አዲስ አበባ: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን እንዳለ ይህ ሐዋርያዊ አስተምህሮ የኛን ተእልኮና ተልእኮው ያስፈለገበትን ምክንያት አጉልቶ ያሳያል ነው ያሉት።
ለእግዚአብሔር መታዘዝ አቅቶን ነው የወደቅነው ያሉት ቅዱስነታቸው ዛሬም የምንነሣው ከእምነት የተነሣ መታዘዝን ገንዘብ ስናደርግ ነው ብለዋል። ከሁሉ በፊት እምነት ይቀድማል፤ ከሱ በኋላ ደግሞ ለእምነቱ በሙሉ ልብ መታዘዝ ይከተላል፤ ይህ ሲኾን መዳን እና ትንሣኤ ይገኛል፤ ዓለም በእግዚአብሔር እየተደረገላት ያለ ጥሪ ይኸው የመታዘዝ ጥሪ ነው ብለዋል።
ይህንን መለኮታዊ ጥሪ ለዓለም የማድረስ ኀላፊነትም ለኛ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተሰጠ እንደኾነ ሐዋርያው አስገንዝቧል ነው ያሉት። ኀላፊነቱ ሲሰጠን ከነመሣሪያው ነው፤ እሱም ፀጋ እና ሐዋርያነት ነው፤ እኛም እሱን ተቀብለናል፤ እንግዲያውስ የተቀበልነውን ፀጋ እና ሐዋርያነት በዓለም ውስጥ ላለው ሕዝበ እግዚአብሔር አገልግሎት ማዋል ከኛ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ጊዜ የሌለበት ክፍለ ዓለም የለም ያሉት ቅዱስነታቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ወኪሎች ሊቃነ ጳጳሳት በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያ እና በአውስትራሊያ የሚገኙ ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናንን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ይህ እድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መለኮታዊ ተልዕኮውን በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ምቹ መደላድል እንደፈጠረለትም ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በመነሣት በየክፍለ ዓለሙ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃነ ጳጳሳት ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሻገር የየአካባቢውን ሕዝብ በማስተማር እና በማቀፍ የተጣለባችሁን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በትጋት እና በንቃት መወጣት ይኖርባችኋል ብለዋል።
በማዕከል ኾኖ እየመራ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚህ ተልዕኮ ምቹ መደላድል የመፍጠር ኀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡ ትምህርተ ሃይማኖትን እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የተማሩ እና በጥልቀት የተገነዘቡ፣ ብስለትም ያላቸው፤ በቋንቋና በሥነ ልቦና እውቀት የላቀ ሀብተ ፀጋ ያላቸውን በሐዋርያነት እያሠለጠነ በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ሊያሰማራ ይገባል ነው ያሉት።
ለሌላው በብቃት መድረስ እንችል ዘንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሲኖዶሱ መንበር በሚገኝባት ምድረ ኢትዮጵያ ከመቸውም የተሻለ ሥራ በመሥራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሕዝቡንም ማገልገል ይገባናል ብለዋል።
በሲኖዶስ ያልታቀፉ ብዙ ወገኖች በሀገር ውስጥ አሉን ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህ ወገኖች አንዳንዶቹ በተለያየ ምክንያት ከኛ የወጡ ናቸው ብለዋል፡፡ የሄዱት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፣ ሌሎችም ወደ መንጋው እንዲቀላቀሉ በርትቶ መሥራት የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው። ፀጋን እና ሐዋርያነትን የተቀበልንበት ዋናው ምክንያት ይህንን ለማድረግ ነውና ነው ያሉት።
ከሁሉ በፊት ያለንን አቅም እና ብቃት በአግባቡ መገንዘብ ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው ለፈጣሪው በቆራጥነት የሚታዘዝ ምዕመን፣ ወጣት፣ ካህን አለን፤ ይህ ትልቅ ፀጋ ነው፤ ይህንን ፀጋ እግዚአብሔር ለእግዚአብሔር መንግሥት በሚመች ሁናቴ ዝቅ ብሎ ማገልገል የክብር ክብር ነው ብለዋል።
ይህንን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሐቅ፣ በቅንነት፣ በትጋት እና በታማኝነት ቆመን ካገለገልነው እና አባትነታችንን እና መሪነታችንን በመልካም አሠራር በትክክል በኅሊናው እንዲቀረጽ ካደረግን፣ ይህ ኀይል ከጎናችን እንደማይለይ እርግጠኞች መኾን እንችላለን ነው ያሉት።
ሃይማኖቱ የሚጠይቀውን ሰብዕና እና ቁመና ይዘን ከተገኘን ያለውን ብቻ ሳይኾን ሕይወቱን ሳይቀር ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል የእግዚአብሔር ሕዝብ አለን ብለዋል።
ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንድናስገኝ የተቀበልነውን ፀጋ እና ሐዋርያነት በክብር እንያዝ ያሉት ቅዱስነታቸው
ሕዝባችን የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ በኢኮኖሚውም ከድህነት የተላቀቀ እንዲኾን፤ ሰላሙ እና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲኾን፣ በማስተማርም በተግባር በመሳተፍም የሕዝቡ መሪዎች እና አርዓያ ኾነን መሥራት ይገባናል ብለዋል።
ከሰላም እጦት የተነሣ በእጅጉ እየተጎዳ ያለውን ሕዝብ ሰላም እና ፍትሕ እንዲያገኝ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ያልታሰበበትን አካሄድ በብስለት እና በንስሐ ማስተካከል አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን አያሳይም ያሉት ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ልማት እና እድገት እናሻግራለን ብላችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እባካችሁ መለስ ብላችሁ እናታችሁ የተንገላታችበትን እዩና በቃ በሉ፤ ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፤ በዚህ አማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ አድርጉ፤ ይህንም ለውድ እናት የሚደረግ ካሣ አድርጋችሁ ውሰዱት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ መልዕክት እና ጥሪም ይህ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለቀጣዩ ጊዜ የሥራ አቅጣጫን የሚያስቀምጠው የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ጉባኤ መጀመሩንም ለኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ክርስቲያን እናበስራለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት አሚኮ