ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በአክቲቪስቶቻቸው አማካይነት ከሚያሰራጩት ፕሮፓጋንዳ ጀረባ ለአሸማጋዮቹ የድርድር ዕቅድ ማቅረባቸው ተሰማ። ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ያቀረበችውን ጥያቄ አስመልክቶ የዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት የያዙት የድጋፍ አቋም ሻዕቢያ የድርድር ዕቅድ ለማቅረብ እንዳስገደደው ለማወቅ ተችሏል። ፋኖም ለድርድር እየተንደርደረ መሆኑ ተሰምቷል።
በዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት አገራት፣ አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለሻዕቢያ አሁን ድረስ ያልተቀየረ፣ የቆየ ጥላቻ እንዳላቸው የሚታወቅ ነው። ከምንም በላይ አልሸባብን በማሰልጠና፣ ትጥቅ እንዲደርሰው በመላላክ፣ መሪዎቹን አስመራ ሸሽጎ በማደራጀት የሚከሰሰው ሻዕቢያ የቀይባህር ቀጠና ላይ የተተከለ የሰላም ጠንቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚገልጹ አሜሪካ የአቋም መውሰጃ ጊዜዋ አሁን እንደሆነ ሲያሳስቡ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ይህንኑ ጥሪና ማስጠንቀቂያ መዘገባችን አይዘነጋም።
“የሻዕቢያና የኢሳያስ አፈወርቂ ማብቂያቸው እየተቃረበ ይመስላል። ይህንኑ የሚያረጋግጡ ምልክቶች እዚያም እዚህም እየተሰሙ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የመመለሷን ጉዳይ አጥብቀው በሚፈልጉ ጡንቸኞቹ አገራት ዘንድ አቋም የተያዘ ይመስላል” ሲሉ በመስከረም 2024 ላይ በአውሮፓ ለኤርትራ ዲፕሎማቶች ቅርበት ያላቸው የተቃዋሚ አመራር አስተያየት ሰጥተውን ነበር። እኚሁ አመራር እንዳሉት ይህን የተረዳውና ግብጽን አምኖ ሲንቀሳቀስ የከረመው ሻዕቢያ ወደ ሰላም ውይይት ለመመለስ ዕቅድ ማቅረቡን መስማታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ከለላ በመስጠት ቀውስ እያመረተ ኢትዮጵያን ሰላም በማሳጣት የሚኖረው ሻዕቢያ አሁን ላይ ቀይ ባህርን አስመልክቶ የያዘው አቋም እንደማያዋጣው፣ ግብጽም ከጌቶቿ ትዕዛዝ እልፍ እንደማትል በመረዳት የድርድር ዕቅድ ማቅረቡን የገለጹት የተቃዋሚ አመራር፣ ዝርዝር ይዘቱን አላብራሩም። ይሁንና የኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባህር መመለስዋን ለመቀበል፣ ነገር ግን ዋስትና የማግኘት ዓላማ ያለው ዕቅድ እንደሆነ አመልክተዋል።
አረቢክ ፖስት ኦንላይን Growing relations between Israel and Ethiopia: between military deals, intelligence influence, and an eye on Egypt በሚል ርዕስ ከሳምንት በፊት ባተመው ሰፊ ሃተታ እስራኤል፣ እንግሊዝ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ፣ የመሳሰሉትን አገሮች ጠቅሶ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የመመለሷ ጉዳይ ያበቃለት እንደሚመስል አስነብቧል። በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙትን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔትናሁና አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ተደጋጋሚ ኝኑነት ቀንና ቦታ ዘርዝሮ በማሰረዳት ድምዳሜ የሰጠው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን ጸጥታ የማስጠበቁን ኃላፊነት በይፋ የመረከቧ ነገር አይቀሬ መሆኑ አመልክቷል።
ከዚህ ሁሉ በላይ በግልጽ እንደሚታወቀው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስና ኢትዮጵያ ያላቸው ጥብቅ ግንኙነት አሜሪካና እስራኤል ሳይወዱ በግዳቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚሆኑበትን ዕድል ያጎላዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሃውቲዎች ከየመን የሚሰነዝሩትን ጥቃት አስመልክቶ እስራኤልና አሜሪካ ቀይ ባህር ላይ አዲስ አቋም እንዲይዙ ስላደረጋቸው አረብ ኤምሬጽ ለምታቀርበው ድጋፍ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆን ጉዳይን የሚከታተሉ ይናገራሉ። አረቢክ ፖስትም ይህንኑ ጽፏል።
የሻዕቢያ ተቃዋሚ አመራር የሆኑት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የካታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ መቆየታቸውን ተንተርሶ የሽምግልና ጉዳይ መኖሩን ሲጠቁሙ ቆይተዋል። የሻዕቢያ ተቃዋሚ አመራር እንደሚሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አቋማቸውን ቀይረው ተማጽኖ የላኩት ላሳዑዲ አረቢያ ነው። ሳዑዲ የአሰብን ወደብ እንድትጠቅምበት ኮንትራት ለመስጠት ሞክረው አለመሳካቱ ሻዕቢያን አላስደሰተውም። ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት ኮንትራት በመስጠት ኢትዮጵያ አሰብ ላይ ያላትን ጥያቄ ምን አልባትም በኃይል የማስመለስ አቋም ከያዘች ሳዑዲን ለማስገባትና እረፍት ለማግኘት የነበረው ዕቅድ ነው የተበላሻው። እናም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ላማስኬድ የተወሰነው ከዚህ በሁዋላ ነው።

በድርድር አቅም ማጎልበትና በድርድር ጠረጴዛ ላይ ብዙ ለማኘት የሚያስሽችሉ ግብዓቶችን መያዝ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ሻዕቢያ ዘወትር እንደሚያደርገው ሁሉ በዙሪያው እሱ የሚያስተባበራቸውና የሚመራቸው ድርጅቶች አሰባስቧል። እነዚህ ድርጅቶች በአስቸኳይ ቅርጽ እንዲይዙ ሰሞኑን የነበረው ርብርብም የዚሁ አካል እንደሆነ የዜናው ምንጭ አብራርተዋል።
ቀደም ሲል “የአንዳርጋቸው ልጆች” የሚል ስያሜ በሚሰጣቸው የዩቲዩብ ሚዲያዎች አማካይነት ፋኖ ወደ አንድነት እንዲመጣ አቶ አንዳርጋቸው የከረረ ትችት በመሰንዘር ቅሬታ አቅርበው ነበር። ይህንኑ ተከትሎ ፋኖን ሲደግፉና ሲያሞካሹ የነበሩ በመደጋገፍ ትችት ሲሰነዝሩ የከረሙት ለዚሁ የሻዕቢያ ዕቅድ መሳካት እንደሆነ መረጃውን ያካፈሉን ጠቁመዋል።
ሻኧቢያ ለድርድር ሲቀመጥ ሃይል ለማግኘት እንደ ግብዓት ለመጠቀም አስቦ በጫና አንድ እንዲሆኑ ሲሰራ ቆይቶ አሁን ላይ የፋኖ ህብረት መፈጠሩን የሚያስረዱት የሻዕቢያ ተቃዋሚ ድርጅት አመራር፣ በቅርቡ በትኗቸው እንደሚሄድ ከወዲሁ ለማስታወቅ እንደሚወዱ ገልጸዋል። ሻዕቢያ ለኤርትራም ሆነ ለኢትዮጵያ ጠንቅ እንደሆነ ለማስረዳት መረጃ እንደማያስፈልግ በማስታወቅ ድርጅቶቹ መተቀሚያ ከሚሆኑና ታሪካዊ ስህተት ከሚሰሩ ከመንግስት ጋር ራሳቸውን ችለው ሊነጋገሩ እንደሚገባ ምክር ሰጥተዋል።
ለበርካታ ወራት ኅብረት ለመፍጠር ታስቦ ሲሠራበት የቆየው የአማራ ፋኖ ኅብረት በቋራ ጎንደር መመሥረቱ ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ነው። የኅብረቱ ዓላማና ግብ ወደ አንድነትን ለማምጣትና የተቀናጀ ጥቃት ለመሰንዘር ሳይሆን ዓቅምን አስተባብሮ ለድርድር ለመቅረብ የታለመ እንደሆነ እየተነገረ ነው። እስክንድር ነጋ የሚመራው አፋሕድ ባወጣው መግለጫ “ከተቻለ እንዋሃድ፣ ካልሆነም አንቀናጅ ካልሆነ ቢያንስ እናበብ” ብሏል።
ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከወሎና ከጎጃም የተሰባሰቡ የፋኖ አመራሮች ባደረጉት ውይይት አንድ የፋኖ አደረጃጀት መመሥረታቸውን ተናግረዋል። ስሙንም አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በማለት መሰየማቸውን አስታውቀዋል። እነዚህ ከሻዕቢያና ከትህነግ ጋር ህብረት ፈጥረዋል የሚባሉት አደረጃጀቶች የአማራ ፋኖ በጎጃም፣ የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ – አማራ)፣ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር እና የአማራ ፋኖ በሸዋ ናቸው። ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ቋራ-ጎንደር ባደረጉት ቀናትን የወሰደ መስራች ጉባኤ ግንቦት 01 ቀን 2017 ዓ.ም የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (Amhara Fano National Force) የተሰኘ ድርጅት” መመሥረታቸውን ይፋ አድርጓል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል አወቃቀር ጠቅላላ ጉባኤ፣ ማዕከላዊ ምክር ቤት፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲሁም የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አካቶ ሕገ ደንብ በማፅደቅ ተቋቁሟል። የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አርበኛ መሳፍንት ተስፉ እንዲመሩት መሥራች ድርጅቶቹ መስማማታቸውን መግለጫቸው አስረድቷል።
አዲሱ የፋኖ ኅብረት የደቦ ወይም የጋራ አመራር መርህ የሚከተል ነው። በመግለጫው እንደተመለከተው አስራ ሶስት መሪዎች ያሉበት የድርጅቱን “ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የዲፕሎማሲ እና የአስተዳደር ሥራዎች” የሚመራ “ማዕከላዊ ኮማንድ” መመሥረቱን አስታውቋል።
በአስራ ሶስቱ መሪዎች የሚመራው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ፤ ስብጥር 1ኛ. አርበኛ ዘመነ ካሴ 2ኛ. አርበኛ ሐብቴ ወልዴ 3ኛ. አርበኛ ምሬ ወዳጆ 4ኛ. አርበኛ ደሳለኝ ሲያስብሸዋ 5ኛ. አርበኛ አስረስ ማረ ዳምጤ 6ኛ. አርበኛ ሔኖክ አዲሴ 7ኛ. ጀነራል ተፈራ ማሞ 8ኛ. አርበኛ ዝናቡ ልንገረው 9ኛ. አርበኛ ድርሳን ብርሃኔ 10ኛ. አርበኛ አስቻለው በለጠ 11ኛ. አርበኛ ሳሙኤል ባለዕድል 12ኛ. አርበኛ ማርከው መንግሥቴ 13ኛ. አርበኛ አከበር ስመኘው”
ከሥነአስተዳደር መርህ እና በተለይ ጥቅብ የዕዝ ሠንሠለትን መከተል ከሚያስገድደው ወታደራዊ አወቃቀር አኳያ በ13 መሪዎች የሚመራ ድርጅት ተቋማዊ ቁመና ይዞ ለመቀጠል እጅግ እንደሚከብደው ከወዲሁ አስተያየት ሲሰጥ እየተሰማ ነው። በይፋም ህብረቱ እንደማይሰራ “ህብረት ፈጥረናል” ባሉት አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉና የሚታወቁ የስልክ ልውውጥ ሲያደርጉ ተሰምቷል።
ከዚህ ሌላ ግን የፋኖው ኅብረት የተመሠረተው በመንግሥት ላይ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ሳይሆን ዋንኛው ዓላማ ድርድር በሚካሄድበት ጊዜ ወንበር ለማግኘት እንደሆነ የፋኖን አካሄድ በቅርብ የሚከታተሉ ለጎልጉል አስተያየታቸውን ያለው ዘገባው ምንጮቹ ድርድር ያሉት ሻዕቢያን ስለማካተቱ ያሉት ነገር የለም።
በተለይ እስክንድር የሚመራውና አፋሕድ ተብሎ የሚጠራው አደረጃጀት ኅብረት በመፍጠር የቀዳሚነቱን ሥፍራ በመያዙ ለድርድር ጥሩ ወንበር እያመቻቸ እንደሆነ ሲነገር የቆየ ሁኔታ ነው። በቅርብ በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ድምፅ እስክንድር ወደ ኤርትራ አንድ የድርጅቱን ከፍተኛ ኃላፊ መላኩን እና ከሻዕቢያ ጋር በመነጋገር አስመራ ላይ ቢሮ እንዲከፈትለት ሲጠይቅ ተሰምቷል። ይህን የሚያስታውሱ እንዳሉት ህብረቶቹ ትህነግን ጨምሮ በወታደራዊ ኃይል ስር ለድርድር ከተቀመጡ የሻዕቢያን ፍላጎት የመደራደሪያ አንድ ወሳኝ ነጥብ እንደሚያደርጉ ከወዲሁ ግምቶች አሉ። የአስክንድር ፋኖና ትህነግ በይፋ የአሰብ ወደብ ጥያቄን እንደማያነሱና ከኤርትራ ወገን መሆናቸውን በይፋ አስታውቀዋል። አዲስ የተመሰረተው የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ህብረት ውስጥ ያሉ አመራሮች በይፋ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በይፋ ልክ እንደ ሻዕቢያ በይፋ አውግዘዋል። ትጥቅና የሰው ኃይል ስልተናም ስለሚደረግላቸው እነ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚያራምዱትን አቋም እንደሚያራምዱ ተመልክቷል። ይህን ያነሱት የመረጃው ሰዎች ሁሉም ተመሳሳይ አቋም እንደሚይዙ ያምናሉ።
ጎልጉል እንደሚለው ከሆነ ደግሞ እስክንድር ነጋ “እንዋሃድ፣ አብረን እንስራ ወይም እንናበብ” ሲል ጥሪ ያቀረበለት አዲሱ ህብረት ለድርድር ራሱን ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታ እያመቻቸ መሆኑን አመልክቷል።
በስልክ በተቀረጥሰ ድምጽ እንድተሰማው እስክንድር ቢሮ እንዲከፈትለት፣ ኮማንዶ እንዲሰለጥልለት እና ከባድ መሣሪያ ተኳሽ የጠየቀ ሲሆን በምትኩ አሰብን እንደማይጠይቅ እንዲያውም የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት እንደሆነ ተናግሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን አሁን ካለው የተበታተነ የፋኖ አደረጃጀት እርሱ የሚመራው የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኝ፣ ለማንኛውም ጉዳይ የተሰባሰበ መሆኑን በመግለጽ የተናገረው እነ ዘመነ የሚመሩት የተበታተነውን ፋኖ በእጅጉ ያሳሰበና ያስቆጣ እንደነበር አይዘነጋም።
ከጥቂት ወራት በፊት “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” በማለት ከእስክንድር ጋር አብሮ የሚሠራው አበበ ጢሞ ማስታወቁን ጎልጉል ዘግቦ ነበር።
የእስክንድር የመቅደም አካሄድ የገባቸው የእነ ዘመነ ቡድን ቢሮ በመክፈትም ሆነ ለድርድር ራሳቸውን በማዘጋጀት ወደኋላ መቅረታቸው በመገንዘብ በአፋጣኝ ኅብረት በመፍጠር ለድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው አሁን የመሠረቱትን በ13 ሰዎች የሚመራ የፋኖ አደረጃጀት ለመመሥረት በቅተዋል። በዚህ ሁኔታ በቀጣይ ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ ድርድሮች ከተቻለ ከእስክንድር ፋኖ ጋር ካልሆነም ራሱን ወክሎ አዲሱ የፋኖ አደረጃጀት ለመቅረብ እየተንደረደ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ጠቅሶ አመልክቷል።
“ሻዕቢያ በአቅም ችግርና በዕቅድ መዛባት የውጊያ ዕቅዱን ቀየረ፤ ድርድር ከጅሏል፤ ትህነግ እያፈገፈገ ነው” በሚል ርዕስ ባጋራነው የዜና ዘገባ ከጦርነት በስተቀር ሁሉንም አማራጭ የተጠቀመው ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ላይ ያቀደው ባለመሳካቱ መጨረሻው እና አይቀሬው አማራጭ ዲፕሎማሲና ድርድር እንደሆነ በግምገማው ማመኑን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። የእነ ዘመነ ካሤን ቡድን በሁሉም መስክ የሚያግዘው ሻዕቢያ ዕገዛውን አጠናክሮ መቀጠል ባለመቻሉ ድርድርን ጊዜ መግዣ ወይም እጅ መስጫ እንዳደረገው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑትን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን በተከታታይ በፋና ቲቪ እንዳሉት ሻዕቢያ የኤርትራን ህዝብ ይዞ ወደ ውጊያ አይገባም። ሕዝቡ ተሰዶ አልቋል። ያሉትም ሁለት ሚሊዮን አይፈጁም ስለዚህ የትግራይ ወጣቶችን ለማስፈጀት የያዘው ዕቅድ እንጂ በራሱ የሚያደርገው ነገር እንደሌለ ማመልከታቸው አይዘነጋም።
የጦር ኃይል አሰላለፍንና የወታደር ብዛትን በዳታ አስደግፈው የሚገልጹ ተቋማት እንደሚሉት ኤርትራ እንደቀድሞ ጊዜ አዳዲስ ወታደውር ማሰልጠን ተስኗታል። አንጋፋዎቹንና ሚሊሻዎቹን ሳይጨምር ሻዕቢያ ያለው ዝግጁ ወታደር ሁለት መቶ ሺህ እንኳን አይሞላም። ወጣቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሻዕቢያን ጥላቻ አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። ይህን መረጃ የሚጠቅሱና የውስጥ መረጃ ያላቸው ሻዕቢያ ጦርነት መሸከም የሚችል አቅምና ቁመና እንደሌለው እየገለጹ ነው።
በዚህ መነሻ ሻዕቢያ ኢትዮጵያ አሰብን ትወስዳለች ከሚል ፍርሃቻ የኢትዮጵያን መከላከያ በትግራይና አማራ ክልል ጦርነት ጠምዶ ፋታ ለማግኘት የነደፈው የትርምስ ስትራቴጂ እንደሆነ አቶ ጌታቸው የሰጡት መረጃ ጎልጉል ካለው በላይ ጎልቶ የሚወጣ ይሆናል።
አስራ ሶስት አመራር ያሉት አዲሱ ፋኖ ገና አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ተጠናክሮ ከመሥራት ይልቅ የመፍረስ ወይም የመበታተን አደጋ ውስጥ እንዳለ አፈትልከው የሚወጡ የድምፅ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ ዘመነ የአዲሱ ፋኖ አደረጃጀት መሪ ሆኖ ባለመውጣቱ “በጎንደሬ አንመራም” የሚሉ ድምፆች የተሰሙ ሲሆን ካስፈለገም “ባሕር ዳርን ይዘን እንገነጠላለን” እንጂ ጎጃም ካልመራ በፍጹም በስብስቡ አንቀጥልም ያሉም አሉ። ይህን ገና ከጅምሩ የተፈጠረው አለመግባባት ሻዕቢያን ሊያስደስት እንደማይችል የሚገልጹ ልዩነቱን ለማስተካከል ሩጫ ተጀምሯል።
ሻዕቢያ በሁሉም አቅጣጫ ዋስትና ፍለጋ እየሮጠ ያለው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና በኃይል አሰላለፍ ብልጫ በመያዟ ሲሆን ሻዕቢያ ያቀረበውን ዕቅድ ስለመቀበሏ የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ሻዕቢያ የላካቸውና አሁን ላይ ስማቸውን ለመጥቀስ የማይቻሉ አደራዳሪዎች ከመንግስት ጋር ግንኙነት መጀመራቸውን የሚያውቁት የሻዕቢያ ተቃዋሚዎች አመራር ” እመኑኝ ሻዕቢያ አይተኩስም። ያስተኩስና ድርድሩን አጣድፎ የሚፈልገውን ለማስፈጸም ነው የሚሯሯጠው” ብለዋል።