የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲነት የሰረዘው ትህነግ ባሰራጨው ደብዳቤ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አሸማጋዮች እግዱን አስመልክተው አስቸኳይ ስብሰባ እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበ።
ትህነግ ለአፍሪካ ሕብረትና የተለያዩ ተቋማት እና የስምምነቱ አፈፃፀም ተከታዮች ላላቸው በፃፈው ደብዳቤ ” ትህነግና እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት እርስ በርስ እውቅና ተሰጣጥተዋል ” ሲል ራሱን ከመንግስት እኩል ለማየት ሞክሯል። ራሱን ሊሻር የማይቻል እውቅና እንደተሰጠው አድርጎ ባዘጋጀው ደብዳቤው ይህንኑ እውቅና እየጣሰ መሆኑን ጠቅሶ ኮንኗል።
ትህነግ ምርጫ ቦርድ ለሰጠው ውሳኔ በሰጠው ምላሽ፣ ስብሰባ እንዲደረግለት ከመጠየቁ በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ ትህነግን ከፓርቲነት የሰረዘበት መንገድ “ተቀባይነት የለውም” ያለ ሲሆን “ምርጫ ቦርድ ለአንድ ወገን ያደላ ውሳኔ አሳልፏል” ብሏል።
ትህነግ ችግሮችን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በድርድር እና በንግግር ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቆ በምላሹም የፌደራል መንግስቱ ዳተኝነት መሆኑን ለነጮችና አፍሪካ ህዝብረት በጻፈው ደብዳቤ አመልክቷል።
በዚሁ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የፕርቶሪያውን ስምምነት አደጋ ላይ መውደቁን፣ አደጋ ላይ የጣለውም የፊደራል መንግስት እንደሆነ ጠቅሷል። ትህነግ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ለፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም ለአደራዳሪዎቹ ባሰራጨው ደብዳቤ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል አስቸኳይ የፓናል ውውይት እንዲካሄድ ጫና እንዲደረግ ጠይቋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት የፀጥታው ምክር ቤት ይሄን ጉዳይ አጀንዳ እንዲያደርገው እና በቀጣይ ስብሰባ ሲቀመጥ እንዲወያይበትና የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንዲመረምር አሳስቧል። አክሎም ውይይት እስከሚደረግ የፌደራል መንግሥቱ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንዲሰርዝ ጫና እንዲያሳድር እና ግፊት እንዲያደርግ ” የሚል ተማጽኖ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድን ውሳኔም ሆነ ትህነግ ላሰራጨው ደብዳቤ የፌደራል መንግስት ይህ እስከተጻፈ ድረስ ያለው ነገር የለም።
ትህነግ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደሚጎዳውና ተግባራዊ ሊሆን እንዳይችል እንደሚያደርገው ጠቅሶ ያሰራቸውን ደብዳቤ አስመልክቶ ለቲክቫህ አስተያየት የሰጡት የህግ ባለሙያው አቶ ያሬድ ኃይለማርያም እግዱ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
ለትህነግ መሰረዝ በሁዋላ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እጣፈንታ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ቀርቦላቸው “ የህወሓት ሙሉ በሙሉ ህጋዊ ሰውነት ማጣት የፕሪቶሪያውን ስምምነት አይሽረውም፡፡ በህወሓት የተፈረመውን የፕሪቶርያ ስምምነት የሚፈፅም አካል በዛው ስምምነት ተወልዷል እሱም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው ” ብለዋል። ስምምነቱን በትግራይ በኩል ሲያስፈፅም የነበረው ትህነግ ሳይሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ህወሓት ስምምነቱን ፈርሞ ትግበራውን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አስረክቦዋል፡፡ የፕሪቶርያው ስምምነት የሚተገበረው በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ነው፡፡ ስለ ፕሪቶርያ ስምምነት አተገባበር ክልላዊ መንግስቱን ወክለው አቶ ጌታቸው ረዳ ነበሩ ማብራሪያ የሚሰጡት፡፡ ሐላፊነቱም እሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ነበር፡፡ አሁን ህወሓት ቢሰረዝም የክልሉ ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት ግን አለ፡፡ ይኸው ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት አሁንም ስምምነቱን ያስፈፅማል /ያከናውናል፡፡
ስምምነቱን የፈረመው አካል ነው ስምምነቱን መተግበር ያለበት የሚባል ነገር የለም፡፡ ያኔም ቢሆን ‘ ስምምነቱን የፈረምኩት እኔ ነኝ መፈፀምም ያለብኝ እኔ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አይደለም /የሚል ጥያቄ አላነሳም ህወሓት፡፡ አሁንም በፕረዝደንት ታደሰ ወረደ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ስምምነቱ ህወሓትን ነው የሚመለከተው እኔ አያገባኝም፣ ስምምነቱንም አልፈፅምም ‘ ብሎ ራሱን እስካላወጣ ድረስ ስምምነቱ ፈርሷል ወደሚል ህጋዊ ሙግት አያስኬድም፡፡ ተፈፃሚነቱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ይቀጥላል፡፡