ዓለም ፊቱን አዞረባት ልጆቿ ግን በስስት ተመለከቷት፣ ዓለም ዘመተባት ልጆቿ ግን ለክብሯ ዘመቱላት፣ ዓለም አዋከባት ልጆቿ ግን አረጋጓት፣ ዓለም አደማት ልጆቿ ግን አከሟት፣ ዓለም ገፋት ልጆቿ ግን ደገፏት፣ ዓለም በጠላትነት ተነሳባት ልጆቿ ግን በፍቅር ቆሙላት፣ ጠላቶቿ ነጻነቷን ሊወስዱባት ወጓት፤ ልጆቿ ግን የወጓትን ወጉላት፣ የነኳትን አዋረዱላት፣ በእብሪት የመጡትን አንበረከኩላት፤ ነጻነቷን ጠበቁላት፣ በጽናት አጸኗት፣ በጀግንነት ጠበቋት፡፡
እልፍ አእላፍ ጦር ተሹሎባታል፣ እልፍ አእላፍ ሰይፍ ተስሎባታል፣ እልፍ አእላፍ ጉድጓድ ተቆፍሮባታል፤ በዙሪያዋ እሳት ይዘው አንዣብበውባታል፤ እርሷ ግን የተሾሉትን ጦሮች ሰበረቻቸው፣ የተሳሉትን ሰይፎች መከተቻቸው፣ በተቆፈሩት ጉድጓዶች ቆፋሪዎችን አስገባቻቸው፣ እሳት ይዘው የዞሩትን በራሳቸው እሳት ገረፈቻቸው፡፡
እርሷ መከራ የማይበግራቸው፤ ችግር የማያንበረክካቸው፤ ጠላት ድል የማይነሳቸው ልጆች አሏት፡፡ ደማቸውን አፍስሰው የሚጠብቋት፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የሚያጸኗት፣ ቀድመው የሚያስቀድሟት፣ ወድቀው የሚያቆሟት፣ ሞተው የሚያኖሯት፣ አፈር ለብሰው የሚያስከብሯት፣ ስሟን በዓለሙ ፊት ሁሉ ከፍ አድርገው የሚያስጠሯት ጀግና ልጆች አሏት፡፡
እንኳን ልጆቿ ተራራና ሜዳዎቿ፣ ሸለቆና ሸንተረሮቿ ፣ ወንዝና ምንጮቿ፣ ዋሻና አምባዎቿ ሳይቀሩ ለነጻነቷ ይቆማሉ፡፡ ለክብሯ ይሰለፋሉ፡፡ ክብሯን ሊደፍር የመጣውን አላላውስም አላራምድም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን የጠበቃት አንድነት፣ ጽናት፣ ጀግንነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ ድፍረት፣ ለነጻነት እና ለሀገር ፍቅር ያለ ቀናዒነት ነው፡፡
ብዙዎች በጠላቶቻቸው እየተነጠቁ ሀገር አልባ ኾነዋል፡፡ ነጻነታቸውን ተነጥቀው እንደ እቃ ተሽጠዋል፤ በሀገራቸው ባይታዋር ኾነዋል፡፡ ባለ እርስት ኾነው ሳለ ምንም እንደሌላቸው ተገፍተዋል፡፡ ተዳፍተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ አይሞከርም፡፡ ይህ አይታሰብም፡፡ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት የሚሠለጥን ጠላት አይገኝም፡፡ አልነበረም፣ የለም፤ አይኖርም፡፡ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያዊነት እና ነጻነት ብቻ ነውና፡፡
ኢትዮጵያ ጠላት የሚቀጣባት፣ ባንዳ እና ባዳ የማይሰነብትባት፣ ድል ማድረግ እንጂ መሸነፍ የማይታወቅባት፣ አንድነት የደረጀባት፣ የሀገር ፍቅር የጸናባት፣ የነጻነት ጮራ የማትጠልቅባት የጽኑዎች ሀገር ናት፡፡ ጠላቶች ትናንት አላሸነፏትም፡፡ ዛሬም አያሸንፏትም፡፡ ነገም አይረቷትም፡፡ እርሷ በቃል ኪዳን ውርስ አያት ቅድመ አያቶች የጠበቋት፤ አባት ተቀብሎ ያስከበራት፡፡ ልጅም ቃል ኪዷኑን ሳያዛንፍ የሚጠብቃት የቃል ኪዳን እና የመታመን ሀገር ናት፡፡
