የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዋሽ–ኮምቦልቻ–ሃራ ገበያ የባቡር መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከቱርኪዬ የሥራ ተቋራጭ “ያፒ መርከዚ” ጋር በለንደን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለሦስት ዓመታት ሲያደርግ በነበረው የአንድ ቢሊየን ዶላር ክስ ድል እንደቀናው ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማከናወን ተመርጦ ውል በመዋዋል ግንባታውን ሲያከናውን የነበረው የቱርኪዬ የሥራ ተቋራጭ “ያፒ መርከዚ”፤ የሰሜኑ ጦርነት በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ያደረሰውን ጉዳት፣ የንብረቶች ዝርፊያና የግንባታ መስተጓጎል ምክንያት ጠቅሶ፤ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው የሚጠይቅ ክስ በለንደን ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት መክፈቱ ይታወሳል።
የቱርኪዬ ሥራ ተቋራጭ ያፒ መርከዚ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍለው በመጠየቅ የመሠረተው ክስ ውድቅ ተደርጎ፤ በተሻለ መልኩ ውጤት የተገኘበት ሲሆን፤ የፍርድ ቤቱ ክርክር ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
የለንደኑ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ሦስት ዓመታትን ከፈጀ የፍርድ ክርክር በኋላ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ከፊል ውሳኔ ማሳለፉው ነው የተነገረው፡፡
ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የውልና የሕግ መከራከሪያዎችን በመቀበል፣ የሥራ ተቋራጩ በኮርፖሬሽኑ ላይ ካቀረበው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የካሳ ክፍያ ጥያቄ ውስጥ አመዛኙን ውድቅ መሆኑን አሐዱ ባገኘው መረጃ ለማወቅ ችሏል፡፡
የሥራ ተቋራጩ ከቱርኪዬ ሀገር እና ከእንግሊዝ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ሲከራከር የቆየ እና ጉዳዩ ረጅም ጊዜ የወሰደ የክርክር ሂደት የነበረው ቢሆንም፤ የሥራ ተቋራጩ ውጤት እንዳልቀናው ታውቋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ በኩል ጉዳዩ በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው በኩል በከፍተኛ ጥንቃቄና ክትትል ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲመራ መቆየቱም ነው የተነገረው፡፡
በተጨማሪም ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የሕግ ባለሙያና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እና የኮርፖሬሽኑ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ሙላቱ የሕግ ጉዳዮቹን ሲከታተሉ እና በለንደን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርበው ክርክር ሲያደርጉ እንደነበር ማወቅ ተችሏል፡፡
በኮርፖሬሽኑ ላይ በለንደን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርቦበት የነበረው ክስ እንደሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ላይ ከቀረቡ ክሶች ከፍተኛው እና ትልቁ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ግንባታው የተቋረጠውን የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር መሠረተ ልማት ቀሪ ሥራዎች በማስቀጠል፣ በአጠረ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑ ታውቋል።