“ኤርትራ የምትመራው ነፃነትን በፍፁም
በማይፈቅድ አምባገነን መንግሥት ነው”
ኢንጅነር ፖውሎ አንቶኒዮ
(የኤርትራ ባህረኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)
በዓለም ላይ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች የማይናገሩላትና ዘብ የማይቆሙላት ሀገር ነች፤ ኤርትራ። ይሁን እንጂ በየቀኑ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ስቃይ የሚደርስባት የተዘነጋች ነች። የሻቢያ መንግስት ሀገሪቱን እንደ ወታደራዊ ካምፕ ከያቅጣጫው በአፈሙዝ ወጥሮ ያስተዳድራታል። በኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በጥብቅ አምባገነናዊ ቁጥጥር፣ በፍርሃት ውስጥ ይኖራሉ። ነገ ምን እንደሚፈጠር ዋስትና የላቸውም። ሕይወታቸው ነጻ አይደለም። በወደፊት እጣፈንታቸው ላይ እርግጠኛች አይደሉም።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም በኤርትራ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ቅጥ ያጣ ሰብአዊነት ከዚህ እንደሚከተለው ለማጋራት ይወድዳል። በተጨማሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ጉዳይ በአንክሮ እንዲመለከተው ከወዲሁ ያሳስባል። ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚሻው በኤርትራ ወስጥ በእግር ብረት ከወርች የታሰረው ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በጠብ አጫሪው የኢሳያስ መንግስት የሚታመሰው ቀጠና ጭምር ነው፡፡ በኤርትራ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት በቀጣናው የሚታየውን አለመረጋጋት ለማስከን ጭምር ስለሚረዳ፣ ‹‹እነሆ ትኩረት›› እያልኩ የሚከተሉትን ዝርዝር ሀሳቦች እንደሚከተለው አነሳለሁ።
በኤርትራ ካሉት ችግሮች አንዱ ላልተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ብሄራዊ አገልግሎት ነው። ኤርትራ ውስጥ ማንኛውም ወጣት ለውትድርና ወይም ለመንግሥት መስራት የግዴታው ነው። ዜጎች ይህንን መሰል ፕሮግራም ሲጀመር ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሚቆይ ቃል ተገብቶላቸው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ብዙ ኤርትራውያን ለዓመታት አልፎ ተርፎ ከአሥርት ዓመታት በላይ በውትድርና ብሄራዊ አገልግሎት ለመቆየት ይገደዳሉ። ፍላጎት ባይኖራቸውም እንኳን መብታቸውን ተጠቅመው ለመውጣት አይችሉም። የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በዚህ ብቻ አይቆምም። ለማገልገል ፈቃደኛ አለመሆን ወደ እስር ቤት መወርወርን፣ በማጎሪያዎች ለስቃይ መዳረግን ያስከትላል። ወጣት ታዳጊዎች እንኳን ከትምህርት ቤት ተወስደው በወታደራዊ ካምፖች ወይም በመንግሥት ፕሮጀክቶች ውስጥ እንዲሰሩ ይገደዳሉ።
ይህ አስገዳጅ የውትድርና ስልጠና ስርዓት ሀገሪቱን ለመጠበቅ አይደለም። በሥልጣን ላይ የሚገኘው የሻቢያ መንግሥት፣ ህዝቡን ለመቆጣጠርና የዜጎችን ጉልበት ለመበዝበዝ ያነበረው አምባገነናዊ ስርዓት ነው። ለዚህ ነው ብዙ ኤርትራውያን በገዛ አገራቸው በባርነት እንደሚኖሩ የሚሰማቸው።
ከዚህም በላይ ኤርትራ የምትመራው ነፃነትን በፍፁም በማይፈቅድ አምባገነን መንግሥት ስር ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ እንደ አገር ከተመሰረተች ጊዜ ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉ ሲሆን፤ ምንም አይነት የፖለቲካ ተቃውሞም ሆነ የፓርቲ እንቅስቃሴ ስርዓታቸው አይፈቅድም። ነፃ ምርጫ የለም፣ ነፃ ጋዜጦች አይታሰቡም (ደብዛቸው የጠፉ ጋዜጠኞች እንዳሉ ልብ ይሏል)፣ መንግሥትን የሚቃወሙ ሲቪክ ማህበራትም ሆነ የግል ድርጅቶች ለይምሰል እንኳን አይገኙም። ባለስልጣናትን የሚሞግትና ‹‹ለምን›› ብሎ ለመጠየቅ የሚሞክር ማንኛውም ሰው እጣ ፈንታው እስር ነው። ሊታሰር፣ ሊሰቃይ ወይም በቀላሉ ደብዛው ሊጠፋ ይችላል። ‹‹መንግስት ሁል ጊዜ የውጭ ጠላቶች ኤርትራን ለመጉዳት እየሞከሩ ነው›› ይላል። በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ትርክት እንደ አንድ ትልቅ ፕሮፓጋንዳ በማንሳት በዚያ ጥላ ስር ለመሸሸግ ይሞክራል። ሆኖም ዓለም ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ሀቅ አንደሚያሳየን፣ ይህንን ሰበብ በመጠቀም ሀገሪቱን በጥብቅ ቁጥጥር ስር የማድረግ ያረጀ ያፈጀ ስልትን ነው የሚከተለው።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር በተከፈተ ሰሞን በስፍራው ተገኝቶ እንደታዘበው፤ ኤርትራ ከፖለቲካዊ ጭቆና በተጨማሪ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያለባት አገር መሆኗን ለመመልከት ሞክሯል። ኢኮኖሚው ፍፁም ሽባ ሆኗል፤ ፈርሷል ማለት ይቀላል። ብዙ ሰዎች በድህነትና በርሃብ ይሰቃያሉ። በርካታ ወጣቶች በውትድርና አገልግሎት ግዳጅ ውስጥ ስላሉ በነፃነት መሥራት፣ መነገድና ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ አይችሉም። አብዛኛው የኤርትራዊያን ቤተሰቦች በቂ ምግብ እንኳን ለማግኘት ይቸገራሉ። በዚያች ዝግ አገር ውስጥ ተስፋ ለማግኘት እንኳ በጣም ከባድ ነው። አንድ ሙሉ ትውልድ ኤርትራዊ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል። በአገራቸው ውስጥ ምንም አይነት ተስፋም ሆነ የወደፊት ራዕይን አያዩም።
በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ከዚያች የጨለማ አገር ውስጥ ለማምለጥ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። በረሃ አቋርጠው፣ ከአጋቾች ጋር ይጋፈጣሉ፣ አንዳንድ ጊዜ አውሮፓ ለመድረስ ሲሞክሩ በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው ይሞታሉ። ኤርትራ የፈጠረችው የስደተኞች ቀውስ፣ ኤርትራውያንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ሀገራትንም ጭምር እየጎዳ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራን ስቃይ ችላ ማለቱ ነው። ‹‹አንዱ ምክንያት ኤርትራ ጥቂት የተፈጥሮ ሃብት ያላት ትንሽ ሀገር መሆኗ ነው›› ይለናል በአልጀዚራ ላይ ምልከታውን ያሰፈረልን ፀሀፊ። ይህንን ሀሳብ የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም ይጋራዋል። እንደሌሎች ዘይት፣ ጋዝ ወይም አስፈላጊ የንግድ መስመር ያላቸው አገሮች በቂ ትኩረት እያገኘች አይደለም። በዚህ ምክንያት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ሀያላን ሀገራት ጭምር በኤርትራ መንግስት ላይ በቂ የሚባል ጫና ሲፈጥሩ አይታዩም። ለሰብአዊ መብት መከበርና ለዜጎች ፍትህ ከመቆም ይልቅ ቀጣናውን ለመቆጣጠርና በመዳፋቸው ስር ፀጥ አድርገው ለማቆየት የበለጠ ሲለፉ አንመለከታለን። ይህ ዓለም አቀፋዊ ግዴለሽነት የኤርትራ መንግስት በህዝቡ ላይ ያለ ከልካይ አምባገነናዊ መዳፉን መጫኑን እንዲቀጥል አድርጎታል። ይህንን መሰል ግዴለሽና ለዘብተኛ አቋም በዓለም ዙሪያ ላሉ ሌሎች መሪዎች በጣም አደገኛ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል።