ቅኝ ገዢዎች ሠራዊት በበዛላቸው፡፡ ኃይል በደረጀላቸው ዘመን ብዙዎችን በኃይላቸው እያስገበሩ ቅኝ ገዝተዋል፡፡ ከሀገራቸው እየተሻገሩ የሌላ ሀገር ወርረዋል፡፡ ቅኝ ተገዢዎችም በቀኝ ገዢዎች አያሌ የመከራ ጽዋዎችን ተጎንጭተዋል፡፡ በመከራ ዶፍ ተደብድበዋል፡፡ ባሕል እና እሴታቸውን፣ ታሪክና ሃይማኖታቸውን፣ ቋንቋ እና ታሪካቸውን ሁሉ ተነጥቀዋል፡፡ ወድደው ሳይኾን ተገድደው የባዕድ ባሕል እና እሴት፣ ታሪክ እና ሃይማኖት፣ ቋንቋ እና ማንነት ተቀብለዋል፡፡
ቅኝ ገዢዎች በሌሎች ሀገራት የተቀዳጁትን ድል በኢትዮጵያ ላይም እናሳካለን መስሏቸው ሞክረዋል፡፡ ቅኝ ለመግዛት ተደጋጋሚ ሞክረዋል፡፡ ዳሩ አልተሳካላቸውም፡፡ ድል እየኾኑ እና እየተዋረዱ ተመለሱ እንጂ፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ተደጋጋሚ ሞክራለች፡፡ ተደጋጋሚም ተሸንፋለች፡፡ ተዋርዳለች፡፡ በዓለም አደባባይ መሳቂያ መሳለቂያ እስክትኾን ድረስ በኢትዮጵያ ተደቁሳለች፡፡
ከዓድዋ ቀድሞ ደጋግማ ሞክራ ተሸንፋለች፡፡ በዓድዋ ጊዜም ተሰባብራለች፡፡ ከዓድዋ በኋላም ለበቀል ዳግም መጥታለች፡፡ በሁሉም ግን ተሸንፋለች፡፡ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለመንበርከክ ተገድዳለች፡፡ ኢትዮጵያ እያንበረከከች፣ ጣልያን እየተንበረከከች ዓመታት አልፈዋል፡፡ ዘመናት ነጉደዋል፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ የተንበረከከችው ጣልያን ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ ከቅርብም ከሩቅም ያሉ ጠላቶችን አንበርክካለች እንጂ፡፡
በዓድዋ ድል ኾና የተመለሰችው ጣልያን ከ40 ዘመን በኋላ ዳግም ተመልሳ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን በሰማይ በምድር፣ በባሕር ሳይቀር አያሌ ሠራዊት አስጭና፣ እሳት እና መርዝ የሚተፋ መሳሪያ ይዛ ነበር የመጣችው፡፡ መርዙንም በጭካኔ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ አረከፍክፋለች፡፡ እሳት በሰማይ አዝንባለች፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ግን በእሳት እና በመርዝ ተረማምደው ድል አደረጉ፡፡
የሀገር ፍቅርን ስንቃቸው፤ የሠንደቅ ዓላማ ክብርን ትጥቃቸው አድርገው በረሃ የወረዱ አርበኞች እሳቱንም፣ መርዙንም፣ አረሩንም፣ ረሃቡንም፣ ጥሙንም፣ እሾህና አሜካላውንም ችለው ነጻነታቸውን አስከብሩ፡፡ የሀገራቸውን ዳር ድንበር አስጠበቁ፡፡
ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 ዓ.ም በተሰኘው መጽሐፋቸው ጣልያኖች በአፍሪካ በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ላይ ድል ከኾኑ በኋላ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደ መግታት አድርገውት ነበር፡፡ ለቅኝ ግዛት የተመደበው በጀትም በግማሽ ቀንሷል፡፡ የጸረ ቅኝ ገዥዎች ቡድንም ጣልያን ከእነ አካቴው የአፍሪካን ምድር ለቅቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ፡፡ ጣልያንም ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ቀጠለች ብለው ጽፈዋል፡፡
