በሌላ በኩል አስረግጠን የምናስቀምጠውና የሀገራችን ህዝቦችም ከዚሁ አንጻር ግልጽ አሰላለፍ እንዲመሠርቱበት የምንሻው ሻዕቢያን በተመለከተ የሰጠነው ምዘና እና ብይን ትክክለኛነት ሲሆን አሁንም በተከታታይ ይሄ እውነታ ይበልጥ እየተረጋገጠ እንደመጣ ተመልክተናል።
አብን ከሻዕቢያ ጋር በተገናኘ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ በግንባር ቀደም አውግዘውን የተሰለፉት ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ ባለሟሎቹ መሆናቸው አስገራሚ ነበር። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሚወሰነው በኢትዮጵያውያን አንድነትና ጥንካሬ እንጂ በሻዕቢያ ይሁንታ ሊሆን እንደማይችል በድጋሜ አስምረን ማስቀመጥ እንሻለን።
ሻዕቢያ በሌሎች የውጭ ሃይሎች በኢትዩጵያ ላይ በጠላትነት የተመለመለ በመጀመሪያ ረድፍ የሚገኝ ባንዳ ድርጅት መሆኑ ሁሌም ቢሆን መታወቅ አለበት። ይህም ሆኖ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥያለሁ ካለ በኋላ ጭምር ኢትዮጵያ ላይ እንደ አልቀት ተጣብቆ መኖር የሚፈልግ ሃይል ነው። ሻዕቢያ “የኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የኤርትራም ነው፣ የኤርትራ የሆነው ግን የኤርትራ ብቻ ነው” የሚል ግብዝ እና ስግብግብ ድርጅት መሆኑም ግልጽ ነው። ዋናው ችግር የሚመጨውም ከዚህ ስግብግብነቱ ነው። ሻዕቢያ ለኤርትራ ከስያሜ ውጭ እንደ ሀገር ፍላጎቱን እና ግዴታውን ለይቶ እንዲቆም አላደረገውም።
ለበርካታ አስርተአመታት ሳያቋርጡ የጦርነት ትርኢት በማሳየት ብቻ ህዝብን በድህነት መግዛት እንደሚቻል ያሳየ ምሳሌ ድርጅት ቢኖር ሻዕቢያ ብቻ ነው። ስለሆነም “የኤርትራ ነፃነት” የሚባለው ጉዳይ በተግባር ሲፈተሽ ቧልትና ይህቁንም ለጭቁን የኤርትራ ህዝቦች የባርነት፣ የስደት፣ የድህነትና የእልቂት ምዕራፍን የከፈተ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም ሆኖ በኤርትራ ህዝቦች በኩል የግድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አለ።
ስለኤርትራ ሉዓላዊነት አበክረው ሲናገሩ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትም መከበር እንዳለበት ማወቅ አለባቸው። የኢትዩጵያን ሉአላዊነትና አንድነት እየጣሱ ስለኤርትራ ሰላምና ሉዓላዊነት ማሰብ ፈፅሞ አይቻልም። ሰሞኑን የሻዕቢያው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጭምር በመግባት ለሰጡት ሸፍጠኛ አስተያየት ከይዘት አንፃር ምላሽ መስጠት ጠቃሚ ላይሆን ይችላል።
በብዝሃ-ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነት ያለ እና የሚኖር ሀቅ ቢሆንም የሻዕቢያው መሪ የኢትዮጵያን ህዝብ ሴም እና ኩሽ ብሎ በመክፈል እርቃን በወጣ አኳኋን በሀገራችን ላይ ቋሚ ጠላትነትን ያወጀበት፣ እንዲሁም ላለፉት 80 አመታት የኢትዮጵያን መንግስታት ተላለኪ በሚል የገለፀበት የሸፍጥ ንግግር ሲሆን፤ ይልቁንም ሻዕቢያ ራሱን በቅጡ መፈተሽ ባለመቻሉ እድሜ ልኩን የጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ተላላኪ በመሆን የተሰለፈና ለዚህም ቀለብ የሚሰፈርለት በመሆኑ ከ”ነጽናት” በኋላ 34 አመታትን ተጉዞም ቢሆን ዛሬም ድረስ የአንድ ሀገርና መንግስት መሠረታዊ መገለጫ የሆኑ ተቋማትንና ስርዓትን መገንባት ያልቻለ በሽፍታነት የቀረ ድርጅት ነው።
ስለሆነም ሻዕቢያ በተለይም በመሪው በኩል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት በህዝቦች መካከል ከፍተኛ የጥላቻ አንድምታ ያለው አጀንዳን በአደባባይ የማስተጋባት መብት የለውም የሚለው ጭብጥ ሊሰመርበት ይገባል። ለዛም ነው በመገንጠልና በፍች መካከል ያለውን ልዩነት በውል ሳይገነዘቡ የገቡበት ሻዕቢያወች አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ተጣብቀው መቀጠል የሚፈልጉት። ተገንጥያለሁ ከተባለ በኋላ አሁንም “በእናቴ ቤት” የሚባል ክርክር አይሰራም። ቢያንስ ከዚህ በኋላ ይህ አስተሳሰብና አሰራር ወጥ በሆነ መልኩ ታሳቢ እና ተግባራዊ እንዲደረግ ለመላው ኢትዮጵያውያን ለማስታወስ እንወዳለን።
በሌላ በኩል ይሄንኑ የሻእቢያ ጥሪ ተከትለው በባንዳነት ለመቀጠር የሚራኮቱ ግለሰቦች እና ስብስቦች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ለማሳሰብ እንወዳለን።
የሻዕቢያ ስነ ልቦና ምንጩ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ታሪካዊ ጠላቶች ከነበሩ የውጭ ሃይሎች ስለሆነ በስትራቴጂ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ በተሻለ ሁኔታ የሚመለከተው የህዝብ ክፍል የለም።
በተያያዘ መልኩ በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና መሰረታዊ ጥቅሞች ላይ ቀና መንፈስ የሌለው መሆኑን በተደጋጋሚና በግልፅ አሳውቋል። በተለይ ሀጋራችን ኢትዮጵያ በመልክዓ-ምድር በታሪክ እና በህግ ያላትን የባህር በር የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት እና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተቀናጀ ትግል ማድረጉን እንደሚቀጥል በድጋሜ ማሳወቅ እንወዳለን።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ምአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