18 ከፍተኛ የትግራይ አመራሮችን ጨምሮ በዘር ማጥፋት ወንጀል 64 ሰዎች ተከሰሱ!
ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ 18 ከፍተኛ የትግራይ የፖለቲካ እና የጦር መሪዎች በፌደራል መንግስት በተሾሙ 64 የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም ድረስ በነበረው የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለጠቅላይ የምርመራ መምሪያ የቀረበው የጽሁፍ ክስ እንዳመለከተው የተጠቀሱት ተከሳሾች በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል።
ክሱ የቀረበው በአቶ አበራ ንጉስ የተባሉ የህግ ምሁር እና ጠበቃ እንዲሁም ከጥቅምት እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ግለሰብ ናቸው።
የክስ ጥቆማ ከቀረበባቸው መካከል፦
– ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)
– አቶ ጌታቸው አሰፋ
– አቶ ጌታቸው ረዳ ካሕሳይ
– ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ሄር
– ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ
– ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ ይገኙበታል።
ለኢፌደሪ ፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን፣ ለወንጀል ምርመራ የጠቅላይ መመሪያ የቀረበውና የተመለከትነው፣ የክስ ጥቆማ ፅሑፍ የተጠቀሱት የፓለቲካና የሰራዊት አመራርሮች የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 269 (ሀ)፣ (ለ) በመተላለፍ በ63 ሰዎች ግድያና በአንድ ሰው የግድያ የሙከራ በማካሄድ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸማቸውን ያትታል።
የክስ ጥቆማ የቀረበባቸው ግለሰቦች በትግራዩ ጦርነት ከጥቅምት እስከ ሰኔ 2013 ዓ/ም ትግራይን ለማስተዳደር በፌደራል መንግስት ውሳኔና በደንብ ቁጥር 479 /2013 ዓ/ም መሰረት ተቋቁሞ በነበረው የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ላይ የወንጀል ድርጊቱ መፈጸማቸውንም ያብራራል።
የክሱ ጥቆማ ፣ የ18ቱን ተከሳሾች፣ የ63 ሟቾችና የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው የተባሉትን አመራሮችና ሠራተኞቾ ስም ዝርዝም በግልጽ አካቷል።


ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter