ተከሳሾቹ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበው በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት እንደየተሳትፏቸው የቀረበባቸው ክስ ተነቦላቸዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ ክስ የመሰረተባቸው ግለሰቦች በአሜሪካና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ መዓዛ መሐመድ፤ ተስፋዬ ወልደሰላሴ፣ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን ኃ.የተ.የግ/ማህበር፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ አመራሮችና ብርቱካን ተመስገንን ጨምሮ 16 ግለሰቦች ናቸው።
ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ) እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3/1/ለ/ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሳሾች ለጊዜው በቁጥጥር ስር ካልዋሉ ሌሎች ግብራበሮቻቸው ጋር በመሆን የፖለቲካ ዓላማን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ በህገ መንግስት የተቋቋመውን የፌደራልና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በኃይል በማስወገድ ስልጣን ለመያዝ፤ ይህ ካልተሳካ ደግሞ መንግስትን በሀይል በማስገደድ ለድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ የሚል ዓላማን በመያዝ መንቀሳቀሳቸው በክሱ ተመላክቷል።
ተከሳሾቹ ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት በአማራ ክልል በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እንዲደርስባቸዉ በማድረግ በአፀፋዉ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች አደጋ እንዲያደርሱ በማድረግ የህዝቡን ሕይወትና ንብረት ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ በሀገሪቷ ውስጥ ከፍተኛ ትርምስ ለመፍጠር ማሴራቸውም ተብራርቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ በላይነት እንዳይኖርና መጨረሻ የሌለው ከፍተኛ የሰው ሕይወት እልቂት እንዲከሰት በማድረግ መንግስት ሀገሪቷን ተረጋግቶ እንዳያስተዳድር፣ የሀገሪቷን አንድነትና ሉዓላዊነት እንዳያስጠብቅ፣ የዜጎችን በሰላም የመኖር መብትን እንዳያስከብር፣ ለሰዉ ሕይወትና ንብረት ደህንነት ዋስትና እንዳይሆን በማድረግ አጋጣሚውን በመጠቀም ተከሳሾቹ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ሆነዉ በመናበብ የተመደቡበትን የስራ ኃላፊነትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር 2017 ዓ.ም ድረስ መንቀሳቀሳቸውን ክሱ ያሳያል።
የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማዘጋጀትና ለ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን ያስጠኑትን ሀሰተኛ ታሪክ እውነተኛ ታሪክ አስመስሎ በመቅረጽና በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላሉ ዜጎች እንዲደርስ በማድረግ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ማድረጋቸው ነው አቃቤ ህግ በክሱ ያስረዳው።
በዋናነትም 6ኛ ተከሳሽ በደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ተጠልፋ እንደተደፈረች በማሰመሰል፤ ሀሰተኛ መታወቂያን ጨምሮ የገንዘብ ድጋፍና እቅድ አውጥቶ በመስጠትና በመተግባር በመሳተፋቸው ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሁለተኛው ክስ ከ7ኛ እስከ 11ኛ ተከሳሾች ባሉ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፥ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና (ለ)፣ 34፣ 43 (3)፣ 46 እና የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4፣ 5 እና 7/4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
7ኛ ተከሳሽ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን ኃ.የተ.የግ/ማህበር እና 8ኛ ተከሳሽ ሲልቨር ስፕሪንግ ፕሮዳክሽንና ፕሮሞሽን ኃ.የተ.የግ.ማህበር (የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን የእህት ኩባንያ) ሆኖ የ6ኛ ተከሳሽ ታሪክ የተላለፈበትን ፕሮግራም የሚመራ፣ 9ኛ ተከሳሽ ማክዳ ፍስሓጽዮን /ማክዳ አሰፋ/ የሲልቨር ስፕሪንግ ፕሮዳክሽንና ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅና የኢ.ቢ.ኤስ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ሃላፊ፣ 10ኛ ተከሳሽ ታሪኩ ሀይሌ ረታ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዳይሬክተር፣ 11ኛ ተከሳሽ ህሊና ታረቀኝ አረጋ በኢ.ቢኤስ ቴሌቭዥን የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ረዳት ናቸው፡፡
በተለይም 9ኛ ተከሳሽ የ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን ታሪክ እውነተኝቱና ትክክለኛነቱ የሚያጠራጥር ነው፤ የዩኒቨርስቲው ስም ባይጠቀስም ባለፉት ዓመታት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ታገትው ጠፉ ከተባሉት ጋር የሚገናኝ ታሪክ ስለሚመስል አሁን የተቀረፀው ፕሮግራም ከተሰራጨ በኋላ ሰዎች የሚረዱት የጠፉት ተማሪዎች እጣ ፋንታ ሞተዋል ማለት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያስደርስ ሊሆን ስለሚችልና ይህ ታሪክ ከተሰራጨ ሁከትና ብጥብጥን አስነስተዉ የሰውን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑና ታሪኳ ልክ ባለመሆኑ ኢክስኪውቲቭ ፕሮዲውሰር ዉሳኔ እንዲሰጡበት እንጠይቃለን የሚል አስተያየት የ7ኛ ተከሳሽ (ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን ኃ.የተ.የግ/ማህበር) የሕግ ክፍል ቢያቀርብላትም አስተያየቱንና የስራ ኃላፊነቷን ወደ ጎን በመተው ትክክለኛ ያልሆነ የተቀነባበረ ታሪክ በቀን 14/7/2017 ዓ.ም በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን አዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ለብዙ ሕዝብ እንዲደርስ ያደረገች በመሆኑ ክሱ ተመስርቶባታል።
10ኛ ተከሳሽ ታሪኩ ሀይሌ ረታ የአዲስ ምዕራፍ ፕሮግራም ዳይሬክተርና 11ኛ ተከሳሽ ህሊና ታረቀኝ ረዳት ዳይሬክተርነት የ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን በአካል ያገኟት በመሆኑ ታሪክ ውስጥ ብዙ የሚያጠራጥሩ እውነት የማይመስሉ ንግግሮች እያሉ፣ በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ እየቻሉ ባለማድረግ ግብረአበር በመሆን በፈፀሙት የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀል ተከስሰዋል፡፡
3ኛው ክስ በ3ኛ፣ በ6ኛ እና ከ12ኛ እስከ 16ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) እና (ለ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9(2) በመተላለፍ ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በመላ ሃሳባቸው፣ በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን የማይገባ ጥቅም ለ6ኛ ተከሳሽ ብርቱካን ተመስገን ለማስገኘት አስበዉ የተሰጣቸዉን ስልጣንና ኃላፊነት በግድፈት ያለአግባብ በመገልገል ሀሰተኛ የነዋሪ መታወቂያ እንዲሰጣት በማድረግ፤ እውነተኝነቱ ሳይረጋገጥ በአስገድዶ መደፈር ምክንያት ለልብ ሕመም በሽታ እንደተዳረገች፣ የኢኮኖሚ አቅምና ቤተሰብ እንደሌላትና እገዛ እንደምትፈልግ እንድትገልጽ ድጋፍ በማድረግ የማይገባትን ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሰማኒያ ሁለት ብር በመጋቢት ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም ከተለያዩ ግለሰቦች ወደ የባንክ ሂሳብ ቁጥሯ እንዲገባላት ሁኔታ ያመቻቹ መሆናቸው በክሱ ተዘርዝሯል።
በዚህም ተከሳኞቹ በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የነበሩ አራት ግለሰቦች በዋስትና እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት የግራነና ቀኙን ክርክር ለመስማት ለግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሲፈን መኮንን
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter