የ32 ዓመቷ ዩክሬናዊት ካታሪና ክሩፒካ የጡቷን መጠን ለመጨመር በቀዶ ሕክምና የገባላትን ኢምፕላንት እንዳስወጣች በማኅበራዊ ሚዲያ ስትናገር በርካቶችን አስገርሟል።
የሰውነትን ቅርጽ ወይም መጠን ለመለወጥ ወደ ሰውነት የሚገቡ የተለያዩ ዓይነት ኢምፕላንቶችን (implants) ከሰውነታቸው የሚያስወጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ካታሪና በኢንስታግራም 7.5 ሚሊዮን ሰዎች የጻፈችውን አንብበዋል። ከሰውነታቸው ኢምፕላንቶች ለማስወጣት የሚፈልጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች መልዕክት ልከውላታል።
“ትልቅ ጡት ደስተኛ እንደማያደርገኝ ገባኝ። ጤነኛም ቆንጆም አያደርገኝም። ልጄ እንደኔ ትልቅ ጡት እንዲኖራት እንደምትፈልግ ስትናገር ኢምፕላንቱን ለማስወጣት ወሰንኩ። ለልጄ ጥሩ ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ” ብላለች።
ኢምፕላንቶችን ማስወጣት ለምን አስፈለገ?
የዓለም ቀዳሚው የሰውነት ማስዋቢያ ቀዶ ሕክምና ተቋም ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ኤስተቲክ ፕላስቲክ ሰርጀሪ እንዳለው፣ ከጡታቸው ኢምፕላንት የሚያስወጡ ሴቶች ቁጥር በ2019 ወደ 46.3 በመቶ ከፍ ብሏል።
ጡት የማሳደግ ቀዶ ሕክምና ከ1990ዎቹ እስከ 2000ዎቹ በ5.4 በመቶ ሲጨምር፣ ከ2022 እስከ 2023 ደግሞ በ13 በመቶ ቀንሷል።
ለውበት በሚል በሚደረገው የጡት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አነስ ያለና ተፈጥሯዊ የሚመስል ጡት ማሠራት የሚፈልጉ ሴቶች አሉ።
የአሜሪካ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማኅበር ኃላፊ ዶ/ር ክርስቲ ሐሚልተን “በ2025 ሴቶች የሚፈልጉት መልክ ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው የተለየ ነው” ትላለች።
በ90ዎቹና በ2000 አካባቢ ትልቅ ጡት ነበር የሚፈለገው። አሁን ደግሞ አነስ ያለ የጡት መጠን ተፈላጊ ሆኗል።
ስብ በጡት ውስጥ በማስገባት ወይም ጡት ከፍ እንዲል ማድረግ የተለመዱ የጡት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ዓይነቶች ናቸው።
የብራዚል የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብሩኖ ሀርኮኖፍ እንደሚለው፣ ትልቅ ጡት የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ቀንሷል።
“አንዳንድ ሴቶች በድጋሚ ኢምፕላንት ማስገባት አይፈልጉም። ኢምፕላንቶቹ ከ10 እስከ 20 ዓመት ካገለገሉ በኋላ ከሰውነት ወጥተው በሌላ ኢምፕላንት ይተካሉ” ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ከጡት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ግንዛቤ መጨመሩ በርካቶች ኢምፕላንቶችን ከሰውነታቸው እንዲያስወጡ ምክንያት ሆኗል።
“ስለ ሲልከን ህመም እና አውቶኢምዩን ሪአክሽን ያለው ግንዛቤ ከፍ ብሏል። የመገጣጠሚያ ህመም፣ የፀጉር መመለጥ እና የሰውነት ክብደት መጨመር ከሲልከን ህመም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ናቸው” ይላል ዶ/ር ብሩኖ።
“ኢምፕላንቱ ዙርያ ካፕሱል ይኖራል። ህመም ሲከሰት ይሄን ካፕሱል ማስወጣት የግድ ነው” ስትል ዶ/ር ክርስቲ ታስረዳለች።
ካታሪና ካንሰር እንዳለባት ባይነገራትም ከጡቷ ኢምፕላንት ለማስወጣት ወስናለች።
“ብዙ ሴቶች ቀዶ ሕክምናውን የሚያደርጉት ለጤና ሳይሆና ለውበት ነው” ትላለች።
ከዚህ ቀደም ከጡት ጡንቻ ሥር ኢምፕላንት ይገባ ነበር። ይህም ተፈጥሯዊ ያልሆነ ቅርጽ ከመስጠቱም በላይ የጡት እንቅስቃሴን ይለውጣል።
“ረዥም ጊዜ የቆየ ኢምፕላንት ያላቸው ሴቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ጡታቸው ወደ ጎን ይሄዳል” ትላለች ካታሪና።
አሁን ላይ የሚሠራ የጡት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ኢምፕላንቱን ጡንቻ ላይ ስለሚያስቀምጥ፣ ጡት ተፈጥሯዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደርጋል።

እየታየ ያለው ለውጥ መነሻው ምንድን ነው?
ዶክተሮቹ እንደሚሉት ተፈጥሯዊ የሰውነት ቅርጽ ያለው ተቀባይነት ለውጥ እያመጣ ነው።
“አፍንጫ፣ ፊት፣ ጡት እና የተቀረው ሰውነትም ተፈጥሯዊ እንዲሆን ይፈለጋል። መጠናቸው ሲጨምር ተፈጥሯዊ ገጽታቸው እንደሚለወጥ ይታመናል” ስትል ዶ/ር ክርስቲ ታስረዳለች።
“ፊታቸው የተለያዩ ስሜቶችን የሚያንፀባርቅ ሳይሆን አንድ ዓይነት ገጽታ ብቻ ያለው መሆኑ አንደኛው ምክንያት ነው” ይላል የሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ብሩኖ።
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ከታለመለት ምክንያት ውጪ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን በማየት ቀዶ ሕክምናውን ላለማድረግ የሚወስኑ እንዳሉ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
“የሰውነት መጠን የሚጨምር ፊለር በየሦስት ወይም ስድስት ወሩ እንደሚያስፈልጋቸው ለታካሚዎች ስንነግራቸው ሐሳባቸውን ይለውጣሉ” ትላለች ዶ/ር ክርስቲ።
ታካሚዎች በተወሰነ መጠን ጎልቶ የማይታይ የቀዶ ሕክምና አማራጭን ይከተላሉ።
የቆዳን ገጽታ የሚያስተካክለው ኮላገን ስቲሙሌሽን (collagen stimulation) አንደኛው አማራጭ ነው።
ኮላገን ሰውነት ውስጥ በብዛት የሚገኝ የፕሮቲን ዓይነት ሲሆን በአጥንት፣ በቆዳ፣ በጡንቻ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ይገኛል። ዕድሜ ሲጨምር መጠኑ እየቀነሰ ይሄዳል።

ተፈጥሮን መከተል
ካታሪና ተፈጥሮን መከተል እንደምትፈልግ ትናገራለች። ከአሳድጋው የነበረውን ንፈሯን ወደ ተፈጥፈሯዊው መጠን መልሳለች። ፊቷ ላይ ያለውን ሽብሽብ ለመሸፈን የምትጠቀመውን ቦቶክስ (Botox) አቁማለች።
“ስለ መልካቸው የሚጨነቁ ሴቶች እኔን አይተው ይማራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ትላለች።
የተፈጥሮ ውበትን መጠበቅ አዲስ እና እየተለመደ የመጣ አካሄድ ነው።
“አሁንም መዋቢያ ምርቶች እየተሸጡ ነው። ተፈጥሯዊ ገጽታን መለወጥ ሳይሆን ጠብቆ ማቆየት ነው የሚፈለገው” ሲል አንድ የዘርፉ ባለሙያ ያስረዳል።

በ2023 የመዋዋቢያ ዘርፍ ሽያጭ ወደ 44 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
ሴቶች መዋቢያዎችን መጠቀም ባያቆሙም የሰውነታቸውን ተፈጥሯዊ ገጽታ የበለጠ ጠብቆ ማቆየት ይሻሉ።
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ተፈጥሯዊ ገጽታን ጠብቆ የማቆየት ፍላጎት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን የሚያስቀር ሳይሆን፣ የሰውነትን ተፈጥሯዊ ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚለውጥ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን የሚያስቀር ነው።
የዓለም አቀፍ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች መረጃ እንደሚጠቀመው፣ እአአ በ2023 ብቻ 15.8 ሚሊዮን የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናዎች ተከናውነዋል።
ይህም በ2022 ከተመዘገበው ቁጥር 5.5 በመቶ ጭማሪ የታይቷል።
ዋናውን ዘገባ እዚህ ላይ ተጭነው ቢቢሲ ያንብቡ