ይህ ስርዓት ወደ ውጭ ለተሰደዱ ኤርትራውያንም የበለጠ ከባድ ነው። ብዙ የኤርትራ ስደተኞች የመንግስትን ስለላ፣ ዛቻና የግዳጅ የውጪ ምንዛሬ ክፍያ (“የዲያስፖራ ግብር”) መቋቋም አልቻሉም። ከትውልድ አገራቸው ቢወጡም የኤርትራ መንግሥት ከሩቅ ሊቆጣጠራቸው ሲሞክር (ቤተሰቦቻቸወን እንደ መያዣ) ይስተዋላል። በዚህ ምክንያት በአገራቸው ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ለመናገር ሳይችሉ ቀርተው አፋቸው ተሸብቦ እየኖሩ ነው። አሁንም ኤርትራ ውስጥ ስላሉት ቤተሰቦቻቸውና ለራሳቸው ደህንነት ጭምር ስጋት አለባቸው። ይህ የሚያሳየው የኤርትራ ጨቋኝ ገዥ አካል፣ ከድንበር በላይ እጁ መርዘሙንና በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያንም ህይወት ጭምር አደጋ ውስጥ መውደቁን ነው፡፡
ኤርትራ ውስጥ ሁሉም ነገር ከወታደራዊ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚያዘጋጁት ለዩኒቨርሲቲ ወይም ለስራ ሳይሆን ለውትድርና አገልግሎት ነው። ስራዎች በአብዛኛው በሻቢያ በኩል ይሰጣሉ። የመንግስት ሰራተኛው ደሞዝ በጣም ዝቅተኛ ነው፤ ዜጎች ሰርተው፣ ጥረው ግረው መለወጥ የማይችሉበት ወጥመድ ውስጥ ይገኛሉ። ይህንን አስከፊ ጭቆና እድል ቀንቷቸው ሰብረው የሚያመልጡት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፤ ድንበሩ ስለተዘጋ በስደት አገር ጥለው መጓዝ አይችሉም። በመንግስት ፕሮፓጋንዳ የታፈነ፣ በኤርትራ ሰማይ ስር ፍርሃት አየሩን የሞላ ነው። በማህበረሰቡ መካከል መተማመን ተሰብሯል። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ‹‹ጎረቤቴ ወይም ጓደኛዬ ለባለሥልጣናት ሊያሳውቅ ይችላል›› ብሎ ይፈራል።
ይህ አስከፊ ስርዓት እንዴት በዚህ ልክ ሊንሰራፋ ይችላል ብለን በጥልቀት ስናስብ፣ በኤርትራ ያለው ችግር ጊዜያዊ እንዳልሆነ ግልጽ ይሆንልናል። የረዥም ጊዜ የተሳሳተ ትርክትና ጥላቻ የወለደው ስርዓት አካል መሆኑ ይገባናል። ኢሳያስ አካሄዱን ለመቀየር ፍፁም ፍላጎት የለውም። ዋናው አላማው በህዝብ ላይ ምንም ቢደርስ በስልጣን ላይ መቆየት ነው። ይህ ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለመላው ቀጣና ትልቅ ችግር ይፈጥራል። ከኤርትራ የሚሰደደው የስደተኞች ጎርፍ፣ በጎረቤት ሀገራት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ይገኛል።
አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳንና ሌሎች የጎረቤት ሀገራት ላይ ስደተኞች ትልቅ ጫና ፈጥረዋል። ጠለቅ ብለን ስናየው አውሮፓ ውስጥ የተፈጠረው የስደተኞች ትርምስ የዚሁ ፈተና አካል ነው። ምእራባውያኑ ከምንጩ መፍትሄ ከማምጣትና አምባገነናዊ ስርዓት እንዲወገድ ከህዝቡ ጋር ከመስራት ይልቅ ድንበሮቻቸውን በኤሌክትሪክ ሽቦ ማጠር ምርጫቸው አድርገዋል።
ዓለም በኤርትራ ጉዳይ የመረጠው ዝምታ ታላቅ የሞራል ውድቀት ነው። ሰብአዊ መብት በሁሉም ቦታ ለሁሉም ሰው በእኩል አስፈላጊ ነው። ኃያላን አገሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የኤርትራን ስቃይ ዓይናቸውን ጨፍነው እየሸሹት ነው። ለሁሉም ሰው ሰብዓዊ ክብርና ነፃነት ይገባዋል። ይህ ግን ለኤርትራና ኤርትራዊያን ሲሆን አይሰራም። ቸልተኝነቱ የአንዳንድ ሰዎች ህይወት ከሌሎች ያነሰ ዋጋ እንዳለው ተደርጎ እንዲቆጠር አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል። ይህ ድርጊት ከሞራል ውድቀትም ያለፈ ግዙፍ ስህተት ነው። በእኔ እይታ የኤርትራ ህዝብ የዓለምን ትኩረት፣ ክብርና ያልተገደበ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባዋል።
