በትግደፍ አመራር ሰጪነት በትህነግ ተባባሪ ሆኖ የተዘጋጀው የቢሆን ዕቅድ ታወቀ። “ብናሸነፍም ብንሸነፍም ወደ ጦርነት እንግባ” የሚል አቋም መያዛቸው ታውቋል። ከመንግስት ወገን እንደሚሰማው ከሆነ ሻዕቢያ አንድ ጥይት ከተኮሰ ወይም ከለላ ከሰጠ ጦርነቱ የቴክኖሎጂና አጭር እንደሚሆን ነው። ከትግራይ ታጣቂ ኃይል ከመሪዎቻቸው ጋር እየሸሹ ሐራ መሬት እየሰፈሩ ያሉት ታጣቂዎች ለሻዕቢያ ስጋት በመሆናቸው የኤርትራው የደህንነት ኃላፊ መመሪያ ሰጥተዋል።
ትግደፍ/ ሻዕቢያና በእነ ዶክተር ደብረጽዩን የሚመራው ትህነግ/ ወያኔ ሚስጥር አስመስለው የጀመሩት ግንኙነት ይፋ ሆኗል። ከትግራይ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሻዕቢያ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የደህንነት ኦፊሰሮች፣ ጄነራሎች፣ የፖለቲካ ኃላፊዎች ትግራይን መቀለ ድረስ እየተመላለሱባት ነው። ገዛ ተጋሩ ድግስ ተደግሶ እነ አብርሃ ካሳ፣ የማነ ማንጁስ በተገኙበት ከትህነግ አመራሮች ጋር ጭፈራ ተደርጓል።
በኩዴታ ከመቀለ የተባረረው የአቶ ጌታቸው ካቢኔ አባል አቶ ጣዕመ አረዶምና አቶ እግብሩ አስራት እንዲሁም በዱባይ የሚገኘው የቀድሞ የሻዕቢያ ሰላይ እንዳሉት ሻዕቢያና ትህነግ ውጤቱ ምንም ይሁን አይሁን ጦርነት መርጠዋል። እንደ አቶ ጣዕመ ከሆነ ሶስት የቢሆን ዕቅድ ነድፈዋል። ደረጃ በደረጃ የሚያስኬዱትም ይህንኑ ነው።
ከአቶ ጣዕመ መረጃ ጋር የሚስማማው የሻዕቢያ የቀድሞ ሰላይ ትህነግ በከፍተኛ መኮንኖቹ አማካይነት ከግብጽ ጋር አስመራ ላይ መምከራቸውን አመልክቷል። ግብጽ ጸረ ድሮን ሳይቀር ከባድ መሳሪያ እንድታቀርብላቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ወያኔና ሻዕቢያ የመከዳዳት ባህል ስላላቸው አስፈጻሚው ግን ሻዕቢያ መሆኑን አመልክቷል።
አቶ ገብሩ አስራት ትህነግ ከምርጫ ቦርድ መሰረዙን ተከትሎ ከሪፖርተር ቲዩብ ጋር ውይይት ያደረጉት አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው ትህነግ ከሻዕቢያና ፋኖ ጋር ግንኙነት መጀመሩን አመልክተው፣ “ከሌላም ጋር ይገናኛል። ስሙን አሁን አልጠራም” ብለዋል። እሳቸው ስም ባይጠሩም ግብጽ ለመሆኗ በርካታ መረጃዎች አሉ።
1ኛ የቢሆን የጋራ ዕቅድ
ዓላማው የፊደራል መንግስትን መወጠርና አቋሙን ማስቀየር ሲሆን፣ በዚህም የአሰብን ጥያቄ እንዲያነሳ፣ ለትህነግም ትግራይን ሙሉ በሙሉ ያለአንዳች ገደብ እንዲሰጥ፣ በፌደራል ደረጃም በሚፈልጉት መጠን የመሪነት ስልታን እንዲሰጣቸው በማስገደድ የሻዕቢያን ጥቅም የሚጎዱ ማናቸውም ጉዳዮች እንዳይነሱ፣ እንዳይወሰኑ፣ መከላከል የሚችሉበትን አቅም ማረጋገጥ። ጫናውን ለማበርታት ፋኖ፣ ሸኔ፣ ኦብነግ ወዘተ የመሳሰሉትን ኃይሎችን ለማስተባበር የተጀመረውን ጥረት አጠንክሮ ወደ ህብረት ማሳደግ። እዚህ ላይ ሱዳንና ሱዳን ውስጥ ለአልቡራን የሚዋጉት የትህነግ ኃይሎችም የሚታሰቡ ናቸው።
በዚህ ዕቅድ ውስጥ የሁለቱ፣ ማለትም ሻዕቢያና ወያኔ ህብረት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ በማስመሰል ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት፣ በፕሮፓጋንዳው አማካይነት የሕዝቡን እይታ መቀየር። ለዚህም ኢትዮጵያዊ ስም ያላቸውን የመገናኛ ዘዴዎች መጠቀም የሚሉበት ይገኙበታል። ይህ ሁሉ ተደርጎ የፌደራል መንግስቱ አቋሙን በመቀየር ስለ ወደብና ትህነግ የሚያራምደውን አቋም ካለቀየረ
2ኛ የቢሆን የጋራ ዕቅድ
