የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም ቲክ ቶክ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እያባባሰ መሆኑን በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል።በቲክ ቶክ በሚደረግ ማሸማቀቅ ሀገር ጥለው የሚሰደዱ ሴቶች መኖራቸውም ተመልክቷል።የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የጥላቻ ንግግሮችን መቆጣጠር አለመቻላቸው ደግሞ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል ተብሏል።
ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪሲሊንስ የተሰኘው የብሪታኒያ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በዚህ ወር ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ፣ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭቶችን እያባባሱ ነው ።
የድርጅቱ የጥናት እና ምርምር ሥራ አስኪያጅ ፌሊሺቲ ሞልፎርድ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት “በኢትዮጵያ በበይነመረብ ላይ የጥላቻ ንግግር እስከ ግድያ የሚያደርስ አሉታዊ ውጤት አስከትሏል።
በጥናቱ መሰረት ባህላዊ የሥርዓተ-ፆታ ሚናዎችን የሚቃወሙ፣ በአመራር ቦታ ላይ ፣ በስፖርት ዘርፍ ያሉ ወይም ለሴትነት እና ለሴቶች መብት በሚሟገቱ ሴቶች ላይ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸዋል።የነፃነት ፖድካስት አዘጋጅ ፅዮን ብሩክ በጥናቱ ትስማማለች። ፅዮን እንደምትገልፀው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም በቲክ ቶክ በሚተላለፉ ይዘቶች የተነሳ በሴቶች ላይ ከበይነመረብ ዘለፋ አልፎ አካላዊ ጥቃት ይደርሳል።
ችግር የተሞላበት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ወርቅነህ ድሪብሳ በበኩላቸው ፣በኢትዮጵያ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም በተለይ ቲክ ቶክ ችግር የተሞላበት ነው ይላሉ።
ድምፅ 2የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ወርቅነህ ድሪብሳ
በተለይ እይታን እና የተከታይን ቁጥር ለመጨመር ሆን ተብለው የሚሰሩ በሴቶች በአካል ጉዳተኞች የዘለፋ እና የጥላቻ የሰዎችን ክብር የሚነኩ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር እና ቅጣት አለመኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው ይገልፃሉ።
ያም ሆኖ እነዚህ የግለሰብን እና የማኅበረሰብን ክብር በሚነኩ ይዘቶች ከመወገዝ ይልቅ እነሱን የሚያበረታታ እና በተለያዩ ድርጅቶች ማስታወቂያ በማሰራት የተለዬ ጥቅም እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ደግሞ ቲክ ቶክ በኢትዮጵያ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ያብራራሉ።
ይህም ሴቶችን በማሸማቀቅ ከተሳትፎ በመገደብ እና ያሉትን የጥላቻ ንግግሮች በማስፋፋት በማኅበረሰቡ ያደረሰው አሉታዊ ተፅዕኖው ቀላል አይለም።
ተንታኞች እንደሚናገሩት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙ ጊዜ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮችን መቆጣጠር እና ማጣራት ባለመቻላቸው የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።
በቲክቶክ ሴቶችን ማሸማቀቅ እና ከተሳትፎ መገደብ
ታሪኳን ለአፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ያጋራችው ሌይላ ምስክር የዚህ ገፈት ቀማሽ ናት።በኢትዮጵያ የሥርዓተ-ፆታ መብትን በሚመለከት በበይነመረብ በምታቃርባቸው ፅሁፎች ብዙ ተከታዮችን ያፈራችው ሌይላ ነገር ግን የሀገር ውስጥ ቋንቋ ይዘት ክትትል ባለመኖሩ በቲክ ቶክ በደረሰባት ዛቻ እና ማስፈራሪያ ለስደት መዳረጓን ተናግራለች።
የሌላ ችግር የጀመረው ጥቅምት 22 ቀን ሴቶች ከሚጎዷቸው ወንዶች እንዲርቁ የሚመክር ቪዲዮ በቲክ ላይ ከለጠፈች በኋላ ነው።የሌላ የቪዲዮ ይዘት በአንዳንድ የቲክ ቶክ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ዘንድ መልዕክቱ «በወንዶች ላይ የተደረገ የጥላቻ ዘመቻ» እና የሀገሪቱን ሀይማኖትና ባህል የማያከብር ነው መባሉንም የዜና ወኪሉ አስፍሯል። የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አያይዞም በሌሎች ፅሁፎች ሌይላ፤በኢትዮጵያ ህግ በወንጄል የሚያስቀጣውን ግብረ ሰዶማዊነትን እንደምትደግፍ ተደርጎ መቅረቡንም ጠቁሟል።በዚህም የግድያ ዛቻዎችን ጨምሮ እሷን ዒላማ ያደረገ የቲክቶክ ቡድን እንደነበረም ለዜና ወኪሉ ተናግራለች።በደረሰባት ዛቻ ምክንያትም ቤተሰቧ፣ ስራዋን እና ያላትን ሁሉ ትታ ወደ ጎረቤት ሀገር መሸሿን ገልፃለች።ይህ ክስተት የስነ ልቦና እና የገንዘብ ችግር እንደፈጠረባት ተናግራለች።
