የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ታዋቂውን በስራ ፈጣሪ ቅድሚያ የሚነሱትን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን እና “ጀነሲስ ኢንቨስትመንት ሰርቪስ” የተባለ ኩባንያን ጨምሮ ህገወጥ በሆነ መንገድ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮችን ለህዝብ በመሸጥ ገንዘብ ሲያሰባስቡ በነበሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
የአማርኛው ካፒታል ጋዜጣ እንዳስታወቀው ባለስልጣኑ በሰጠው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ህገወጥ የሰነድ ሽያጭን በመጠቀም ከህዝብ ገንዘብ በማሰባሰብ ተግባር ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።
በተለይም በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ እና በ”ጀነሲስ ኢንቨስትመንት ሰርቪስ” ኩባንያ ላይ እየተካሄዱ ያሉት ምርመራዎች በህገ መንግስት የተረጋገጠ የመሰማት እና የመከላከል ሙሉ መብታቸው በተጠበቀ ሁኔታ እንደሚከናወኑ ባለስልጣኑ አረጋግጧል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ ህብረተሰቡ ከካፒታል ገበያ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
በተለይም በንግድ ድርጅቶች ምስረታ ላይ ሲሳተፉ የንግድ ምዝገባ እና ምስረታ ሰነዶችን ከሚመለከተው አካል እንዲያረጋግጡ እንዲሁም ገንዘብ ከመክፈላቸው በፊት በባለስልጣኑ ፈቃድ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ብቻ ምክር እንዲፈልጉ ጠቁሟል።
ባለስልጣኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም ለማቅረብ የሚሞክሩ አካላት ካሉ ለባለስልጣኑ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በእንደዚህ አይነት ህገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter