የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ የሚመራው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በሚከተለው ዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ሳቢያ ክልሎችን ሲያቋቋም የተሽከርካሪዎች ታርጋ በክልል፣ በከተሞች፣ እና በተለያዩ ስያሜዎች እንዲተኩ ማድረጉ ይታወሳል። አሁን የተሰማው ዜና ይህን አሰራር አስቀርቶ “ኢት” በሚል እንደሚተካ ተሰምቷል።
ETH”፣ እንዲሁም “ኢት” የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ታስቦ የተዘጋጀው አዲሱ ሰሌዳ፣ ለቁጥጥር እና ለምዝገባ ዓላማ የሚያገለግሉ መረጃዎችን የሚሰጡ ምሥጢራዊ ምልክቶችን ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል። ከቢቢሲ የወሰድነው ዜና ከስር ያንብቡ።
በኢትዮጵያ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ‘ኢት’ የሚል መለያ እና የኢትዮጵያ ካርታ ያለበት አዲስ የመለያ ሠሌዳ ቁጥር እንዲኖራቸው የሚያደርግ መመሪያ ጸደቀ። በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የወጣው መመሪያ በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ ያሉ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ላይ የሚቀመጠውን የተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች መለያዎችን አላካተተም።
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶች እና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 በሚል መጽደቁን ባሳወቀው በዚህ ሰነድ ላይ በአገሪቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ እንደሚቀየር ገልጿል።
ይህ የተሽከርካሪዎች መለያ ቁጥር ሠሌዳ መለወጥ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ያደረገ እንዲሆን እና የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን፣ የሀብት ብክነት እንዲሁም የሐሰተኛ ሠሌዳዎችን ለመቆጣጠር መሆኑ ተጠቅሷል።
አዲስ በወጣው የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶች እና ምልክቶች መወሰኛ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 መሠረት በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የሚውሉት የሠሌዳ ቁጥሮች ተመሳሳይ መለያ እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ተደንግጓል።
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በወጣው መመሪያ ክፍል ሁለት ስር ስለተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳ ዓይነቶች እና ምልክቶች በሚል እንደተጠቀሰው ሁሉም የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳዎች በእንግሊዝኛ እና በግዕዝ ፊደላት ኢትዮጵያን የሚያመለክት አጭር ጽሁፍ እና የሀገሪቱ ካርታ ይኖራቸዋል።
“በሀገሪቱ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ የኢትዮጵያ ካርታ እና ሀገራችን ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት “ETH”፣ እንዲሁም “ኢት” የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡”
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ አሰጣጡ ሦስት የላቲን ፊደላትን እና አራት ቁጥሮችን በመጠቀም ተከታታይ ቁጥር ያላቸው የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎችን እንዲመረቱ እንደሚያደርግም መመሪያው ላይ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎች የቀለም ኅብር፣ ፊደላት በተጨማሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎቹ ሲመረት ለቁጥጥር እና ለምዝገባ ዓላማ የሚያገለግሉ መረጃዎችን የሚሰጡ ምሥጢራዊ ምልክቶችን እያንዳንዱ የሠሌዳ ዓይነት እንዲኖረው ይደረጋል።
በዚህ መመሪያ መሠረትም የመለያ ቁጥር ሠሌዳዎቹ የተሽከርካሪዎችን ባለቤት፣ የሚሠጡትን አገልግሎት እና የኃይል አጠቃቀምን የሚያመለክቱ ቀለማት እንዲሁም ሌሎች መለያዎች እንደሚኖራቸው መመሪያው ላይ ተጠቅሷል።
በዚህም መሠረት በኤሌክትሪክ ወይም ታዳሽ ኃይሎች የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ከሌሎች በተለየ መልኩ “አረንጓዴ ትራንስፖርት (Green Transport)” የሚል የጽሁፍ መለያ እንደሚይዝ መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ “ልዩ መግለጫ ያለው የተለየ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ” የሚፈልጉ ግለሰቦች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ለሚጠይቅ “እንደሁኔታው በልዩ ሁኔታ ሊሰጣቸው” እንደሚችል የሚኒስቴሩ መመሪያ ያስረዳል።
መመሪያው እንደሚገልጸው የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው አዲስ የሠሌዳ ዓይነት ከዚህ ቀደም በተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ላይም ተግባራዊ ይሆናል።
መመሪያው በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች “የቀድሞውን ሠሌዳ ለመዝጋቢው አካል በመመለስ አዲስ የተሸከርካሪ የመለያ ቁጥር ሠሌዳ” መውሰድ እንደሚኖርባቸው መመሪያ ላይ ተጠቅሷል።
ተሽከርካሪዎቹ ነባሩን ሠሌዳ በመመለስ አዲሱን የሚወስዱት “ሚኒስቴሩ በሚያዘጋጀው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት” እንደሆነም መመሪያው ገልጿል።
በአጼ ሚኒሊክ ዘመን የመጀመሪያዋ ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ከገባች ጊዜ አንስቶ ለመኪኖች የመለያ ቁጥር መሠጠት እንደተጀመረ የሚነገር ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ወደ ሥልጣን በመጡት አስተዳደሮች በአገሪቱ ቢያንስ ሦስት ጊዜ የተሽከርካሪዎች መለያ ሠሌዳ ቁጥር ለውጥ ተደርጓል።
በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው የሠሌዳ ቁጥር፣ ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የተቀየረ ሲሆን፣ በደርግ ዘመን የነበረው ደግሞ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ለውጥ ተደርጎበታል።
በኢህአዴግ ዘመን ለአገልግሎት የበቃው እና እስካሁንም በሥራ ላይ ያለው የተሽከርካሪዎች መለያ ቁጥር ሠሌዳ ‘ኢት’ የሚል መለያ ካላቸው ከተወሰኑ ተሽከርካሪዎች ውጪ አብዛኞቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ስም ሁለት ፊደላትን የያዙ ናቸው።
ዜናው የቢቢሲ ነው
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter