መንግሥት ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር እንዲገቡ በመፍቀዱና ተግባራዊ ምላሽ በመስጠቱ ከፍ ያለ ምስጋናችንን ማቀረቡን ቋሚ ሲኖዶስ ባሰራጨው መግለጫ አስታወቀ፤ ጳጳሳቱ ወእ አገር ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የሦስቱ የብፁዓን አባቶችን ወደ ሀገር መግባት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። ቋሚ ሲኖዶስ በመግለጫው ” በውጭ አህጉረ ስብከት ተመድበው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በመፈጸም ላይ የሚገኙት
- ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፤
- ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) የሰሜን ካሊፎርኒያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤
- ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጅያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን እንዲሳተፉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ጥያቄ አቅርባ እንደነበር አመልክቷል።
” መንግሥትም ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው” በሚለው የቤተክርስቲያኒቱ መግለጫ “የሀገራችንን ሰላም ለማጽናት፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የታሪክ ገጽታ ለመጠበቅ ተቀራርቦ መነጋገር የተሻለ መፍትሔ መሆኑን ተረድቶ ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር ገብተው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን እንዲሳተፉ መፍቀዱን ተረድተናል ” በሚል የአብሮነትንና ተባብሮ የመስራትን ሚስጢር ተመልክቷል።

” በመሆኑም መንግሥት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያቀረበችውን ጥያቄ ተቀብሎ ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር እንዲገቡ በመፍቀዱና ተግባራዊ ምላሽ በመስጠቱ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን ” ብሏል።
ቋሚ ሲኖዶስ፥ ” ወደፊትም እግዚአብሔር በሰጠን ምድር፤ አባቶቻችን ባቆዩልን ሀገር አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ለሀገራችንና ለሕዝባችን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ግንኙነታችንን በማጠናከር በጋራ ለመሥራት ዝግጁዎች መሆናችንን እንገልጻለን ” ሲል አሳውቋል።
ቀደም ሲል የጳጳሳቱን መታገድ በስፋት ሲያስተጋቡ የነበሩ ሚዲያዎች ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ የመንግስትን ውሳኔ አድንቆ ምስጋና ማቅረቡን ከመዘገብ ተቆጥበዋል። ዜናውን በቀደሞ ዜናቸው መጠን ያልዘገቡበት ምክንያት ግልጽ ባይነገርም አብዛኞች ዜናው ለፖለቲካ ገበያ የሚውል ባለመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል። “ነገ መንግስትና የህክምና ባለሙያዎች ስምምነት ቢፈጥሩ በተመሳሳይ ዜናውን አይዘግቡትም” ያሉም አሉ።