ከላይ የተጠቀሱትን ኃይሎች አስተባበሮ ውጊያ በመክፈት ኢትዮጵያን መበተን የሚለው አቋም ተይዞበታል። “ኢትዮጵያን መበተን” የሚለው ሁለተኛው የቢሆን ዕቅድ እንዲሳካ በአንድ ጊዜ ከሁሉም አቅጣጫ ጦርነት በመክፈት ማዕከላዊ መንግስቱን ገልብጦ ኢትዮጵያን መሸንሸን ነው። በዚህ ዕቅድ መሰረት ትግራይን እስከ አገው ምድር በማስፋት፣ ወልቃይት ጸገዴን በማካተት፣ ራያና አፋርን በመጨመር ከኤርትራ ጋር ማዋሃድ ነው።
ይህን ዕቅድ ተጋራዊ ለማድረግ ሻዕቢያና ወያኔ ስር የገባው ፋኖ ምን ይዞ እንደሚወጣ የተቀመተ ነገር የለም። ወልቃይት፣ ጸገዴን፣ አገውን፣ ራያን ለትግራይ አሳልፎ ለመስጠት የቅንጅቱ አባል የሆነው ፋኖ አቋምና ፍላጎት ምን እንደሆነ መረጃውን ያሰራጩት ለጊዜው ያሉት ነገር የለም። በዕቅዱ ኦሮሚያን በዘመቻ ለተወሰነ ጊዜ ወሮ የተመረጡ የኢኑስትሪ መንደሮችንና የልማት አውታሮችን ከመዝረፍ በዘለለ ሌላ ዕቅድ አልተያዘም። ወይም ለጊዜው አልተሰማም። የሻዕቢያው ሰላይ እንዳለው ዝርፊያውን የሚያከናውን ቡድን የተቋቋመው ከዓመትና ሁለት ዓመት በፊት ነው።
3ኛ የጋራ የቢሆን ዕቅድ
ሁሉም ካልሆነና የፌደራል መንግስት እጁን የሚጠመዘዝ ካልሆነ ወይም የሚሸነፍ ካልሆነ ትግራይን ዲፋክቶ መንግስት ማድረግ የዕቅዱ አካል ነው። በዚህ ዕቅድ መሰረት ትግራይ አሰብ ወደብን እንድትጠቀም ይደረጋል። ሻዕቢያ ትግራይን አዝሎ እስከ እውቅና ድረስ ያዘግማል።
የትህነግ የግል ግምገማ
ከዚህ ውጪ የእነ ዶክተር ደብርጽዮን ቡድን በግል ከሻዕቢያ ተደብቆ ያደርገው ግምገማ ሙሉ በሙሉ እነ አቶ ጣዕመ አረዶም እጅ ገብቷል። የአቶ ጌታቸው ካቢኔ የነበሩት አቶ ጣዕመ እንዳሉት በፕሪቶሪያው ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ሻዕቢያ በርካታ ወታደሮቹን ከስሯል። ትህነግ ሲገመግም ሻእቢያ ምን ያህል ወታደሮች እንዳሉ ጠቅሶ አስተማማን ኃይል እንደሌልው አስምሮበታል። አቶ ጣዕመ “ለጊዜው ይለፈኝ” በማለት ያለውን የወታደር አቅም ጭምር መረጃው እንደደረሳቸው አመልክተዋል።
“በኤርትራ እናቶች የልጆቻቸው ሃዘን እስካሁን በይፋ አልተረዱም፤ ዳግም የጦርነት ስጋት አላቸው” በሚል ርዕስ ጁን 11 ቀን 2024 ኢትዮሪቪው ባወጣቸው ዘገባ ሻዕቢያ በርካታ ወታደርቹን መገለጹ ይታወሳል። በዚሁ ዘገባ ነዋሪነቷ አሜሪካ የሆነ ኤርትራዊ አዲስ አበባ አስቀምጣ የምትረዳቸውን እህቶቿን ለመጠየቅ ወደ ኢትዮጵያ ባቀናችበት ወቅት “ለስራ ተመዝገብ ተብሎ ወደ ሳዋ ከተተራ በሁዋላ ጦር ሜዳ የተላከው ወንድሜ ህይወቱ አልፏል። እናቴ መርዶ ሰምታ እርም ሳላላወጣች ዘወትር በር በሯን እያየች ታነባለች። በኤርትራ መርዶ መስማት እንኳ አይፈቀድም” በማለት ሃዝኗን ገልጻ ነበር።
በወቅቱ ” የፈተና ውጤት ይነገራችኋል፣ ስራ ትመደበላችሁ፣ ወደ ሳዋ እንድትገቡ” የሚል ጥሪ ተላልፎላቸው ሳዋ የገቡ ወደ ትግራይ ለጦርነት መላካቸውን፣ በትግራይ በኩል አምልጦ አዲስ አበባ እንደገባ የሚናገረው ምስክር ነበር ያስታወቀው። በርካታ ሴቶች ወታደሮች ያለ በቂ ስልጠና ለጦርነት መጋዛቸውንም ይኸው ወጣት አመልክቶ ነበር።
