ሻዕቢያና ወያኔ አዲስ የፍቅር ጨዋታ መጀመራቸውን ተከትሎ ሻዕቢያ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች መልቀቁን የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ሰራተኞች በስፋት እየዘገቡ ቢሆንም መረጃው ቅጥፈት መሆኑ ተጋለጠ። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አካል የሆኑ ለኢትዮሪቪው “ቢቢሲ ላይ የተጻፈው እውነት ነው። ተጨማሪ መረጃ የለም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ የሻዕቢያ ወታደሮችን ከያዙት አካባቢ በማስወጣት የአገር ድንበር እንዲያስከብር በተደጋጋሚ ሲጠየቅ እንደነበር በማስታወስ “መንግስት ትክክል ነበር ” ያሉ ዛሬ ሁሉም ዕቅድ እርቃኑን መውጣቱን አመልክተዋል። መከላከያን መሃል አስገብቶ ለመምታትና ከባድ መሳሪያ ዳግም ለመታጠቅ በማቀድ ሲቀርብ የነበረው ጥሪ ዛሬ ሻዕቢያና ወያኔ በጋራ ጦርነት ለመክፈት የያዙትን ዕቅድ ያፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ይፋ መሆኑን ያመልከቱ ” አሁን የተጀመረው ሌላ ቅሰቀሳ ነው። ሻዕቢያን ከወንጀሎቹ ነጻ ማውጣት” ብለዋል።
በዝርፊያ፣ በጭፍጨፋና በአስገድዶ መድፈር ወንጀል በህግ ሊጠየቅ የሚገባው የሻዕቢያ ኃይል ዳግም በይፋ ትግራይ ላይ እየፈነጨ መሆኑ በግልጽ እየታየ ከትግራይ ውልቅ ብሎ መውጣቱን የሚናገሩ የትህነግ ፕሮፓጋንዲስቶች እንደሚሉት ሳይሆን ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል። ዘገባው ትክክል እንደሆነ የሚገልጹ “የትህነግ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች ታዘው የሃሰት መረጃ እያሰራጩ ነው” የተነሳው አንድ የፍተሻ ኬላ እንጂ የተለቀቀ መሬት እንደሌለ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። ዘገባውን ያንብቡ።
“ኢሳያስ ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያልሞከሩት መንገድና ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም” የለም የሚሉ አገር ወዳድ ልሂቃን፣ አሁን ጊዜው ኢሳያስን የማስወገጃ እንጂ እንደቀድሞ የማባበያ ጊዜ እንዳልሆነ እየገለጹ ነው። የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመነበር አካሄዱ ማናምንቴ ቢሆንም በጥንቃቄ ሊያዝ እንደሚገባው አስታውቀዋል። ኦነግም ቅሬታውን አሰምቷል።
በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የድንበር አካባቢዎችን የተቆጣጠሩት የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ወደ ዛላምበሳ በሚወስደው መንገድ ላይ አስቀምጠውት የነበረን አንድ ኬላ ማንሳታቸውን የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከሰሞኑ የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች ለቅቆ ስለመውጣቱ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ሲሠራጭ ቆይቷል። ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ የክልሉ አካባቢዎች ክፍት ስለመሆናቸውም ሲነገር ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች እና ምንጮች ግን የኤርትራ ሠራዊት አሁንም አካባቢዎቹን ለቅቆ እንዳልወጣ ገልጸዋል።
በዛላምበሳ፣ በራማ፣ በሽራሮ እና በባድሜ አካባቢዎች የተያዙ ቦታዎች አሁንም በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ነገር ግን በዛላምበሳ መስመር የሚገኝ አንድ የኤርትራ ሠራዊት ኬላ ግንቦት 10/2017 ዓ.ም. መነሳቱን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል። ምንጩ እንደሚናገሩት ኬላው የተቀመጠው ከትግራይ ጦርነት በኋላ ነበር።
ከአዲግራት ወደ ዛላምበሳ በሚወስደው መንገድ ላይ በነበረው ኬላ ምክንያት በዚህ መስመር የሚያልፉ ሰዎች እና ተሽከርካሪዎች በኤርትራ ሠራዊት ፍተሻ ይደረግባቸው እንደነበርም ገልጸዋል።
ከአዲግራት ወደ ዛላ አላምበሳ በሚገኘው መንገድ ላይ የነበረ እና በኤርትራ ሠራዊት የቆመ አንድ ኬላ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንዲነሳ ሆኗል ብለዋል። በሚያልፉ ሰዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ይደረግ የነበረው ፍተሻም መቆሙን እንደሚያውቁ አክለዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በተለያዩ የትግራይ ክልል የድንበር አካባቢዎች የኤርትራ ሠራዊት እንደሚገኝ ባለሥልጣኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ለምሳሌ በዛላምበሳ አዲ ሀቂ ሰፈር፣ ዝባንሁፅ አካባቢ፣ አዲስ ዓለም አካባቢ በከፊል፣ አዲ ዓሰርተ እና የኢሮብ አካባቢ ዳርቻዎች የኤርትራ ሠራዊት ይገኛል ብለዋል።
ከዛላምበሳ በ20 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ፋጺ ከተማ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጉምሩክ ባለሥልጣን አሁንም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን እንደሚቆጣጠርም አብራርተዋል።
“ከዛላምበሳ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ፋጺ ላይ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የፍተሻ ጣቢያ ስለነበረ በድንበር ላይ መደበኛ የንግድ ልውውጥ ማድረግ አይቻልም” ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሽራሮ እና የራማ ድንበር አካበቢዎች ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ኤርትራ ሠራዊት ለቅቆ አለመውጣቱን ገልጸዋል።
አንድ የሽራሮ አካባቢ ነዋሪ፤ በወረዳው ስር የሚገኙት አዲ ፀፀር፣ ብችላማ፣ ሰምበል፣ ባድመ፣ ሀድሽ አዲ፣ ደምቦ ጉዳሙ እና ደምቦ ሞንጊል የተባሉ አካባቢዎች በኤርትራ ሠራዊት ስር እንደሚገኙ ገልጸዋል። እነዚህ አካባቢዎች ከጦርነቱ በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የነበረባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል።
ነዋሪው፤ “በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጨው ነገር ውሸት ነው። ሁሉም ነገር እስካሁን ባለበት ነው ያለው። ምንም ዓይነት የፌደራል ኃይልም የለም፤ የትግራይ ፀጥታ ኃይልም የለም። የኤርትራ ሠራዊት ብቻ ነው በአካባቢው ያለው” ብለዋል።
በራማ ድንበር አካባቢ የሚገኙ ሌላ ነዋሪም በተመሳሳይ በኤርትራ ሠራዊት የተያዙ አካባቢዎች እና ድንበሩን በተመለከተ አዲስ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጀመራቸውን የሚገልጹት ነዋሪው፤ የአካቢው ነዋሪዎች የኤርትራ ሠራዊት በሚቆጣጠረው አካባቢ ወደ ሚገኝ ወንዝ በመሄድ እንስሶቻቸውን ውሃ እንደሚያጠጡ ተናግረዋል።
“አሁን ሕዝቡ ወደ ወንዝ ይወርዳል፣ አንዳንድ ነገር ያደርጋል። በጎቹን፣ ከብቶቹን ውሃ እያጠጣ ይመለሳል። ሌላ የሚያደርገው ነገር ካለ እንደዚያ ያደርጋል። ከዚህ በፊት እንደዚህ አልተለመደም ነበር አሁን ግን ያለው ሁኔታ ይህ ነው” ብለዋል።
ከኤርትራ በኩል ከብቶች፣ ግመሎች እና ሌሎች እንስሳት አልፈው በሚመጡበት ጊዜም በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
“ግመሎች ሲመጡ የእኛ ቲዲኤፎች [የትግራይ ኃይሎች] አሉ፣ የእነሱም አሉ ተባብረው ያስመልሳሉ። የኤርትራ ከብቶች ወይም የኤርትራ በጎች ተለያዩ እንስሳቶች ሲመጡ እንደዚያ ጥሩ ነገር አለ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ ግን ይፋዊ በሆነ መልኩ የተጀመረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለ ነዋሪው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ማድረጋቸውን ተከትሎ የድንበር ኮሚሽን የሁለቱን ሀገራት ድንበር ካመላከተ በኋላ መሬት ላይ ባለመወሰኑ አሁን ድረስ የሁለቱ ሀገራት ድንበር በግልጽ ሳይለይ ቆይቷል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትን ደግፈው ሲዋጋ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ይገባኛል በሚላቸው እና በሌሎችም የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ ሲነገር ቆይቷል።