“ሾልኮ የወጣው ሚስጥራዊው ሰነድ ” ተብሎ የተሰራጨው መረጃ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው ላጋለጡት ወንጀል የሰጠውን መልስ ተከትሎ የተሰጠ ይመስላል።
ሪፖርተር ቲዩብ አቶ ገብሩ አስራትን “የድርጅቱን ሚስጢር በዚህ ደረጃ ማጋለጥ…” ብሎ ለተየቃቸው ደብቆ ካልሆነ በስተቀር ከዚህም በላይ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ጥርጥር እንደሌላቸው ገልጸዋል። አያዘውም ምን አልባትም በመንግስት ሚዲያ ለፕሮፓጋንዳ እንዲውል ማድረጉ ላይ ካልሆነ በስተቀር የትህነግ ሰዎች ሌብነት ሊሸፈን እንደማይችል አመልክተዋል።
አሁን ደርስ የማይታወቁ እስር ቤቶች መኖራቸውን፣ ገዳዮች እንዳሉና በርካታ ወነጀሎች እንደሚፈጸሙ ያመልከቱት አቶ ገብሩ አስራት፣ ትህነግ አሁን ቢሰረዝም ቀድሞ የሞተ ድርጅት መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ሾልኮ ወጣ ከተባለው ሰነድ ጋር ተያያዥነት ስላለው የአቶ ገብሩን አስተያየት ቀንጭበን ወሰድን እንጂ ዋናው መነሻ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የከፍተኛ ጦር መኮንኖች ስም ተነሳ በሚል ያወጣው መረጃ ነው።
” የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመሆናቸው ብቻ ያወቁትን ሚስጥር እሰከ መጨረሻ መጠበቅ ሲገባቸው ለርካሽ ገበያ አቅርበዋል ” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት አቶ ጌታቸውን ወርፎ መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም። በዚሁ መግለጫ ላይ ” ጥቂት ወንጀለኞችን ለማዳን ሲባል በህዝብ ስም መነገድ ይቁም ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ምላሽ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ፅህፈት ቤት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሯቸውን ንግግሮች አስመልክቶ የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫው አቶ ጌታቸው ለፋና ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃለመጠይቅ ” የህግ ልዕልና ለማረጋገጥ ያለመ ሳይሆን የህዝቡን የትግል ታሪክና ቀጣይነት የሚያጎድፍና የሚያጨልም በቂም በቀል የታጨቀ ነው ” ሲል ገልፆታል።
” በስልጣን ቆይታቸው የታዩ ወድቀቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ አካል ሲያላክኩና ከሳሽ ሲሆኑ ሰንብተዋል ” ያለው ፅ/ቤቱ ” ይህ ወደ ሚድያ ፕሮፓጋዳ የወረደ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ” ብሏል።
የፅ/ቤቱ መግለጫ ፤ አቶ ጌታቸው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስመልክቶ በብዙ ጥረት ተጠንቶ ወደ እጃቸው የገባ ኮፒ ያልተደረገ ሰነድ በወቅቱ ተጠያቂነት ሳያረጋግጡ ቀርተው አሁን በማህበራዊ ሚድያ እንዲሰራጭ አደርገዋል ሲል ይከሳል።
” ይህ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ሊያጠቋቸው የፈለጓቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ፍትህና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጎዳ በጥናቱ ተሳትፎ የነበራቸውና አካላትና ቤተሰቦቻቸው ጭምር ለአደጋ የሚያጋልጥ የነውር ነውር ነው ” ሲል በምሬት ወቅሷል።
” የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመሆናቸው ብቻ ያወቁትን ሚስጥር እንደ አንድ የህዝብ ብሄራዊ ጉዳይ እሰከ መጨረሻ መጠበቅ ሲገባቸው ለርካሽ ገበያ ማቅረባቸው ማንነታቸው ያሳየ ተግባር ነው ” ሲል አቶ ጌታቸው ረዳን ወርፉዋቸዋል።
የፕሬዜዳንት ፅ/ቤቱን መግለጫ ተከትለው ወድያውኑ ምላሽ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ ” የተጠናው ጥናት ተንተርሶ ወደ እርምጃ እንደማይገባ ስላወቅኩኝ ወደ ሚመለከተው የበላይ አካል መረጃውን ልኬዋለሁ ” ብለዋል። ስም ባይጠቅሱም ሰነዱን ከፌደራል መንግስት አስረክበዋል። ከትግራይ እንደወጡ አስቀድመው ሰነዱ እጃቸው ላይ እንዳለ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
አቶ ጌታቸው ” በጥናት ሰነዱ መሰረት ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ከሚገባ ተጠያቂዎች እንዳንዶቹ ከአገር ወጥተዋል ” ሲሉ ሆን ተብሎ እንዲኮበልሉ መደረጉንም አመልክተዋል።
” ሰው መሸጥ (slave trading in modern parlance ) ለትግራይ ህዝብ የማይመጥን ወንጀል ነው ‘ የሚል አገላለፅ በፕሬዜዳንት ፅህፈት ቤት የወጣ መግለጫ የለም ” ያሉት አቶ ጌታቸው ” ሰነዱ ግለሰቦችን ከማጥቃት ባለፈ የህግ ልዕልና እንዲረጋገጥ ያለመ ነው ” ሲሉ አብራርተዋል።
ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ” በጥናት ሰነዱ የተቀመጠው ሃቅ ነው ጥቂት ወንጀለኞች ለማዳን ሲባል በህዝብ ስም መነገድ ይቁም ” ብለዋል። ከሰሞኑን አንድ ሚስጥራዊ ሰነድ ሾልኮ ወጥቶ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። በማህበራዊ ሚዲያዎችም በርካቶች እየተቀባበሉት እንደሚገኙ ጠቅሶ ቲክቫህ እንዳተመው ከሆነ ሰነዱ ቁልፍ ጉዳዮችን ይዟል።
ሚስጥራዊ ሰነዱ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር (በብዛት ኤርትራውያን በህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር የሚመለከት) እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተጠና ሰነድ ሲሆን በአራት ክፍሎች የተከፋፈሉ 69 ገፆች አሉት።
በሰነዱ በጥናት የተለዩ የወንጀል ተግባራት ፦
– ስልጣን ያለአግባብ በመጠቀም
– በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በመያዝና በማዘዋወር (መኒ ላውንደሪንግ)
– ሰው ማፈንና መሰወር
– በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ከአገር ወደ አገር ማዘዋወር
– የመንግስት ስራ ምቹ ባልሆነ መንገድ መምራት
– ሃላፊነት ባልተገባ መንገድ በመጠቀም
– ሙስና የመሳሰሉት ወንጀሎች መፈፀማቸውን ያረጋግጣል።
በሰነዱ በተጠቀሱ የወንጀል ተግባራት በሰራዊት አመራር ያሉ የነበሩ የጀነራል መዓረግ ካለቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እስከ ቀበሌ አመራር ያሉ አስተዳዳሪዎች ነጋዴዎችና ሌሎች የሚገኙባቸው 231 ተጠርጣሪዎች በስምና አድራሻቸው ተጠቅሷል።
ሰነዱ በህገ-ወጥ መንገድ የተዘዋወሩ ኤርትራውያን ስም የተዘዋወሩበት ቦታና ቀን ፣ ያረፉባቸው ሆቴሎች እንዲሁም ለህገወጥ ዝውውሩ ገንዘብ ገቢ ያደረጉባቸው የባንክ የሂሳብ ቁጥሮች ሰፍረዋል። የጥናት ሰነዱ የሰው ማስረጃ ፣ የድምፅ ቅጂ፣ እንዲሁም በድብቅ የተቀረፀ ምስል ያካተተ እንደሆነ ይዘረዝራል።
በሰነዱ በቀንደኛ ተጠርጣሪነት ከተጠቀሱት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ የሆኑት ተወልደ ገ/ትንሳኤ (ዕምበብ) በቅርቡ ከአገር መውጣታቸው ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከፋና ቴሌቪዥን በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል።
አቶ ጌታቸው አስቀድመ ይዘውት እንደወጡ የገለጹትን ሰነድ ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ የተሸሸጉ ወንጀሎችን የሚያጋልጡ መረጃዎችንም እንደሚያካትት እየተገለጸ ነው። ከአዲሱ ፓርቲያቸው ምስረታ ጋር ተያይዞ አያወጡ ያለው መረጃ ሊጎዳቸው እንደሚችል ርዕዮት ሚዲያ ጠቁሟል። መረጃው ሃሰት ይሆናል በሚል ሳይሆን በመንግስት ሚዲያ መናገራቸው ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ገልጿል። ይልቁኑ በርዕዮት በኩል ወይም ዪኤም ኤስ ብኩል መናገር እንደነበረባቸው አመልክቷል።
ለምን በመንግስት ሚዲያ ተናገሩ በሚል አንዳንድ ቅሬታ ቢሰማ፣ አቶ ጌታቸው ዙሩን እንደሚያከሩት ነው እየተሰማ ያለው።