ሀሳብ ባረጠበት ቀዬ፣ ትምህርት እና መዝናናት ቄንጥ በሆኑበት ጊዜ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ላይ ማላገጥ አግባብ አይደለም…
እንዲህ ያለ ብሔራዊ ማላገጥን የሥነ-ምግባር ኮድ አውጥቶ የሚቆጣጠር እና የሚመራ አካል ሊኖር ይገባ ነበር፤ የጋዜጠኝነት እና የቲያትር ሞያ በዚህ ልክ ሊደፈር እና ሊዋረድ አይገባውም፤ እኛ ተመልካቾችም መሸነጋገሉን ትተን እንዲህ ያለውን ሥራ ማውገዝ አለብን፤ የሚበጀውን እንምረጥ…
“የሚዲያ ባሕላችን ትልቅ ጉድባ ውስጥ ከትቶናል”
(ዮናስ ታምሩ ገብሬ)
የሚዲያ ባሕላችን ትልቅ ጉድባ ውስጥ ከትቶናል፤ ማሰብ እንዳንችል፣ ለአዳዲስ ሀሳቦች ዝግጁ እንዳንሆን፣ በመዝናኛ ፕሮግራም ሰበብ ከወግና ባሕላችን እንድናፈነግጥ፣ ለፈጠራ ዝግጁ እንዳንሆን፣ እንዳንማር እና እንዳንገነዘብ እየሆንን ነው…
…አስከፊ ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል፤ ሚዲያዎቻችን በማዝናናት ሰበብ እያሰነፉን እንደሆነ ግልጽ ነው፤ የትውልድን ንቃተ-ሕሊና ለመደጎም፣ ብሎም ለማስተማርና ለማሳወቅ ትምህርት፣ ሐይማኖት፣ ፖለቲካ እና ሚዲያ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አይካድም።
አንድ የመዝናኛ ፕሮግራም ቢያስተምር አይከፋም፣ የግድ ማስተማር ብቻ የለበትም፤ ነገር ግን የመዝናኛ ፕሮግራም ፈጠራ የታከለበት፣ አዲስ ነገርን የሚያሳይ፣ ጥበብን በውስጡ መያዝ ያለበት…ወዘተ. መሆን አለበት፤ አድማጭ ተመልካች ጊዜውን እና ሰዓቱን ሰውቶ መስማት መመልከቱ ልብ ይባልልኝ፤ አንድም ሊዝናና ወይም ሊማር የተለመ አድማጭ ወይም ተመልካች ትልሙን ለነፋስ እና ለጂኒ ጃንካ አስረክቦ ማረፍ የለበትም…
…በሚዲያ ብቅ ብሎ ፕሮግራም የሚያሰራጭ ጋዜጠኛ ወይም የቲያትር ባለሞያ ኃላፊነት የጎደለው ፕሮግራም ማሰራጨት የለበትም፤ ማዝናናትም ልክ አለው፤ ማስተማርም ልክ አለው፤ ለምሳሌ የመዝናኛ ፕሮግራም ወጥ እና ዳጣ የሚልሱ ተወዳዳሪዎችን ሊያሳየን ይገባል ብዬ አላምንም፤ ወጥ ማስላስ ምኑ ላይ ነው ፈጠራው? ይኼ ምኑ ያዝናናል? በዚህ የሚዝናኑ ሰዎችስ ጤናቸው መፈተሽ የለበትም?…
…በጣም የሚከነክነኝ ነጻነት ወርቅነህን የመሰለ ቲያትረኛ፣ በካራክተር አክተር የሚስተካከል የሌለው፣ መድረክ ሲመራ ኢንፕሩቫይዜሽን የገባው ድንቅ ሰው ‹‹የቤተሰብ ጨዋታ›› በሚል ቤተሰባዊ ጨዋታን የሻረ አጓጉል ፕሮግራም ሲያቀርብ ሳይ፣ እኛና ሞያችን መሳ ለመሳ እየተጓዝን እንደሆነ ይሰማኛል፤ የቲያትር ባለሞያ ነው እንደውም መድረክን ቀጥ አድርጎ፣ ፈጠራ አክሎ፣ በሚያዝናና መልኩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ማቅረብ የነበረበት፤ ግን አልሆነም፤ የግል ዕይታዬ ቢሆንም የሚያዝናና እንዳልሆነ ግልጽ ነው…
ደረጄ ኃይሌን የመሰለ የሀሳብ ሰው ከቴሌቪዥን መስኮት ያወረድነው ሀሳብ ስለማንወድድ ነው፤ ካጠፋሁም ይቅርታ ይደረግልኝና፣ ሀሳብ ይዞ የሚያስተምርና የሚያዝናና ፕሮግራም ጠራችን ነው፤ ሀሳብ እንደ እሳት እንፈራለን፤ ሰይፉ በዱባ ወጥ ቀልዶቹ አሥራ አምስት እና ከዚያ በላይ ዓመታትን ሊያቸከን አይገባም ነበር፤ እንደሕዝብ ቧልተኞችና ሐሜተኞች ስለሆንን ሐሜቱን፣ የሰው ትዳር መፈትፈቱን (እንግዶቹም ያበሽቁኛል፤ ትዳሬን ፈታሁ፣ ትዳሬን አቀናሁ ሲሉ መቀላመድ አልነበረባቸውም፤ የግል ጉዳይ ነውና ቤታቸው ይጨርሱት) እንወድድለታለን።
በሚዲያ የምንሰማው ‹እንትና ከእንትና ተናከሰች፤ እገሊት ከእንትና አረገዘች ወይም ተፋታች› የሚገድደን ሰዎች ነን፤ የቆምንበትንና የደረስንበትን የሚያሳይ አሳፋሪ ጉዳይ ነው፤ ከእኛ ይልቅ የልጆቻችን ዕጣ-ፈንታ ያሳዝነኛል፤ መክሸፍን ነው የምናወርሳቸው፤ በማይረባው የምንገለፍጥ፣ በማያስተምረውና ፈጠራ ባልታከለበት ‹እኚ› የምንል ደላጎች ነን…
…ከማይረባ ፕሮግራም ላይ የሚኮርጁ አሳፋሪ ጋዜጠኞች ሞልተዋል፤ ድኩምን መኮረጅ የባሰ ድኩምነት ነው። የአየር ሰዓት እጥረት ባለበት ሀገር፣ ሀሳብ ባረጠበት ቀዬ፣ ትምህርት እና መዝናናት ቄንጥ በሆኑበት ጊዜ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ላይ ማላገጥ አግባብ አይደለም…
እንዲህ ያለ ብሔራዊ ማላገጥን የሥነ-ምግባር ኮድ አውጥቶ የሚቆጣጠር እና የሚመራ አካል ሊኖር ይገባ ነበር፤ የጋዜጠኝነት እና የቲያትር ሞያ በዚህ ልክ ሊደፈር እና ሊዋረድ አይገባውም፤ እኛ ተመልካቾችም መሸነጋገሉን ትተን እንዲህ ያለውን ሥራ ማውገዝ አለብን፤ የሚበጀውን እንምረጥ፣ ለሀሳብ እንዘጋጅ፤ እንዴት ብሎ ወጥ የላሰ ይሸለማል? ሆቴሎችንና በሳር የተሽሞነሞኑ ሰርጣ-ሰርጦችን ስለምን በመዝናኛ ፕሮግራም ሰበብ ታሳዩናላችሁ? ፒዛ ሲቀቀል ማየት ምኑ ያዝናናል? ሣርና የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ራቁት መታየት የሚያዝናና ነው? መዝናኛ ወግ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ወግ አዋቂ ጋዜጠኛ ያስፈልጋል…
…ወግ፣ ሙዚቃ፣ ባሕል፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ቲያትር፣ ግጥም፣ ቀመር፣ ንባብ፣ ቃለ-መጠይቅ፣ ጨዋታ…ወዘተ. የሌሉበት የመዝናኛ ፕሮግራም ምኑ ነው መዝናኛ ያስባለው? ዕድሜህን፣ ትዳርህን፣ ጤናህን… ሌላም ሌላውንም የሰዋህበትን ሞያ ማንም ገብቶ ሲቀባጥርበት ስታይ ይከብዳል፡፡
ተመልካች ሆይ የሚያዝናና እና እጅ፣ እጅ የሚል ነገር ለይ፤ በማይሆን ፕሮግራም እየሳቅክ ጉንጭህ ጡንቻ እንዲያወጣ አታድርግ፤ ተዝናና ነገር ግን የሚያዝናና እና የማያዝናና ነገር ለይ፤ መዝናናት በፈጠራ እና በአዳዲስ ነገሮች ነው እንጂ በእንቶፈንቶ መዝናናት የለም፤ ለልጆቻችን ይኼንን ደካማነት አውርሰን አንሙት…
…ጉንደር ፍራንክ የሚባል ሶሾሎጂስታዋይ አለ፤ የDependential Theory ጽንሰ-ሀሳብ ባለቤት ነው፤ ይኼ ጽንሰ-ሀሳብ አንድን ሙከራ፣ ሀሳብ፣ ጫና፣ እንቅስቃሴ…ወዘተ. ለማክሸፍ የሚጠቅም ስትራቴጂ ሲሆን፣ በመከልከል፣ በማገድ፣ በድምጸ-ታቅቦ ወይም በዝምታ እንደሚገለጽ ያትታል፤ አንድ ማሳያ እንካችሁ፡-
በላቲኖች፣ በአፍሪካዊያን እና በኤዚያዎች ላይ የሚደርሰውን የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ ለማክሸፍ ወይም ለመምታት አንዳንድ ነገሮችን መከልከል እና ማገድ መፍትሔ እንደሆነ ይናገራል፤ ለምሳሌ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከኤዚያ ወደ አውሮፓ ሄደው እንዳይሸጡ በማድረግ ስፖርትና ባሕላቸውን ማዳከም፣ ቡናን ከአፍሪካ እና ከብራዚል ወደ ምዕራብ ያለመላክ፣ አልማዝን ከደቡብ አፍሪካ ብሎም ኮፐርን ከኮንጎ ወደ ምዕራብ ባለመላክ የምዕራባዊያንን ኢኮኖሚ ማዳከም አንድ ስልት እንደሆነ ይናገራል…
…ይኼንን ጽንሰ-ሀሳብ ወደ መዝናኛ ፕሮግራሞቻችን እናምጣውና፣ ባለመከታተል፣ ስፖንሰር ባለመሆን፣ በመቃወም፣ ሌሎች ነገሮችን በመጠቆም፣ ማሻሻያዎችን በመስጠት… ለልጆቻችን ዕጣ-ፈንታ ብንሠራ ትውልድና ሀገር ይኖረናል፤ በቧልት ዕድሜውን የሚባጅ ትውልድ አይኖረንም፤ ለፈጠራ እና ለአዳዲስ ነገሮች እንዘጋጃለን።
ከአዘጋጁ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛ እና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን ለማዘጋጀት በቅቷል፤ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በyonastamiru@yahoo.com በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።
Via AdissAdmas