ራስ ዱሜራን በድጋሚ የራሷ ማድረግ ትችላለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የባህር በር ጥያቄ ሲያነሳ እሳትና ጭድ የሆኑት ኤርትራና ጅቡቲ አብረው ታች ላይ ማለታቸውን ልብ ይሏል። እነዚህ ሀገሮች በራስ ዱሜራ ቀጣና እንዳልተወዛገቡ ሁሉ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ራስ ዱሜራን የራሷ ካደረገች ሁለቱም ሀገራት ወደቦቻቸው አልጫ ተብሎ እንደሚጣለው ጨው ጥቅም አልባ ይሆናሉ የሚል ወልካፋ ግምት ይዘው አንድነት ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑ እየታየ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የሄደበትን መንገድ በቀጣይ በቅልጥፍና ካካሄደ ታላላቅ ሀገራት ከጎኑ ለመቆም እንደፈቀዱ እየተሰማ ነው። ግብፅና ሳዑዲ አረቢያ ጭምር በየመን ሁቲዎች ምክንያት ለዳሸቀው ኢኮኖሚያቸው ሲሉ አዎንታዊ አመለካከት እንዳላቸው ከጨዋታው አንደምታ መረዳት ይቻላል።
ከጊዜ ምህዋር አንፃር ጥሩ ግንዛቤ ያላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጅቡቲ ጋር ያላቸውን የራስ ዱሜራ ባለቤትነት ጥያቄ በሰላም ለመፍታት እና በድጋሚ የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዳይ ለማዳፈን አፍታ እየጠበቁ መሆናቸው እየተስተዋለ ነው። ሰውየው ኢሳያስ ከዚህ ባሻገር በጥልቀት በመሄድ የሰሜን ኢትዮጵያ ቅራኔዎችን በማጋም ሌላ ዙር ጦርነት ለማስጀመርም እየዋተቱ ስለመሆኑ ምልክቶች አሉ።
ይሁን እንጂ የጨዋታው ካርዶች በሙሉ በኢትዮጵያ እጅ የሚገኙ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት የተለየ የባለሙያዎች ቡድን አቋቁሞ እየተማከረ ጨዋታውን ቢያካሂድ ድል ያገኛል።
የመጨረሻው መጀመሪያ ራስ ዱሜራ – የኢትዮጵያ የማሪያም መንገድ …
wz news