በአማርኛ ፣ በትግርኛ እና የአፋን ኦሮሞ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ይዘቶችን በተገቢ ሁኔታ ማስተካከል ባለመቻሉ ቲክክ ቶክ ለተከሰተው ችግር የተወሰነ ኃላፊነት እንደሚወሚወስድ ሌላ ተናግራለች።በስርዓተ ጾታ ላይ ያተኮረው የነፃነት ፖድካስት አዘጋጇ ፅዮን ጉዳዩን« አስፈሪ »ስትል ትገልፃለዋች።
ለይላ ለዜና ወኪሉ እንደተናገረችው «በቲክ ቶክ ላይ በኢትዮጵያውያን ወንዶች የተሰሩ ብዙ ቪዲዮዎችን ተመልክቻለሁ ስለሴቶች አሰቃቂ አስተያየቶችን ሲሰጡ አይቻለሁ ነገር ግን ምንም እየተደረገ አይደለም» ብላለች።ፂዮን ብሩክ የለይላን ሀሳብ ታጠናክራለች።
የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ሀላፊነትን እንዲወጡ ማስገደድ
ቲክ ቶክ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደገለፀው «የጥላቻ ንግግሮችን እና ሴትነትን ዝቅ የሚያደርጉ ይዘቶችን እንደማይታገስ እና 92 በመቶ የሚሆኑ ይዘቶችን ለእነርሱ ሪፖርት ከመደረጉ በፊት በቴክኖሎጂ እና በሰዎች ጥምረት አማርኛን ጨምሮ ከ 70 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች በመጠቀም ያስወግዳል።
ያም ሆኖ ባለሙያዎች እንደሚሉት ችግሩን ለመቀነስ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ሀላፊነትን እንዲወጡ ማስገደድ ያስፈልጋል።የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የበለጠ ኃላፊነት እንዲወስዱ ለማስገደድ ከሚሞክሩ አገሮች መካከል ኬንያ አንዷ ነች። የኬንያ ፍርድ ቤቶች የፌስቡክ ዋና ኩባንያ በሆነው በሜታ ላይ በመድረኩ ላይ በቀረቡየጥላቻ ንግግሮችን ላይ በቅርቡ ብይን ሰጥቷል። ከነዚህም አንዱ በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም በፌስ ቡክ ስሙን፣ ፎቶውን እና አድራሻውን ጨምሮ የትግራይ ወታደራዊ ሀይሎች አባል ነው ተብሎ ከተለጠፈ በኋላ፤ የተገደለውን የዩንቨርስቲ መምህር መአረግ አማረን ያካትታል።
የጅማ ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህርሩ ወርቅነህ ድሪብሳ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ ቲክ ቶክ ካደረሰው ችግር ብዛት እና ጥልቀት አንፃር ለመፍትሄው ዘግይተናል ይላሉ። ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመፍታት የረዥም እና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ይጠቁማሉ።
በሌላ በኩል የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎችም የይዘት ክትትል እንዲያደርጉ ማስገደድ ሌላው መፍትሄ መሆኑንም ይገልፃሉ።
የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የይዘት ክትትል መቀነስ እና መዘዙ
ሜታ በጎርጎሪያኑ ያለፈው ጥር ወር በዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርገውን የእውነታ ማጣራት መርሃ ግብሩን ማብቃቱን አስታውቋል። ይህ ርምጃ ደግሞ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ችግሩ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አለ።በእስያ-ፓሲፊክ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ የእውነታ ማረጋገጫ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ የሚገኘው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤እንዳሰፈረው «የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የይዘት ክትትል እንደገና ካልተጀመረ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ ልዩነቶች እና ስጋቶች በበይነመረብ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ባለባቸው ሀገራት፤ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።»ሲሉ፤ የሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪሲሊንስ ሀላፊ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ግጭት እና ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ውጥረት በነገሰባት ኢትዮጵያ፤ሁኔታው ጥላቻ እንዲያጎለብት ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዳይታረም ያደርጋል። ሲሉ ኢትዮጵያዊቷ የዲጂታል መብት ባለሙያ መግደላዊት ጌታሁን ለዜና ወኪሉ አስረድተዋል።
ጸሃይ ጫኔ DW
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter