የፍልስጥኤማዉያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ የምግብ ማከማቻ መጋዘኖች እና የህዝብ መገልገያ ማዕድ ቤቶች ላይ ዘረፋ ፈጽመዋል ያላቸውን የታጠቁ ወሮ በሎች መግደሉን ለቡድን ቅርበት ያላቸውን የመረጃ ምንጮች ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሃማስ ባለስልጣናት በትጥቅ ታግዞ ዘረፋ ይፈጽማል ያሉት ቡድን ከእስራኤል ጋር በመተባበር ይከሱታል። እስራኤል ግን ስለቀረበባት ክስ ያለችው ነገር የለም ።
አንድ የሃማስ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ” ሁሉንም ከሃዲዎች አሳደን እንመታቸዋለን “ብሏል።
ሚኒስቴሩ አያይዞም ” አስፈላጊ ነው የምንለውን ሁሉ ርምጃ እንወስዳለን ፤ በዚህ መልኩ እያሸበሩ እንዲቀጥሉም አንፈቅድም ” ብሏል።
ኢስማኤል አል ታዋብታ የተባሉ በሃማስ የሚመራ መንግስት ዳይሬክተር እንደሚሉት ወሮ በላ ያሏቸው ቡድኖች “ጎሳን መሠረት አድርጎ” የተደራጁ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከእስራኤል መንግስት የቀጥታ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው እምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት ።
ይህንኑ ተከትሎ በዘረፋ ተግባሩ ላይ መሰማራታቸው በተረጋገጠባቸው የዘራፊ ቡድኖቹ አባላት ላይ “አብዮታዊ ” የተባለ ርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
ሃማስ በጋዛ ሰርጥ እየተባባሰ የመጣዉን “የወሮበሎች ዘረፋ ” ለመቆጣጠር የሰዓት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀመጡም ተሰምቷል።
ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለመያዝም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኋላ ሰዎች እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አግዷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ወንጀለኞችን ዒላማ አድርጋ በሰነዘረችው የድሮን ጥቃት አንድ የፖሊስ መኮንን መገደሉን እና ሌሎች መቁሰላቸውን አንድ የሃማስ ባለስልጣን ተናግረዋል።
እስራኤል ከሃማስ ጋር የደረሰችው የተኩስ አቁም ስምምነት ከተናደ በኋላ ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ሰርጡ ይገባ የነበረ የሰብአዊ ርዳታ ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አድርጋለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው በጋዛ ሰርጥ እስራኤል የሰብአዊ ርዳታ እንዳይገባ ማገዷን ተከትሎ የሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰ መጥቷል።
እስራኤል በበኩሏ ወደ ሰርጡ የሚገባውን የሰብአዊ ርዳታ ሃማስ እየሰረቀ ለአባላቱ ያከፋፍላል ስትል ትከሳለች። ሃማስ በበኩሉ በእስራኤል የሚቀርብበትን ክስ አይቀበልም ። Via Dw