መጪው ዘመን የሰው ሠራሽ አስተውሎት(Artificial Intelligence) ወይም የ”AI”መሆኑ ርግጥ እየሆነ ነው። ይታያችሁ በቀጣይ አምስት ዓመታት ወይም እስከ 2025 ዓ.ም በኢኮኖሚው ላይ 17.5 ትሪሊየን ዶላር ይጨምራል። ይህ የቻይናን ጥቅል ሀገራዊ ምርት ያህል ማለት ነው። በዓለማችን በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት የ85 ሚሊየን ዜጎችን የሥራ እድል ቢነጥቅም፤ ለ97 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል።
ይህ በአጠረ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእያንዳንዳችን የሕይወት ቅንጣት የሚነካ ስለሆነ ስለ AI ግንዛቤ መያዝም ስላለበት ወይም AI Literacy መጎልበት ስለሚገባው ብዙሃን መገናኛዎች ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። የዛሬ መጣጥፌ መነሻም ይሄና ሰሞኑን በመዲናች ከAI ጋር ተያይዘው የተዘጋጁ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ናቸው።
አፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን አህጉራዊ ባሕል እና አካታችነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ልትገነባ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚያ ሰሞን የገለጹ ሲሆን፡፡ “አርተፊሻል ኢንተለጀንስን ለአፍሪካ ብልፅግና እና ትብብር” በሚል ሃሳብ እየተካሄደ ባለው “አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ” መርሐ-ግብር ላይም ተሳትፈዋል፡፡
ይህን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የቴክኖሎጂ ልህቀት ሽግግር ከቴክኖሎጂ ለውጥ እና ዝማኔ በላይ መሆኑን፤ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማለት የሰውን ልጅ የማሰብ ችሎታ ከረቀቁ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተሳሰር ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባሕልን ባከበረ መልኩ ከሰው ልጅ ችሎታ ጋር በመዋሃድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው፡፡
ከቴክኖሎጂ ልህቀት አንጻር አፍሪካ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት፤ ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራትን የሚያበረታታ እና አካታች የሆኑ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመገንባት ረገድ አርአያ እየሆነች እንደምትገኝም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት ዘርፍ በአስደናቂ መንገድ ላይ ትገኛለች ሲል የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እውቅና ተሰጥቷታል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ፤ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት ዘርፍ በአስደናቂ መንገድ ላይ መሆኗን፤ ያዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ጠቃሚና ወቅቱን የዋጀ ነው፤ ከማለታቸው ባሻገር በአፍሪካ አካታችና ዘላቂ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በመገንባት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የሕብረቱ ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ገልጸዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ የለውጥ ኃይል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው የሀገራት የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ፣ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ እና የደህንነት ዋስትና የትኩረት ማዕከል ሆኗል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስትራቴጂ አጀንዳ 2063ን ማሳካት የሚያስችል ልማት ላይ መሆኗን እና ይህም ሀገር በቀል ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በማልማት ከሕብረቱ አጀንዳ ግብ ጋር የተጣጣመ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ያሳያል።
ሀገር በቀል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልማት ለአፍሪካ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በዘርፉ የብዝሀ ባሕል፣ ቋንቋና የብዝሀ ዘርፍ ልማትን በማካተት በአስደናቂ መንገድ ላይ መሆኗን አመልክተዋል። የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰው ሠራሽ አስተውሎት በፈጠራ፣ በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ በደህንነትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር የጎላ አበርክቶ እንዳለው፤ ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ መሰነቋን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አዘጋጅነት ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱ ይታወሳል። ከ10 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተሣታፊዎች መገኘታቸውን፤ ኤክስፖው ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያሳየችበት ትልቅ መድረክ መሆኑን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያተረፉ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን፤
የሳይበር ደህንነት መሠረተ ልማት፣ ጥበቃ እንዲሁም በዘርፉ ሊቀረፉ ስለሚገባቸው ችግሮች እና አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የአፍሪካን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለማሳካት ያለውን አስተዋጽኦ የሚያመላክቱ ውይይቶችም መካሄዳቸውን፤ በተጨማሪም ተሳታፊ በሆኑ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻዎች መካከል የልምድ ልውውጦች መደረጋቸውንና አርተፊሻል ኢንተለጀንስን ከዓለም አቀፍ፣ ከአህጉራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች አንጻር የሚተነትኑ ጥናታዊ ጽሑፎች በኤክስፖው ላይ መቅረባቸውን፤ በኤክስፖው ከፍተኛ ተቀባይነትና ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ማስተዋወቃቸውም ተመላክቷል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት /Artificial Intelligence /AI/ጉዳይ ከሳይንስ አልፎ የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የሳይበር ጦርነት፣ የወታደራዊ ዝማኔ፣ የሉዓላዊነትና የልዕለ ኃያልነት እርካብ መቆናጠጫ ከመሆን አልፎ የጂኦፖለቲካ ሚዛን መለካኪያ ከሆነ ውሎ አደረ። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በAI የበላይ የሆነ ዓለምን በመዳፍ ለመጨበጥ ተጨማሪ አቅም ያገኛል። አሜሪካና ቻይና በዚህ ዘርፍ ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቁ ያሉት ለዚህ ነው።
ማን አሸናፊ ሆኖ እንደሚመጣ በቅርብ እናያለን። የAIን ጉዳይ በቁንጽል ሳይሆን በማሕቀፍ ማየት ያስፈልጋል። እንደ ሀገር የሚሰጠው ትኩረትም ይሄን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል። የምዕራባውያን የስለላ፣ የደህንነትና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልሳን የሆነውና ተነባቢው የ”Foreign Affairs”መጽሔት ሰሞነኛ ዕትም በአንድ ጊዜ ከአንድም ሁለት ጥልቅ መጣጥፎችንና ትንተናዎቹን በAI ላይ ማድረጉ ምን ቁምላቸው አበበ በአማራ ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፤ በደቡብ መገናኛ ብዙኀን፤ በጋዜጠኝነትና በታሪክ ባለሙያነት ያገለገሉ ሲሆን፤ የደቡብ ኤፍ ኤምን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም አቋቁመዋል። በፌዴራል ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በአለ በጅምላ በኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። ከአአዩ በቋንቋና ታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን፤ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ተስተጓጉሏል። ጥልቅ ሀሳብ ያዘሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ፁሑፎችን በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ ጋዜጦች በማውጣት ይታወቃሉ። ያህል ገዥ አጀንዳ እየሆነ እንደመጣ ያረጋግጣል።
