የ82 ዓመቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በፍጥነት የሚስፋፋ የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለባቸው ይፋ ካደረጉ በኋላ አሜሪካውያን በቶሎ እንዲፈወሱ ምኞታቸውን እየገለጹ ነው።
ባይደን ላይ በምርመራ የተገኘው ይህ የፕሮስቴት ካንሰር በወንዶች ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ በአብዛኛው ደግሞ ጥቁሮች በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሚሸኑበት ጊዜ ያይዋቸውን ምልክቶች መሠረት አድርገው ባለፈው ሳምንት መብቂያ ላይ ሐኪም ዘንድ ከሄዱ በኋላ ካንሰሩ እንዳለባቸው እና ወደ አጥንቶቻቸው መስፋፋቱ ተነግሯቸዋል።
ይህ ከ40ዎቹ የዕድሜ ክልል በተሻገሩ ወንዶች ላይ የሚከሰተውን የካንሰር ዓይነት በተመለከተ ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች እዚህ ቀርበዋል።
የፕሮስቴት ካንሰር ምንድን ነው? ማን የበለጠ ተጋላጭ ነው? መከላከል ይቻላል? መልክቶቹ ምንድን ናቸው? ሕክምናስ አለው?
ለበርካቶች ፕሮስቴት ሲባል ሁለቱ የወንድ ልጅ የዘር ፍሬዎች አካባቢ ወይም የዘር ፍሬ ከረጢቱ ውስጥ ያለ አካል እንደሆነ ነው የሚያስቡት።
የኩላሊት፣ የፕሮስቴት፣ የሽንት ፊኛ እና ቧንቧ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፍፁም ሠለሞን ግን ፕሮስቴት ከሽንት ፊኛ በታች ያለ አካል ነው ይላሉ።
እንደ ዶ/ሩ ገለጻ ከሆነ ፕሮስቴት በወንድ ልጅ ብልት እና ፊኛ መካከል የሚገኝ ዕጢ ነው።
ፕሮስቴት የዘር ፈሳሽ የማመንጨት ጥቅም አለው። የወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ወደ ውጪ ሲፈስ ሰባ በመቶ ያህሉን የሚያመነጨው ፕሮስቴት መሆኑን ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።
የወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ሕዋስ የሚዋኘው እንዲሁም ምግቡን የሚያገኘው ከዚህ ፈሳሽ መሆኑን ባለሙያው ይጠቅሳሉ።
ታድያ የፕሮስቴት ችግር ያለበት ወንድ የዘር ፈሳሹ ወደ ውጪ መፍሰሱን ትቶ የሚመለሰው ወደ ፊኛው ነው።
ስለዚህ ይላሉ ዶ/ር ፍፁም ፕሮስቴት፣ የዘር ፈሳሹ ወደ ፊኛ እንዳይመለስ እና ወደ ውጪ እንዲወጣ ይረዳል።
ፕሮስቴት ልክ እንደ ምራቅ አመንጪ እና ታይሮይድ ዕጢዎች ሁሉ ዕጢ (ግላንድ) ነው።
የፕሮስቴት ዕጢ የሚገኘው ወንድ ላይ ብቻ ነው።

ፕሮስቴት ካንሰር
ዶ/ር ፍፁም በየትኛውም የሰውነታችን ክልፍ ላይ ካንሰር ሊከሰት ይችላል፣ ስለዚህም ፕሮስቴትም ለካንሰር ይጋለጣል ይላሉ።
በዓለም ላይ ከስምንት ወንዶች መካከል አንዱ በሕይወት ዘመኑ በፕሮስቴት ካንሰር ይያዛል።
ፕሮስቴት አጥቢ እንስሳት ላይ በሙሉ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ካንሰሩ ከሰው ውጪ የታየው ውሾች ላይ ብቻ ነው።
80 በመቶ ያህሉ ፕሮስቴት ካንሰር ቀስ ብሎ የሚያድግ እንዲሁም ህመም ሳያስከትል ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ነው።
በብዛት የፕሮስቴት ካንሰር በመጀመሪያ ከፕሮስቴት ዕጢ ላይ ተወስኖ ይቆይና ከባድ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ቀስ እያለ የሚያድግ ችግር ነው።
ማን የበለጠ ተጋላጭ ነው?
ለፕሮስቴት ካንሰር አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል አንዱ ዕድሜ ነው።
እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ጥቁር ወንዶች እንዲሁም በቤተሰባቸው ውስጥ የፕሮስቴት ካንሰር የተያዘ ሰው የሚገኝ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎችም ዕድሜያቸው 40 የሞላቸው ወንዶች በየዓመቱ ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።
ዶ/ር ፍፁም በበኩላቸው ፕሮስቴት ካንሰር ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የመገኘት ዕድሉ እጅጉን በጣም አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 30 የሆነ ወንዶች በፕሮስቴት የመያዝ ዕድላቸው አንድ በመቶ ብቻ ነው።
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የፕሮስቴት ካንሰር የሚከሰተው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆናቸው ወንዶች ላይ ነው መሆኑን ዶ/ር ፍፁም አመልክተዋል።
አፍሪካውያን ከነጮች አንጻር ሲታይ በዚህ ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው ግለሰቦች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
ወንድም፣ አባት፣ አያት እንዲሁም አጎቱ በፕሮስቴት ካንሰር የተያዘበት ግለሰብ የተጋላጭነት ዕድሉ ሰፊ ነው።

ከቅርብ ቤተሰብ መካከልም አባቱ በዚህ ካንሰር የተያዘ እና አያቱ የተያዘ ወንድ ዕኩል የተጋላጭነት ልክ እንደሌላቸው ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።
አባቱ ወይንም ወንድሙ በፕሮስቴት ካንሰር የተያዘ ወንድ፣ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከሁለት እና ሦስት እጥፍ በላይ ተጋላጭ ነው።
ሌላኛው መታየት ያለበት በቤተሰብ ውስጥ ካንሰር የተያዘው ሰው በስንተኛው ዕድሜው ላይ ተገኘበት የሚለው ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።
ይህንንም ሲያብራሩ ከ65 ዓመት በታች የፕሮስቴት ካንሰር የተገኘበት አባት፣ ልጁ ለካንሰሩ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል ይላሉ።
ይህም ማለት ልጁ እስከ 5 እጥፍ ድረስ ለፕሮስቴት ካንሰር የተጋለጠ ነው።
ሌላኛው ደግሞ ይላሉ ዶ/ር ፍፁም፣ አባቱ እና አያቱ በፕሮስቴት የተጠቁ እና አባቱ ብቻ የተያዘ ልጅን ብናወዳድር፣ ሁለቱም የቤተሰብ አባላቱ የተያዙበት ግለሰብ የበለጠ ተጋላጭ ነው ይላሉ።
የዘረመል (ጄኔቲክ ሚውቴሽን) ላይ እክል ካለ የበለጠ ለዚህ ካንሰር ያጋልጣል።
ካንሰር በአብዛኛው ሲታይ ሕዋሱ በተነሳበት አካል ወይንም ስፍራ ከመጠን በላይ ይራባል።
ከዚያም በመቀጠል ባለበት አካል ላይ ብቻ ተገድቦ ሳይቀመጥ ወደ ሌላ የአካል ክፍሎች ይሠራጫል።
ፕሮስቴት ካንሰር ተገቢውን ሕክምና በተገቢው ሰዓት ካላገኘ የሽንት ፊኛን ሊያፍን ያችላል።
የፕሮስቴት ካንሰር ዕጢው ላይ ከተራባ በኋላ አጠገብ ወዳሉ የሽንት ቧንቧ እና ፊኛ ይዛመታል።
ከዚያም አልፎ በደም ስር ተሠራጭቶ ወደ ጀርባ ይሄዳል።
ፕሮስቴት ካንሰር ብዙ ጊዜ በደም ስር አድርጎ ወደ ጀርባ፣ አከርካሪ አጥንት እና ሆድ ውስጥ ወዳሉ ንፍፊቶች ይስፋፋል።
ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?
የፕሮስቴት ካንሰርን ለመከላከል አመጋገብን ማስተካከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬ የበዛበት፣ ዓሳ፣ የዓሳ ዘይት፣ የወይራ ዘይት (ኦሊቭ ኦይል) ያለው ምግብ መመገብ ለመከላከል ይረዳል።
ከእነዚህ በተጨማሪ አረንጓዴ ሻይ እንዲሁም ቫይታሚን ዲ መጠቀም የመከላከል አቅምን ያጎለብታል።

የፕሮስቴት ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው?
- ቶሎ ቶሎ ሽንት መመምጣት- በተለይ በምሽት
- ደም የቀላቀለ ሽንት
- የሽንት ማስቸገር ስሜት
- ሽንት ሲወጣ መቅጠን
- በእንቅልፍ ልብ ሽንት ማምለጥ
- የሽንት መቆራረጥ፤ ማስማጥ
- ከሸኑ በኋላ የመጨረስ ስሜት አለመኖር
- ወደ ጀርባ ከተሠራጨ በኋላ ደግሞ የታችኛው ጀርባ ክፍል ህመም
- የእግር ማበጥ ናቸው።
ቅድመ መከላከል
የፕሮስቴት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ቀስ ብሎ የሚያድግ በመሆኑ፣ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመሠራጨት እና ሕይወትን አደጋ ላይ ለመጣል ረዥም ጊዜ ይወስድበታል።
ስለዚህም ቢያንስ በዓመት ወይንም በሁለት ዓመት አንዴ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ ነው።
በተለይ ለካንሰሩ የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው፤ ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።
ቅድመ ምርመራ ለመጀመር የተለያዩ አገራት፣ የተለያዩ መመሪያዎች እንዳላቸው የሚናገሩት ዶ/ር ፍፁም፣ አንድ ሰው ዕድሜው ከ50 አስከ 55 ዓመት ሲሆን ቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ ይመከራል።
ተመሳሳይ የቤተሰብ ታሪክ ያለው ግለሰብ ደግሞ ዕድሜው ከ40 አስከ 45 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እያለ ምርመራውን ቢጀመር መልካም መሆኑን ገልፀዋል።
“ቢያንስ ቢያንስ በየሁለት ዓመቱ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይመከራል” ሲሉ ያክላሉ።
የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና
ከሁሉ በፊት በቤተሰብ ውስጥ ያለን የፕሮስቴት ካንሰር ታሪክን ማወቅ እንዲሁም ወደ አርባዎቹ የዕድሜ ክልል ሲገባም በተወሰ ጊዜው ውስጥ ምርመራ ማድረግ ችግሩ ካለ ስር ሳይሰድ ለማከም ይረዳል።
ምርመራው ተደርጎ የፕሮስቴት ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ የተለያዩ ዓይነት ሕክምናዎች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከእነዚህም ውስጥ በቀዶ ሕክምና ካንሰሩን ማውጣት፣ የጨረር ሕክምና ወይንም ደግሞ የወንድ ልጅ ቴስቴስትሮን ካንሰሩን በዋነኛነት ስለሚመግብ በሰውነት ውስጥ ያለውን የቴስቴስትሮን መጠን ለመቀነስ ሕክምና ይሰጣል።
via BBC