” ምርጫችን ሰላም ነው ፤ አስተዳደራችንን የሚነካ የህወሓት ክፋይ ቡድን አንታገስም” ሲሉ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ሰላማዊ ሰልፈኞች ድምጻቸውን አሰሙ። ” ኋላቀር አስተሳሰብን እንቃወማለን ፣ የሻዕቢያ ተልእኮ ከሚያስፈፅም ሃይል ጋር ግንኙነት የለንም ” በሚል ተቃውሞ አሰምተዋል።
ግንቦት 7/2017 ዓ.ም በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው ከተማ የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት ባላፈው ሳምንት የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚቃወም ሰልፍ ማካሄዳቸው በምስል ተደግፎ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭቷል።
ቀደም ሲል ሰልፉ እንደሚካሄድ ያስታወቁ ሚዲያዎች የሰልፉን መካሄድ አስመልክተው እንዳሉት ከሆነ ሕዝቡ ዶክተር ደብረጽዮን በሚመሩት ትህነግ ላይ ምሬቱን አሰምቷል፤ አስተዳደራቸውን ለማፍረስ የያዘውን ኧቅድ እንዳይሞክረው አሳስበዋል።
ግንቦት 6/2017 ዓ.ም ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የተሰረዘው ህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ባለፈው ሳምንት ወይን ለተባለ የድርጅታቸው ልሳን በሰጡት ቃል ” ድርጅታቸው በክልሉ ደቡባዊ ዞን የአመራር ማስተካከያ እንደሚያካሂድ ” መዛታቸውን ተከትሎ ነው ሕዝብ ቁጣውን ያሰማው።
የዞኑ አስተዳደር በመራውና ባስተባበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ደብረጽዮን የሰጡትን መግለጫ ሙሉ በሙሉ በመቃወም ቡድኑ ያሰበውን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስጠነቀቁ የቁጣ ድምፆች ተሰምተዋል። ሕዝቡ ቁጣውን የገለጸው በምሬት ሲሆን በሌሎች ከተሞችም የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚቅጥል ተመልክቷል።
በሰልፉ ላይ ከተነሱት መፈክሮች መካከል ምርጫችን ሰላም ነው፣ አስተዳደራችን ለሚነካ የህወሓት ከፋይ ቡድን አንታገስም፣ ኋላቀር አስተሳሰብን እንቃወማወለን፣ የሻእቢያ ተልእኮ ከሚያስፈፅም ሃይል ግንኙነት የለንም፣ በምስለኔ አንመራም፣ ወዘተ የሚሉና ሌሎች መፈክሮች መድመጣቸውን ቲክቫህ ካሰራጨው መረጃ ለመረዳት ተችሏል። ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችም በተመሳሳይ ዘግበዋል።
ስጋት የገባቸውና በሰላማዊ ሰልፉ የተገኙ እናቶች ልብን በሚነካ መልኩ ጦርነት ዳግም አንዳይቀሰቀስ ምህላ አድርገዋል። እናቶቹ እንባቸውን እያፈሰሱ መሬት ላይ ተኝተው ምህላ ሲያደርጉ ታይቷል። በዚሁ ወቅት በርካቶች ምህላውን እያዩ ሲያለቅሱ እንደነበር ተመልክቷል። “ጦርነት በቃን፣ ሰላም ነው የምንፈልገው” የሚሉት ሰልፈኞች በእናቶች አማካይነት እንባ እያፈሰሱ ተማጽኖ ማቅረባቸው የሰላም ወዳዶችን ልብ ነክቷል።
በሰላማዊ ሰልፉ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የማይጨው ከተማ ከንቲባ ዮሃንስ አዱኛና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቱ ኪሮስ ፤ ህዝቡ ሰላሙ እንዳይነጠቅ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ንቁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በማይጨው የተደረገው ይህ ሰልፍ ከትህነግ መሰረዝ ጋር ተያያዥነት የሌለው ቀድሞ የተያዘ ፕሮግራም እንደሆነ ከስፍራው መረጃ ማግኘታቸውን፣ ሰልፉ እንደሚካሄድ አስቀድመው የዘገቡ አመልክተዋል።
ሰልፉ በታቀደለት መሰረት መከናወኑና መጠናቀቁን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ዜና በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች በተመሳሳይ “ጦርነት አንፈልግም” የሚሉ ሰለፈኞች አደባባይ በመውጣት ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩትን ትህነግ እንደሚያወግዙ እየተነገረ ነው።