ኢላን መስክ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሾመ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የተባረሩበት የዶጅ ንቅናቄ ኃላፊ ነበር። ዶጅ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የብክንት ቅነሳ መሥሪያ ቤት ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ሲያገለግል ቆይቷል።
መስክ በማኅበራዊ ሚድያው ኤክስ በኩል ይፋ ባደረገው መግለጫ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግኖ ነው ስንብቱን ይፋ ያደረገው። ሲጀመርም ኃላፊነቱ ውስን ነበር።
ቢቢሲ እንደተረዳው ዋይት ሐውስ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ኢላን መስክ የመንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የተሰኘ መለያው እንዲነሳ አድርጓል። የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ዶጅን እየመራ እንደማይቆይ እና ኃላፊነቱ ጊዜያዊ እንደሆነ ሲያስታውቅ ቆይቷል።
“ፕሬዝደንት ትራምፕ ብክነትን እንድቀንስ ዕድሉን ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ። ነገር ግን ዶጅ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ጉምቱ የቴክኖሎጂ ሰው “ልዩ የመንግሥት ሠራተኛ” የሚል ኃላፊነት ተሰጥቶት በዓመት 130 ቀናት እንዲሠራ ተፈቅዶለት ነበር።
ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ባለፈው ጊዜ ስሌት መሠረት በያዝነው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር መገባደጃ 130 ቀናት ይሞሉታል።
ነገር ግን መስክ በትራምፕ የበጀት ረቂቅ አዋጅ “እንደተከፋ” ባስታወቀ ማግስት ኃላፊነቱን መልቀቁ አነጋጋሪ ሆኗል።
የትራምፕ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በትሪሊ የን ዶላሮች የሚቆጠር የግብር እፎይታ እና የመከላከያ በጀት እንዲጨምር የሚያበረታታ ነው።
መስክ የትራምፕ አስተዳደርን ሲቀላቀል 2 ትሪሊየን ዶላር ብክነት እቀንሳለሁ ብሎ ነበር የተነሳው። ነገር ግን ይህን ቁጥር ወደ 150 ቢሊዮን ዝቅ አድርጎታል።
በዶጅ ምክንያት ከ2.3 ሚሊዮን የፌዴራል ሠራተኞች መካከል 260 ሺህ የሚሆኑት ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል።
መስክ ባለፈው ሚያዚያ ከመንግሥት ኃላፊነት ገሸሽ ብሎ ትኩረቱን የግል ኩባንያዎቹ ላይ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።
ኢላን መስክ የዋይት ሐውስ ልዩ ሠራተኛ ሳለ የቴስላ መኪና ሽያጭ 13 በመቶ አሽቆልቁሏል። የቴስላ የአክሲዮን ገበያም 45 በመቶ ወርዶ እነደነበር ጠቅሶ የዘገበው ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ነው።