ሰሞኑንን ንግግር ያደረጉት የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፉወርቂ ይፋ ያደረጉት የኃይል አሰላለፍ ትግራይን የጦርነት ማዕከል ስለሚያደርጋት ሕዝብ ስጋት ውስጥ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው። የትግራይ ሰራዊት አባካት እየከዱ ሲሆን አሰላለፉ ፋይዳ ቢስ ቢሆንም በጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባው የሚጠቁሙም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
በጤና ችግር ሳቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ አጭር ንግግር ያደረጉት ፕረዚዳንት ኢሳያስ፣ የሰሜኑና የደቡቡን ሕዝብ ለሁለት ከፍለው ያቀረቡበትና ጦርነት እንደሚካሄድ ፍንጭ በሰጡበት ንግግራቸው “የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት” አጀንዳቸው ላይ ቀይ ባህርን ለጥፈው ዓላማቸውን ይፋ አድርገዋል።
በቂ ወታደርና ተተኪ ኃይል የሌላቸው ኢሳያስ አፉወርቂ የትግራይንና የአማራን ወጣቶች በማሰለፍ ኢትዮጵያን ለመበተን ይህን ዕቅድ እንደነደፉ አቶ ጌታቸው ረዳ ደጋግመው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ሕዝብ እየተሰደደ አተቃላይ የነዋሪ ቁጥሯ ከሁለት ሚሊዮን እንደማይበልጥ የሚነገርላት ኤርትራ ያላትን አባት ጡረተኛ ጦር ሳይቀር ክተት የጠራች መሆኑ ቀደም ሲል ተገልጾም ነበር። ከእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድንና በተለይም ጎጃም አካባቢ ካለው የፋኖ ኃይል ጋር ግንኙነት የጀመረው ሻዕቢያ ይህንኑ የሰው ኃይል ችግሩን ለመቅረፍ ቢያስብም በትግራም በአማራም በኩል ሰፊ ተቃውሞ ተነስቶበታል።
“ነገሩ አሁን ገባን” በማለት ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ የፋኖ ኃይሎች እጃቸውን እያሰጡ ሲሆን ግንኙነቱን የተቃወሙ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ደግሞ ከኃይላቸው በመነጠል ላይ ናቸው። ይህንኑ የሚያረጋግጥ ዜና እየተሰማ ቢሆንም ህብረቱ መንግስት የሚጥልበት ደረጃ መድረሱን በመግለጽ የፕሮፓጋንዳ ስራ የሚሰሩ አስመራ ድረስ አቅንተው መመሪያ ሲቀበሉ ታይቷል።
እነዚህኑ ክፍሎች እንደሚመሩና እንደሚያደራጁ የሚታወቁ አካላትም ባደራጇቸው ሚዲያዎች ቀርበው በይፋ የኢሳያስን ንግግር እየተነተኑና እያጎሉ ህዝብ ለማንቃት ሲሞክሩ ታይተዋል።
እነሱ ይህን የበሉ እንጂ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ከእነ መሪዎቻቸው ወደ አፋር ክልል በማቅናት ራሳቸውን እያደራጁ እንደሆነ በስፋት መረጃ እየወጣ ነው። እነዚህ ወገኖች ሻዕቢያ ትግራይ ገብቶ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመው እጅግ አስነዋሪና ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ሊዘነጋ እንደማይገባው የሚገልጹ ናቸው።
ከተራ ጭልፋና የቤት ቁሳቁስ እስከ ፋብሪካ ንብረት ተደራጅቶ የዘረፈው የኢሳያስ መንግስት ዳግም ትግራይ ውስጥ እኒፈነጭ መፈቀዱ ያስቆታቸው በገሃድ በሰላማዊ ሰልፍ እየተቃወሙ ሲሆን፣ በመካከሉ ጦርነት ከተጀመረ ትግራይ የጦርነቱ ማዕከል ሆና ለጉዳት እንደምትጋለጥ የሰጉ ከወዲሁ ጥሪ እያሰሙ ነው።
“ኦሮሞነትን አስተሳሰብ አድርጎ ያቀረቡት ኢሳያስ መስመር ለቀዋል። የጤና ችግርም ሳይኖርባቸው አይቀርም። የጤና ችግር ያለበት ሰው የሚለኩሰው እሳት ኤርትራንም ሊበላት ይችላል። ሁሉም ነገር በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባዋል። ” የሚሉ ወገኖች የትግራይ ኃይሎች አንድ ላይ ሊመክሩ እንደሚገባ ደጋግመው እየመከሩ ነው።
ቀደም ሲል ሶስት የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅት ስጋታቸውን ገልጸው መላ እንዲባል ጥሪ ሲያቀርቡ የትግራይ ሕዝብ በራሱ የትግራይ ልጆች ለዳግም መከራ እንዳይዳረግ አሳስበው ነበር። በዚሁ ማሳሰቢያቸው “የታጠቁ ኃይሎች በዚህ እና በዚያ ስላሉ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያጋጥም ይችላል” ብለዋል። ወደ ነጻ መሬት እየተንቀሳቀሱ ያሉ የትግራይ ሰራዊት አባላት ሁኔታም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አመልክተው አዲሱን የክልሉን መሪ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደን መክረው ነበር።
ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየት የሰጡ ደግሞ በትግራይ ክልል የሚስተዋለው የግል ጥቅም አሳዳጅነትና ሥልጣን ወዳድነት በክልሉ አስከፊ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ፖለቲከኛው አቶ ጠዓመ አርዓዶም አመለከቱ። በክልሉ ዳግም ጦርነት ከተጀመረ እጅግ አውዳሚ እና የሕልውና ስጋት የሚፈጥር እንደሆነ አስታወቁ። በትግራይ ሁሉን የሚያካትት ዕርቅ ካልተካሄደ ትግራይን የጦርነት ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል።
አቶ ጠዓመ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የግል ጥቅም እና ሥልጣን ወዳድነትን ተከትሎ በሚፈጠሩ ግጭቶች ክልሉ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት በማወክ ሰሞኑን የተፈጠረው የችሎት ብጥብጥ የክልሉ ሁለንተናዊ ውድቀት ማሳያ ነው። ትግራይ ከገባችበት ችግር እንድትወጣ በክልሉ ብሔራዊ ዕርቅ እና አንድነት በአፋጣኝ መደረግ አለበት ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ለብሔራዊ ዕርቅ እና አንድነት ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም በፍጥነት ተግባራዊ መሆን እንዳልቻለና ከጉዳዩ ክብደት አንጻር ጊዜ የሚሰጠው ሊሆን እንደማይገባ አመልክተዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከጦርነቱ ወዲህ በከባድ ጭንቀት እና ጫና ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ጠዓመ፤ በመሆኑም የማያግባቡ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተው አንድነትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች እና የሕዝብን ጥቅም በማስከበር ላይ ትኩረት በማድረግ የጦርነት ወሬ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ማስቆም ይቻላል ብለዋል።
በፖለቲካው ዙሪያ ውስጣዊ ልዩነት በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻሉ፤ ለግል ጥቅምና ሥልጣን ሲባል በተፈጠረው ግጭት እያደገ በክልሉ አሁን ያለው አስከፊ ገፅታ ሊፈጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ትግራይ አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠለች ወደ ከፋ ጦርነት ትገባለች ያሉት አቶ ጠዓመ፤ ምናልባትም ከእዚህ ቀደም አይታው የማታውቀው በዞን ደረጃ የመከፋፈል እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል ብለዋል። በደቡባዊ ዞን እየታየ ያለው የፖለቲካ ለውጥ የእዚህ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ዳግም ጦርነት ከተጀመረ እጅግ አውዳሚ እና የሕልውና ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ አሁናዊ ሁኔታ እና አሁን የሚስተዋሉት የተለያዩ ችግሮች መከሰት ዋና መነሻው ፖለቲካዊ ውድቀት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የእዚህ መነሻም ሕወሓት (በቅርቡ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ፓርቲ) በውስጡ ያጋጠመው የመምራት ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁኔታውን በማጤን በአፋጣኝ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ ካልተገባ፤ ጦርነቱ በትግራይ ጀምሮ የሚያቆም ሳይሆን ወደ ኤርትራ እንዲሁም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ሱዳንን ጨምሮ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ተስፋፍቶ ሌላ ጂኦግራፊካል ኮንፌዴሬሽን ሊፈጥር ይችላል ብለዋል፤ ትግራይ ለራስዋ እና ለሌሎች ስጋት እንዳትሆን እርስ በርስ መነጋገር እና በክልሉ ብሔራዊ ዕርቅ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።