“የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የስራ ኃላፊዎች ውክልና አለኝ” በሚል በስራ ሥምሪትና በትምህርት ዕድል ስም ዜጎችን የሚያጭበረብሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሕጋዊ የስራ ስምሪት ስምምነት ወዳልተደረገባቸው ሀገራት ከሚደረግ ህገ-ወጥ ጉዞ መቆጠብ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ከ700 በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደተቻለ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በ3ኛው የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪካ ሕብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በቤልጂየም ብራስልስ ውጤታማ ተሳትፎ አድርገዋል ብለዋል።
በስብሰባው የአውሮፓና አፍሪካን ሁሉን አቀፍ ትብብር ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር የአህጉራቱን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በተመረጡ የልማት ፓኬጆች ላይ በትብብር ስለመስራት መነሳቱን አስረድተዋል።
በዚህም በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በታዳሽ ኃይል ግንባታ፣ በግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ፣ በሳይበር ደኅንነትና መሰል ዘላቂ ልማት ላይ በጥልቀት መምከር እንደተቻለ ገልጸዋል።
በጉባኤው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ማስገንዘብ ያስቻሉ ስኬታማ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም በአዲስ አበባ የተስተናገዱ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች የከተማዋን የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ መዲናነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
እነዚሁ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ ጉባኤዎች በኮንፍረንስ ቱሪዝም የመዲናዋን ተመራጭነት ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በስኬት መስተናገዳቸውንም አንስተዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በማይናማር እና በሌሎች ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ኢትዮጵውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
በዚህም በሁለት ሳምንታት ውስጥ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ከ700 በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደተቻለ ገልጸዋል።መንግስት ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ህጋዊ ስራ ስምሪት ውል ወዳልተደረሰባቸው ሀገራት ከመጓዝ መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በሕገ-ወጥና ሀሰተኛ መረጃ ዜጎችን የሚያጭበረብሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በማጋለጥ የመንግስትን ጥረት ማገዝ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።
በውጭ ሀገራት የሚደረጉ የስራ ስምሪትና የነፃ ትምህርት ዕድልን በሚመለከት “የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የስራ ኃላፊዎች ውክልና አለኝ“ በማለት የሚያጭበረብሩ ግለሰቦችና ተቋማት እንዳሉ እንደተደረሰበት ጠቁመዋል።
በዚህም የተለያዩ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ዜጎችን የሚያታልሉ አካላትና ደርጅቶችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።ኢዜአ