“ለጋ ወጣቶች ናቸው። አብዛኞቹ ሴቶች ጉዳት የደርሰባቸው ናቸው። መናገር ስለማይቻል እንጂ በኤርትራ ህዝብ ከፍቶታል። ልጆቻቸው ያልተመለሱላቸው ገብቷቸዋል። ቢሆንም ግን መርዶ ሰምተው እርም ማውጣት ይፈልጋሉ። በተለይ በትግራይ ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ በይፋ መርዶ ሲነገር በኤርትራ ዝም መባሉ ሃዘኑን የከፋ አድርጎታል” ያሉ ምስክሮች፣ በኢርትራ የቻሉ ተሰደዋል። ያለቁ አልቀዋል። ሻዕቢያ ተጠባባቂ ጦር ሳዋ ካስለጠነ ጊዜ እንደተቆጠረ አመልክተዋል። ይህም ይትህነግን ግምገማ እወነት ያደርገዋል። ስለሆነም ሻዕቢያ ፋኖና ትግራይ ስር የሚሮጠው አቶ ጌታቸው በቅርቡ እንዳሉት የሰው ኃይል ስለሌለው ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የአርሚ፣ ክፍለጦር፣ ኮርና ዕዝ አዛዥ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ “ሐራ መሬት/ ነጻ መሬት” ላይ የሰፈሩት የትግራይ ሰራዊት አካላት የእነ ደብረስዮንን ትህነግ አስግቶታል። በግምግማቸው ” አሁን ላይ እንደፈለገን ተዋጋ፣ በዚህ ሂድና ይህን ፈጽም የምንለው ኃይል የለንም” በማለት ስጋታቸው አኑረዋል። በግል ይህን እየገመገሙ ከሻዕቢያ ጋር የቢሆን ዕቅድ የሚነድፉት የትህነግ ሰዎች የተሳሳተ ሂሳብ እያሰሉ መሆኑን አቶ ጣዕመ ያስረዳሉ።
በሰው ኃይል ችግር የተወጠረው ሻዕቢያ “አንዋጋም የሚሉትን፣ የሸሹትን እየያዛችሁ ወደ እኔ ላኩ” በማለት በሰጠው መመሪያ መሰረት በርካታ የትግራይ ወጣቶች ወደ ኤርትራ መጋዛቸውን የሚተቁሙ እየተበራከቱ ነው። ዝርዝር ባይገልጹም አቶ ጣዕመም ይህን ተናግረዋል።
ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ገብሩ አስራት ” ደም የሚጠጣው” ያሉት ትህነግ ወደ ጦርነት እንደሚገባ ግምታቸውን አኑረዋል። ምክንያቱም ትህነግ ሌላ ባህል የለውም። እመነቱም፣ ባህሉም፣ ኑሮውም ጦነት ሰለሆነ የተለየ አማራጭ ሊያ እንደማይችል አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው ሰሞኑን ከፋና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኤርትራ ውስጥ ወጣቶች ተሰደው፣ ግማሾችም በየባህሩና በረሃው አልቀው የቀረው ህዝብ ከሁለት ሚሊዮን በታች መሆኑን መጠቆማቸው አይዘነጋም።
የእነ ደብረጽዮን ትህነግ የፌደራል መንግስትን አስመልክቶ በዝግ ባደረገው ግምገማ፣ ከየአቅጣጫው የተወጠረ ቢመስልም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል መገንባቱን፣ ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቁንና ቴክኖሎጂ የሚጠቀም መሆኑን አንስተው በስሌታቸው መሰረት መሄድ እንደማይችሉ መክረዋል። ለዚህም ይመስላል የዲፕሎማሲውን አግባብ ማጣቀስ የጀመሩት።
ከሁሉም በላይ ግን ሻዕቢያን ይዘው ወደ ጦርነት ከገቡ የአውሮፓ አገራት፣ ህብረትና አሜሪካ እንደማይደግፏቸው መረዳታቸው፣ በተቃራኒው ከመንግስት ጋር እንደሚቆሙ ምክቶች እየታዩ ስለሆነ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸው ይደመጣል።
ዘኢኮኖሚስት ትህነግ ጦርነት ከጀመረ አሜሪካ የጉዞ ማዕቀብን፣ ሃብትን ማገድ የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እያሰበች መሆኑን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል። ሰሞኑን አሜሪካ ሻዕቢያ ወታደር እያንቀሳቀሰ መሆኑን፣ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ጠቅሳ መግለጫ አውጥታለች። አቶ ገብሩ “መረጃ አለኝ” በማለት ለሪፖርተር እንዳሉት ፈረንጆቹ ትህነግን አይደግፉም። “ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፣ ብናሸንፍም፣ ብንሸነፍም እንዋጋ” የሚለው ድምዳሜ መጨረሻው ምን ይሆን?