ጀምስ ማኒካና ማይክል ስፔንስ በገራ፤ “The Coming AI Economic Revolution”በሚል ርዕስ ባስነበቡን መጣጥፍ፤ የAI አንድ ዘርፍ የሆነው አዲሱ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም ጄነሬቲቭ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ብቻ ለዓለም ኢኮኖሚ በዓመት 4 ትሪሊየን ዶላር ያበረክታል። በዓለማችን በግዙፍነቱ 4ኛ እንደሆነ የሚነገርለት የጀርመን ጥቅል ኢኮኖሚ 4 ትሪሊየን ዶላር መሆኑን እዚህ ላይ ልብ ይላል።
እንግዲህ ይህ ሌሎች እንደ አውቶሜሽን ያሉ የAI ዘርፎች ለኢኮኖሚው ከሚያመነጩት 11 ትሪሊየን ዶላር በተጨማሪ መሆኑ ነው። በAI ባቡር መነሻንና መዳረሻን ጠንቅቆ አውቆ በጊዜ መሳፈር ወሳኝ ስለሆነ ነው ትኩረት ተሰጥቶ የምናየው። ኢትዮጵያ አበክራ ከሶስት ዓመታት በፊት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቋቁማ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በተለያዩ ተቋማት ሥራ ላይ ለማዋል እየጣረች ያለችው ለዚህ ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በማሰልጠን ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ይገባል ሲሉ የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አማካሪና በebs የቴሌቪዥን መርሀ ግብር አዘጋጅ ሰለሞን ካሳ፤ በኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚገኝበት ደረጃና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በዚያ ሰሞን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በእርሻ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርትና በሌሎች በርካታ አገልግሎቶች ላይ እንደሚተገበር፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለኢትዮጵያ ክፍተትን በመሙላት፣ ወደኋላ ያስቀረን እና ያልተቀላጠፈ ሥርዓታችንን ለማዘመን ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በዚህ ሂደት አልፈው ከሀገራቸው አልፈው ለዓለም ብዙ ማበርከት እንደሚችሉ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ብዙ ዘርፎች እንዲወለዱ ምክንያት መሆኑን፤ ዘርፉን እንደ ኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለ ሀገር በቀል ተቋም ገርቶ በራስ ልክ ማሰልጠንና ለበጎ ተግባር ማለትም ለሀገር ጥቅምና ልማት ማዋል ግድ እንደሚልም አሳስበዋል። በነገራችን ላይ AI ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰው በ70 ዓመታት ውስጥ ነው። ከአንድም ሁለት ሶስቴ የገጠመው ፈተና ከእነ አካቴው ደብዛውን ሊያጠፋው ተቃርቧል። እገረ መንገድ የዚህ ተአምራዊ ቴክኖሎጂ እርሾ የሆነውን የኢንዱስትሪ አብዮት እናውሳ።
የኢንዱስትሪ አብዮት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ተጀምሮ በ19ኛው መክዘ ተጠናክሮ የቀጠለ ወሳኝ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እምርታ ነው። አዳዲስ ፋብሪካዎች የተፈጠሩበት፣ የእንፋሎት ኃይል በስፋት ጥቅም ላይ የዋለበት፣ ማሽኖች ወደ ሥራ የገቡበት፣ ምርትና ምርታማነት የጨመረበት እና ከተሞች የተስፋፉበትና ዛሬ የምንገኝበት ዓለም የተበየነበት ታላቅ ክስተት ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ሶስት የኢንዱስትሪ አብዮቶች የተካሄዱ ሲሆን አራተኛውን ደግሞ ተያይዘነዋል።
ሁሉም የየራሳቸውን አዳዲስ የፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ማዕበል አስነስተዋል። የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ አብዮት ችቦ በእንግሊዝ ተለኩሶ ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ የተቀጣጠለ ሲሆን የዘመነ ፋብሪካና የእንፋሎት ኃይል መለያው ናቸው። ሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በ19ኛው መክዘ መገባደጃ ተጀምሮ እስከ 20ኛው መክዘ መጀመሪያ የቀጠለ ሲሆን እንደ መኪናና አውሮፕላን ያሉ መጓጓዣዎች፤ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው።
ሶስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከ20ኛው መክዘ አጋማሽ ዛሬ ድረስ የቀጠለው ሲሆን የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት፣ አውቶሜሽን፣ ሮቦቲክስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች የተስፋፉበትና በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው። ብዙ ሊቃውንት አሁን የምንገኝበትን ጊዜ የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረበት፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀናጀበት፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደ ሥራ የገባበት፣ በይነ መረብ እያንዳንዱን የሕይወት ቅንጣትና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማዳረስ የጀመረበት ከመሆኑ ባሻገር በአኗኗራችንና በግንኙነታችን ላይ የዝሆን ዳናውን እየተው ያለ ምዕራፍ ነው። እጃችን የገባን ቴክኖሎጂ ተለማምደነውና ተዋውቀነው ሳናበቃ እጃችን ላይ የሚያረጅበትና በፍጥነት የሚለዋወጥበት ዘመን ነው።
ለብዙዎቻችን የሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ ግኝትና ቴክኖሎጂያዊ እመርታ የቅርብ ጊዜ ክስተት ቢመስለንም የዘርፉ ልሒቃን ግን ጥንስሱ ጥንታዊ ነው ሲሉ ሀተታ ተፈጥሮንና ሥነ ቃልን በዋቢነት ያወሳሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተስፋም ስጋትም ይዞ ወደፊት እየመጣ ያለው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ግን የተጀመረው በ20ኛው መክዘ አጋማሽ ሲሆን የኮምፒውተር ሊቃውንት ስልተ ቀመር ወይም አልጎሪዝምና አስበው የሚሠሩ ማሽኖች ወደ ሥራ እየገቡበት ያለ ጊዜ ነው።
በ1943 ዓ.ም ዋረን ማክኩሎችና ዋልተር ፒትስ በጋራ በነርቭ አውታረ መረብ የሚታገዝ ሂሳባዊ ሞዴል ወይም mathematical model of neural መፍጠራቸው ለዛሬው ሰው ሠራሽ አስተውሎት እርሾ ሆኖ አገልግሏል። በ1950 ዓ.ም አለን ተርኒግ እንደ ሰው ማሰብ የሚችል ማሽን ፈልስፎ ሙከራ አደረገ። በ1950ዎቹና 60ዎቹ General Problem Solver (GPS) እና ሎጂክ ቴዎሪስትን ጨምሮ በርከት ያሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞች በለጸጉ።
በ1956 ዓ.ም የዳርትማውዝ ጉባኤ “ሰው ሠራሽ አስተውሎት”ራሱን ችሎ እንዲጠና ከመወሰኑ ባሻገር ዛሬ የምንጠቀምበትን ይሄን መጠሪያውን አገኘ። በዚሁ ጉባኤ የተሳተፉ የዘርፉ ሊቃውንት AI ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረጉ። በ1970ዎቹና 80ዎቹ በAI (Artificial Intelligence) ዘርፍ የሰውን ልጅ የመወሰን አቅም የሚተካከል የኮምፒውተር ፕሮግራም ለማበልጸግ ርብርብ ይደረግ ነበር።
ዳሩ ግን በ1990ዎቹ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ ምርምሮቹ መቀዛቀዝ ጀምረው ነበር። በ21ኛው መክዘ ደግሞ እንደገና ማንሰራራት ጀመረ። ከዚህ በኋላ ነጮች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ ነው። ሰውን ተክተው የሚሠሩ፣ ስልተ ቀመርን algorithm የሚረዱ ማሽኖች ሥራ ላይ መዋል ጀመሩ። በርካታ መረጃዎችን አብላልተው የሚሠሩ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኮምፒውተሮች ወደ ሥራ መግባታቸው ዘርፉን ያጎለብተው ጀመር።
አሁን አሁን AI የማይገባበት የሕይወት ቅንጣት የለም። በጤናችን፣ በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን፣ በመረጃ አፈላለጋችን፣ በፖለቲካችን፣ በትምህርታችን፣ በኢኮኖሚያችን፣ በምርምራችን፣ በግብርናችን፣ በማዕድን ፍለጋና ልማታችን፣ በአገልግሎት አሰጣጣችን፣ ወዘተረፈ እሱ በዚያ አለ። ለሰው ልጅ በርካታ ትሩፋት ይዞ የመጣ ቢሆንም ስጋት መደቀኑ አልቀረም።
የሰው ሠራሽ ክህሎት በዚህ ከቀጠለና ያለ ሰዎች ጣልቃ ገብነትና ተሳትፎ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ከጀመረ የሰውን ልጅ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ ይችላል የሚል ስጋት እየፈጠረ ነው። የArtficial Intelligence AI ጉዳይ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል ይሉናል በጎግል የሰው ሠራሽ ክህሎት ቤተ ሙከራ የዲፕማይንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴሚስ ሀሳቢስ። ብዙዎቹ በAI ላይ ሙከራ እያደረጉ ያሉ ተመራማሪዎች እጃቸው ውስጥ የገባው ቴክኖሎጂ እጅግ አደገኛ መሆኑን በቅጡ የተገነዘቡ አይመስሉም ይላሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው። በዘረ አዳም ሕልውና ላይ አደጋ ስለደቀነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከተለያዩ ምንጮች ያጠናቀርሁትን መረጃ እንዲህ ላጋራችሁ ወደድሁ።
