“ኢዜማ የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄ በአግባቡ የሚረዳው እና መብትን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅን የሚደግፈው ተግባር ነው፡፡ በእርግጥ መብትን ለማስከበር የሚኬድበት ስልት ግን ዜጎችን ለአደጋ የማያጋልጥ ሊሆን ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለን። ሁላችንም እንደምንረዳው የስራ ማቆም አድማ የማድረግ መብት ለጤናው ዘርፍ ሲሆን ቀጥተኛ ገፈት ቀማሹ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት የሚመጣው የሕብረተሰብ ክፍል መሆኑ እሙን ነው።” ሙሉ መግለጫውን ከስር አይንብቡ
ኢዜማ መብትን በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ መጠየቅን ይደግፋል!
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ላለፉት ረጅም ዓመታት ከሙያቸው ጋር በተገናኘ በርካታ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ እንደነበረ ይታወቃል። ሆኖም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግስት አካል ቀና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በቸልተኝነት በማየት ተጨባጭ ያልሆነ ተስፋ ከመስጠት የዘለለ ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ መፍትሔ ሲሰጥ አልተስተዋለም፡፡
በተለይም ላለፈው አንድ ወር የጤና ባለሙያዎች ጥያቄያቸውን በፅሁፍ ጭምር እንዳሳወቁ እና መልስ እንዲሰጣቸው በአደባባይ እየጠየቁ የሚገኙ ቢሆንም መንግስት ለጉዳዩ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒው እንቅስቃሴ ሲያደርግ መታየቱ አግባብነት ያለው ተግባር አይደለም፡፡
የባለሙያዎቹን ጥያቄ የመጠየቅ ህገመንግስታዊ መብት አክብሮ መንግስት በግልፅ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠቱ፣ ችግራቸውን የመረዳት ፍላጎት እንዳለው ለማሳየት ሙከራ አለማድረጉ እና ማስፈራሪያ አዘል አቅላይ መንገድን መከተሉ ሲብስም የተደረጉ ሙከራዎች ካሉ በወቅቱ በተገቢው መንገድ አለማሳወቁ ሃላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት የሚመነጭ የመንግስት ስህተት ነው።
የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄዎች ተገቢ መልስ የሚሰጥ የመንግስት አካል በመጥፋቱ ባለፈው ሳምንት ጥያቄው ከፍ ብሎ ወደ ከፊል ስራ ማቆም አድማ አምርቷል። በዚህም ምክንያት የጤና አገልግሎት ፈላጊው የማሕበረሰቡ ክፍል ለእንግልት እና ለስቃይ እየተዳረገ ይገኛል፡፡ በዚሁ ከቀጠለም ማሕበረሰቡ ለተጨማሪ እንግልት እንዳይዳረግ ያሳስበናል፡፡
ባለሙያዎቹ ፖለቲካዊ ዓላማ እንደሌላቸው እና የትኛውም የፖለቲካ አካል ጥያቄያቸውን ተንተርሶ ትርፍ ለማግኘት እንዳይንቀሳቀስ ደጋግመው ማሳሰባቸው፤ ከኢዜማ መርህ ጋር የሚስማማ በመሆኑ መልዕክቱን በማክበር ኢዜማ ምንም አይነት ሀሳብ ላለመሰጠት በጥንቃቄ ሲመለከት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው እንቅስቃሴ ወደ መፍትሔ ከማምራት ይልቅ እየተወሳሰበ ሕዝቡን ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍል ብሎም ለተጨማሪ ሀገራዊ ትርምስ የሚጋብዝ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ደረጃ ላይ መገኘቱ አሳስቦናል። ሒደቱ በዚሁ ከቀጠለ በተግባር ለባለሙያው ጥያቄ መልስ ከማስገኘት ይልቅ ጠቃሚ ወዳልሆነ ሀገራዊ አለመረጋጋት የማምራት አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡
ኢዜማ የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄ በአግባቡ የሚረዳው እና መብትን በሰላማዊ መንገድ መጠየቅን የሚደግፈው ተግባር ነው፡፡ በእርግጥ መብትን ለማስከበር የሚኬድበት ስልት ግን ዜጎችን ለአደጋ የማያጋልጥ ሊሆን ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለን። ሁላችንም እንደምንረዳው የስራ ማቆም አድማ የማድረግ መብት ለጤናው ዘርፍ ሲሆን ቀጥተኛ ገፈት ቀማሹ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት የሚመጣው የሕብረተሰብ ክፍል መሆኑ እሙን ነው። ይህ ከመሆኑ አንፃር አጣዳፊ ህክምና የሚፈልጉ ዜጎች በስቃይ ውስጥ የመቆየት ብሎም የመኖር ያለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት በመሆኑ እንዲሁም ተያያዥ የሞራል ጥያቄ የሚያስነሳ ከመሆኑ አንፃር ትክክለኛ ስልት አይሆንም፡፡
ይህን ታሳቢ በማድረግም ወደ መፍትሔው ለመሄድ እና ከአላስፈላጊ ውጥረት ለመውጣት
1ኛ. መንግስት ስህተቱን አምኖ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እየተደረገ ካለው የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የጤና ባለሙያዎችን እንዲፈታ ብሎም በመገናኛ ብዙኃን ወጥቶ ለባለሙያዎቹ ጥያቄዎች ያለውን መረዳት በአግባቡ እንዲገልፅ እንዲሁም ለመፍትሔው ከባለሙያዎቹ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ቃል እንዲገባ እንጠይቃለን፡፡
2ኛ. የጤና ባለሙያዎችም ከስራ ማቆም አድማው ተመልሰው የመፍትሔው አካል ለመሆን በጋራ እንዲሰሩ እንጠይቃለን።
3ኛ. የጤና ባለሙያ ማህበራትን ያቀፈ እና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ያካተተ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ፣ በመካከለኛ ጊዜ እንዲሁም በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በመለየት ግብረ ኃይሉ ለባለሙያው እና ለማህበረሰቡ የደረሰበትን ውጤት በመገናኛ ብዙኃን እንዲያሳውቅ ምክረ ሀሳባችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም በባለሙያዎቹ ደጋግሞ እንደተባለው ከዚህ ሂደት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከርን እኛም አብዝተን የምንፀየፈው መሆኑን አስምረን እያረጋገጥን! ይህን መጥፎ ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ሀገራዊ ትርምስ እና ሁከት በመፍጠር መንግስት ላይ ያለን የፖለቲካ ቅሬታ መወጣጫ ለማድረግ መሞከርም ሆነ ሌሎች አድማዎችን አቀጠጣጥሎ የመንግስት ስልጣን ለመነቀነቅ የሚሞከር የሞኝ ሙከራ ጊዜው ያለፈበት የከሰረ መንገድ አድርገን የምንረዳው መሆኑን ለመግለፅ እንፈልጋለን፡፡
በዚህ የመብት ትግል ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ስትሳተፉ እስር እንግልት እና አፈና ለደረሰባችሁ የጤና ባለሙያዎች ሁሉ የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ መብትን መጠየቅ በምንም መልኩ ሊያሳስር እና ሊያሳፍን እንደማይገባ በዚህ መንገድ ጥያቄውን ለማፈን መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም ድርጊቱን እኛም አጥብቀን የምናወግዝ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
ግንቦት 10/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