የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ጉባዔ በቀጣናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በመገምገም ተግባራዊ እርምጃዎችን በጋራ ለመውሰድ ከስምምነት መደረሱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ። በስብሰባው ላይ ከሰላሳ በላይ አገራት ተሳታፊ ሆነዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ታዜር ገ/እግዚአብሔር በሰጡት መግለጫ እንዳሉት “በመረጃ ትብብር የቀጣናውን ደኅንነት ማጠናከር” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ የተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ጉባዔ የሚፈለገውን ግብ አሳክቷል። ቁልፍ በሆነው የቀጠናው ሰላም ላይ የጋራ አቋምና አስተሳሰብ በመያዝ ከስምምነት ላይ ደርሷል።
በጉባዔው “የአንድ ሀገር የፀጥታ ችግር የአንድ ሀገር የራሱ ችግር ብቻ አይደለም” የሚለው ሐሳብ የጉባዔው ትኩረት እንደነበር ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። በዚህ አግባብም የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከል በጋራ መሥራት ወሳኝ እንደሆነ በቀጠናው አገራት ዘንድ ከስምምነት ተደርሶበታል።
በአገራቱ የደኅንነት ተቋማት መካከል፤ የደኅንነት ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የመረጃ ልውውጥ እንዲኖርም ከመግባባት ላይ መደረሱ የስምምነቱ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የየአገራቱ የደህንነት ተቋማት መረጃ ከመመጋገብ ጀምሮ በቀጠናው ስጋት ላይ አስፈላጊ ነው የሚሉትን ትብብር ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በተካሄደው በዚህ ጉባዔ ከአፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ የተውጣጡ ከሰላሳ በላይ አገራት መሳተፋቸውንም ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
የጉባዔው ተሳታፊዎች ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ የሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል። ጉብኝቱ አፍሪካውያን ከተባበሩ እንደ ህዳሴ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት መፈፀም እንደሚችሉ ለማሳየት ዕድል ፈጥሯል። ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅምና ሃብት የሰሩት ትልቅ ፕሮጀክት ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህም በላይ በግድቡ ዙሪያ የሚነዙ የተዛቡ መረጃዎችን ለማጥራት አመቺ አጋጣሚ ሆኗል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ተሞክሮ መቅሰማቸውን አንስተዋል፡፡