Artficial Intelligence ወይም AI ግስጋሴ በሰው ልጆች ሕልውና ላይ የደቀነው አደጋ፤ ክፉኛ ያሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለ6 ወር እንዲቆም በግልጽ ደብዳቤ መጠየቃቸው የእዚያ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር። ኤለን መስክን ጨምሮ የAI አባቶች በመባል የሚታወቁ ከ1100 በላይ የዘርፉ ጉምቱ ሊቃውንት በፉክክርና በውድድር፤ እየተለቀቁ ያሉ የAI ግኝቶች በዚሁ ከቀጠሉ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ አደጋ ሊደቅኑ ስለሚችሉ እንዲቆሙ መንግሥትንም ኩባንያዎችንም ተማጽነዋል።
ተማጽኖው የመጣው ጉግልና ማይክሮ ሶፍት ራሱን ችሎ የሚሠራ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከለቀቁ በኋላ ነው ይለናል የእንግሊዙ ዜና አገልግሎት ሮይተርስ። በግልጽ ደብዳቤ እንዲቆም ከጠየቁት መካከል የStability AI ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤማድ ሞስታ፤ ዮሹዋ ቤንጊዎ፣ ስቱዋርት ሩሶ፣ የአፕል መሥራች ስቲቭ ወዚናክ ሌሎች ኢንዱስትሪው ላይ የሚሠሩ ጉምቱዎች፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጣሪዎቹን ጨምሮ ማንም ሊቆጣጠረው፣ ሊረዳውና ሊተነብየው የማይችል አደጋ በሰው ዘር ላይ ስለደቀነ እንዲቆም ተማጽነዋል። ሲቆም ደግሞ የዘርፉን ተዋናዮችን ያሳተፈ፣ ለሕዝብ ግልጽ የሚሆንና ክትትል የሚደረግበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ፈጠራ ሰዋዊ ነው። የሰው ልጅ ላለፉት 300,000 ዓመታት ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን፣ የምግብ አሠራር ዘዴዎችን፣ የፖለቲካ ማኒፌስቶዎችን፣ ማኅበረሰቦችን፤ በአጠቃላይ ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮችን ፈጥሯል ይሉናል አንድሪው ቾውና ቢሊ ፔሪጎ በጋራ በTIME መጽሔት ባስነበቡን መጣጥፍ። በዚህ ቅጽበት እንኳ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም Artificial Intelligence/AI/፤ ሰዓሊውን ተክቶ ረቂቅና ውብ ስዕሎችን እየሳለ፣ ሰዎችን ሆኖ በኢሜል መልስ እየሰጠ፣ ሙዚቀኛውን ሆኖ ሙዚቃን እየቀረጸ ነው።
ወይም ዋና ሥራ አስፈጻሚውን ተክቶ ስለ ኩባንያው የዕቅድ አፈጻጸም ለታዳሚው ገለጻ እያደረገ፤ አልያም በኮምፒውተር ኮድ የተፈጠረ ስህተትን ለይቶ መፍትሔ እየሰጠ፤ የሕንጻ ግንባታ ንድፍ እያዘጋጀ፤ ተማሪውን ተክቶ እየተፈተነ፤ ጋዜጠኛውን ተክቶ መጣጥፍ እየጻፈ፤ ለሕመምተኛው የጤና ምክር እየሰጠ፤ ተከሳሹን ተክቶ ጥብቅና ቆሞ ሊሆን ይችላል።
ምን አደከማችሁ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ያልገባበት የሕይወት ቅንጣት የለም ማለት ይቻላል። የመድኃኒትንና የቤት ዋጋን ከማውጣት አንስቶ እስከ መኪና መገጣጠምና በማሕበራዊ ሚዲያ የምንመለከተውን ማስታወቂያ እስከ መወሰን ደርሷል። በዚህ ተገርመን ሳናበቃ አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም Generative AI ወደ ሥራ እየገባ ነው ይሉናል እነ አንድሪው በጽሑፋቸው።
ይሄኛው አስተውሎት ጥራትና ጥልቀት ያለው አዲስ ጽሑፍ፣ ምስልና ድምጽ መፍጠር የሚችል ነው። አዲሱ የሰው ሠራሽ ክህሎት ወይም Generative AI ማሕበራዊ ሚዲያ ጥቅም ላይ ከዋለበት ጊዜ አንስቶ አስገራሚው ቴክኖሎጂያዊ ግኝት ወይም እምርታ ነው። የዚህ ግኝት አካል የሆነው ChatGPT የተሰኘው የድረ ገጽ ማፈላለጊያ ወይም ሰርች ኤንጅን ለምንጠይቀው ነገር ሁሉ ምላሽ መስጠት የሚችል ሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው።
ሌላው አዲሱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም Dall-E የምናልመውንና የምንመኘውን ስዕል መሳል የሚችል ነው። በተለይ ChatGPT ባለፈው ጥር ሥራ ላይ ከመዋሉ ከ100 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት፤ ኢንስታግራምና ቲክቶክ ይዘውት የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብሯል። በየቀኑ 13 ሚሊየን ደንበኞች እየተጠቀሙበት ይገኛል። በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ እንደ ChatGPT ያሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎቶች ወደ ገበያው ለመግባትና ተጠቃሚዎችን ለማፍራት የሞት ሽረት ፉክክር ላይ ተጠምደዋል። ከMidjourney እስከ Stable Diffusion እና GitHub’s Copilot ውድድር ላይ ናቸው ይሉናል የመጽሔቱ ፀሐፊዎች።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com