የኤርትራ የጭቆናና አምባገነናዊ ስርዓት፣ የእውነተኛ የሰው ልጆች ሁሉ ህመም ሊሆን ይገባል። ነፃነትን ሳያዩ የሚሞቱ ሽማግሌዎች ህልም ልብ ይሰብራል። በዚህ ስርዓት የሚሰቃዩ ኤርትራዊያን ሁሉ ሰርተው፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብት ያላቸው ሰዎች ናቸው። በመሆኑም ትኩረትን ይሻሉ።
የኤርትራ መንግሥት “አገራዊ ስጋት ስላለ (በውጪ ወራሪ ምክንያት) በጠንካራ አምባገነናዊ ስርዓት ስር፣ ሁሉም ብሄራዊ ውትድርና እየሰለጠነ በተገደበ ነፃነት መኖር አለበት” የሚል ውሀ የማያነሳ ፕሮፓጋንዳ ሁሌም ይነዛል። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር በተደረገው የሰላም ስምምነት ጊዜም ቢሆን፣ ኢሳያስ ለህዝቡ ነፃነትን የመስጠት እቅድ እንዳልነበረው ግልፅ ነው፡፡ አሁንም አፈናው በዚሁ ልክ ቀጥሏል። ይህ የሚያሳየው ለኤርትራውያን እውነተኛ ስጋት በጠላትነት የተፈረጁ ጎረቤቶች ሳይሆኑ እራሳቸው ገዥዎች መሆናቸውን ነው።
የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኤርትራ ጉዳይ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት ብሎ ያምናል። የኤርትራውያን መከራና ስቃይ ፍፁም ቸል ሊባል አይገባም። ፖሊሲ አውጪዎች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የኤርትራን ቀውስ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። በሃያላን ሀገሮች የእርስ በእርስ የዝሆኖች ልፊያ ላይ ብቻ ማተኮር በቂ አይደለም። እያንዳንዱ የሰው ልጅ ለምድራችን በእኩል አስፈላጊ ነው።
ሀሳቤን ሳጠቃልል፤ በኤርትራ ያለው ቀውስ፣ ከሰብዓዊ መብቶችና ከሰው ልጆች ርህራሄ ያፈነገጠ እውነተኛ ወንጀል፣ ጥልቅ ቀውስና ልብ የሚሰብር ድርጊት መሆኑን አምናለሁ። ኤርትራን “የተዘነጋች አገር” ብቻ ብሎ መግለጽ በቂ አይደለም። የኢሳያስ አምባገነናዊ ጭካኔ የተሞላበት በሰው ልጆች ላይ የተቃጣ ድርጊት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መቋጫ በሌለው ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ሳቢያ ለታሰሩ፣ በረሃብ ለሚሰቃዩ፣ በድህነትና በፍርሃት ለሚገኙ ዜጎች እርህራሄ ሊሰማን ይገባል። የዓለም ማህበረሰብ፣ ዝምታው የውድቀት ምልክት መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። ከሁሉም በላይ የኤርትራ ህዝብ እራሱ ዝምታውን መስበር፣ ታሪኩ፣ መብቱና ማንነቱ እንዲመለስለት ዘብ መቆም አለበት። ኤርትራ የተረሳች ሀገር ሆና መቀጠል የለባትም። ህዝቦቿ ነፃነት፣ ክብርና የወደፊት ተስፋ ያሻቸዋል፡፡ በፍርሃትና በአምባገነናዊ ሥርዓት ተሸብበው እስከ መቼ ይኖራሉ? ፍትሀ ለሰው ልጆች ሁሉ ይስፈን። ሰላም!!
AdissAdmas
TIPS
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security
Ethiopia, Creditors Agree on $8.4 Billion Debt Restructuring
Ethiopia’s peaceful quest for access to sea gained int’l recognition: PM Abiy