ነገር ግን በልቧ ቂሟን አልሻረችም፡፡ መሸነፏን አልረሳችም ነበር፡፡ ላይ ላዩ ፍቅር ውስጡ ውስጡ ጠብና ከጀርባ የሚሸረብ ሸር ነበረው፡፡ በሙሶሊኒ የሚመሩት ፋሽስቶች ሥልጣን መያዝ የጣልያንን ቅኝ ግዛታዊ ምኞት ጥንካሬ ሠጠው፡፡ የጥንቱን የሮማን መንግሥት ኃይል እና ዝና እንደገና ለማደስ ታጥቆ የተነሳው የፋሽስት ቡድን የመጀመሪያው ዓላማው የዓድዋን ሀፍረት መሻር ነበር፡፡ ነገር ግን ይሄን አላማቸውን ገሃድ አላወጡትም ነበር፡፡ ውስጥ ውስጡን ይሠሩ ነበር እንጂ፡፡
ዓመታት እየተነባበሩ ቀጠሉ፡፡ ጣልያኖችም ቀስ በቀስ የደበቁትን ገለጡ፡፡ በኢትዮጵያ ላይም የወረራ ጦርነት ጀመሩ፡፡ በኢትዮጵያውያን ላይ የመርዝ ቦንብ ጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያንም በጀግንነት ስለ ሀገራቸው ነጻነት ተፋለሙ፡፡ ጣልያኖች የጎደፈ ስማቸውን ለማደስ ኢትዮጵያውያን የአባቶቻቸውን ገድል ለመድገም፣ አንዳንዶቹም በዓድዋ ላይ ዘምተው ነበርና ዳግም ድል ለማምጣት ነበር የሚዋጉት፡፡ ዱር ቤቴ ያሉ አርበኞች በዱር በገደሉ እየተዘዋወሩ፡፡ ረሃብና ጥሙን ችለው የወራሪውን ጦር መውጫ መግቢያ አሳጡት፡፡ ቁም ስቀሉን አሳዩት፡፡
ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች አዲስ የጦር መላ ፈጥረው፣ አዲስ የጦር ስልት ቀይሰው፣ ሀገራቸውን ከጥፋት ወገኖቻቸውን ከእልቂትና ከባርነት ለማዳን ተነሳሱ፡፡ ጠላትን በመግደል ለሀገር ሞቱ፡፡ እነዚህም አርበኞች ናቸው፡፡ አርበኝነት ማለት ለሀገር ለወገን ሲሉ ከውጭ ጠላት ጋር መጋደል ማለት ነው ብለው ጽፈዋል፡፡
እነዚህ ለሀገር የቆሙ አርበኞችም ለነጻነት ሲሉ ተዋደቁ፡፡ ያለ እረፍት ተዋጉ፡፡ የአርበኞች ዓላማ አንድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ነጻ መውጣት፡፡ ስለ ሀገራቸው በአንድነት ጸንተው፣ በአንድነት ዘምተው፣ በአንድነት ተዋግተው፣ በአንድነት መክተው እና ወግተው ድል አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያን ነጻነት እና አንድነት አስከበሩ፡፡ የሀገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለበለቡ፡፡ እነርሱን ያስነሳቸው የሀገር ፍቅር ነው፡፡ ያጸናቸውም የሀገር ፍቅር ነው፡፡ የድል ምንጫቸውም የሀገር ፍቅር እና አንድነት ነው፡፡ ከአንድነት ጋር ድል አለች፡፡ ከአንድነት ጋር ነጻነት አለች፡፡ ከአንድነት ጋር መከበር እና መፈራት አለችና፡፡ ኢትዮጵያውያንም በአንድነታቸው ተፈሩ፤ በአንድነታቸው ተከበሩ፤ በአንድነታቸው ነጻነታቸውን አስከበሩ፤ ራሳቸው ኮርተው ሀገር እና ትውልድ አኮሩ፡፡
መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው ከአይበገሬ ታሪከኛ ጥንታዊ ሀገሮች መካከል የእኛዋ ኢትዮጵያ አንዷ ናት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ የአርበኝነት ተጋድሎዋ በነጻነት መኖር ብቻ ሳይኾን በዓለም የታፈረች እና የተከበረች ናት፡፡ ከጥንታዊዎቹ ኃያላን ግሪኮች፣ ከሮማውያን ምኞት እና ሙከራ ሌላ በየጊዜው ኃይል የተሰማቸው፣ የቅኝ ግዛት ምኞት ያሰከራቸው ወራሪዎች እና ተስፋፊ ጠላቶቿ ዒላማ አድርገዋታል፡፡ ነገር ግን ሁሉም እየተቀጡ ተመልሰዋል ብለው ጽፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች አይበገሬ የአርበኝነት ተጋድሎ ገድል የሚያስረዳን አንድነት ኃይል መኾኑን አንድነት ታላቅነት መኾኑን፣ የዚህች ጥንታዊት አይበገሬ ነጻና አኩሪ ሀገር ባለቤት ለመኾን የቻልነው በአንድነታችን እና በኅብረታችን ነው፡፡ ሀገራችን ከተቆረቆረችበት ጀምሮ የየዘመኑ ተከታታይ ትውልዶች በፈረቃና ባላቋረጠ መራር መስዋዕትነት ያቆዩንን ሀገር እና ያወረሱንን የታሪክ ቅርስ እኛም በፈንታችን ለተከታዩ ትውልድ እናወርሳለን ወይስ እናፈርሳለን ብሎ የዛሬው ትውልድ ራሱን መጠየቅ አለበት ነው የሚሉት፡፡
መንግሥቱ ኃይለማርያም ሲጽፉ የትናንት ጸረ ፋሽስት አርበኞቻችን የታገሉት እንደ ጥንቱ ተመሳሳይ መሳሪያ ታጥቆ ከመጣ ጠላት ጋር በክንድ መሣሪያ ሳይኾን በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ ከማይታወቅ እጅግ ከተራቀቀ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ጋር በዓለም ሕግ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ ዝናብ እየዘነበባቸው ነበር፡፡ የጸረ ፋሽስት አርበኞቻችን እና ጀግንነት ልዩ እና ተደናቂ የሚያደርገው ለትግል የተሰማሩት በማንም አሳሳቢነት፣ ቀስቃሽነት ወይንም ትዕዛዝ ሳይኾን በእያንዳንዳቸው ተነሳሽነት ነው እንጂ ብለዋል፡፡
የዘመቱት ለሹመት እና ለሽልማት አይደለም፡፡ ለሀብትም አልነበረም፡፡ ለሀገር ለመስዋዕትነት ነው እንጂ፡፡ የዚያ አካባቢ ነው የዚያ ጎሳ ነው ሳይባባሉ በአንድነት ተደራጅተው ለአንዲት ኢትዮጵያ ነጻነት እና ሉዓላዊነት ተፋለሙ፡፡ በአንድነትም የነጻነት ክብርን ለሀገር እና ለትውልድ ሸለሙ፡፡ እነርሱም በደምና በአጥንት የረቀቀ ነጻነትን ተሸለሙ፡፡ ነጻነት የሸለሙት፤ የከበረች ሀገር ያስከበሩት ጀግኖች አርበኞችም በሚያዚያ 27 ቀን ከፍ ብለው ይከበራሉ፡፡ ስማቸው እየተጠራ ይዘከራሉ፡፡ ይወደሳሉ ይሞገሳሉ፡፡ ስለ ምን ቢሉ እነርሱ ስለ ሀገር ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ነፍሳቸውን አሳልፈው ሀገራቸውን አኑረዋልና፡፡
እነኾ እነዚህ ጀግኖች ቃል ኪዳን አኑረዋል፡፡ ትውልድ ሁሉ በአንድነት እንዲኖር፣ ለሀገሩ በፍቅር እንዲያብር፣ ዳን ድንበሯን እንዲያስከብር፣ ለሀገር ሲባል ቂም እና በቀልን እንዲሽር፡፡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትን አጽኑ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እንደ ቀደሙት አርበኞች ሁሉ በጀግንነት ጽኑ፡፡ መከፋፈልን አስወግዱ፡፡ አርበኝነትን ለማክበር፣ አርበኞችንም ለመዘከር ቅድሚያ የሀገር ፍቅር፣ የአንድነት መንፈስ ያስፈልጋልና፡፡ ዘረኝነትን ያሰበች ልብ አርበኝነትን ልታስብ አትችልምና፡፡
በደም ማሕተም ያጸኑትን ነጻነት፣ በአጥንታቸው ክስካሽ ያበረቱትን አንድነት፣ በፍጹም የሀገር ፍቅር ያደመቁትን ኢትዮጵያዊነት ጠብቁ፤ አስጠብቁ፡፡ ያን ጊዜ የአባቶቻቸው ልጆች ትባላላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ በጀግንነት የተጠበቀች፣ በመስዋዕትነት የጸናች ናትና በጀግንነት ጠብቋት፡፡ በመስዋዕትነት አጽኗት፡፡
በታርቆ ክንዴ አሚኮ ዲጂታል