በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ሰሞኑን ከደመወዝና ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ያሉባቸውን ቅሬታዎች በተለያዩ መንገዶች ሲገልፁ ቆይተዋል። ይህ የጤና ባለሙያዎቹ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ማሻሻያ ጥያቄ አሁን ጎልቶ ወጣ እንጂ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ሲቀርብ እንደነበር ይታወሳል።
I shall do by my patients as I would be done by; shall obtain consultation whenever I or they desire; shall include them to the extent they wish in all important decisions; and shall minimize suffering whenever a cure cannot be obtained, understanding that a dignified death is an important goal in everyone’s life.
የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ካለባቸው የሥራ ጫናና ለኅብረተሰቡ ከሚሰጡት ያለተቆጠበ የጤና አገልግሎት አኳያ አሁን ላይ እየተከፈላቸው ያለው ደመወዝና የሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም በቂ ነው ማለት ባይቻልም፤ አጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ መክፈል ከሚችለው አኳያ ሲታይ የደመወዝ ሆነ የጥቅማጥቅም ጥያቄው ቀጣይ ሀገራዊ ልማት ላይ የሚመሠረት ነው።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግም የጤና ባለሙያዎች ያለባቸውን የኑሮ ጫና ተቋቁመው ለማህበረሰቡ ጤና ትኩረት ሰጥተው ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ሲወጡና ለሙያቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ሲጠብቁ ቆይተዋል። አሁንም አብዛኛው የጤና ባለሙያ ከእዚህ የተለየ መንገድ ላይ አይደለም።
የሕክምና ባለሙያዎች የደመወዝ ሆነ የጥቅማጥቅም ጉዳይ አጠቃላይ ከሆነው የሀገር ኢኮኖሚ እና ከደረሰበት እድገት ደረጃ የሚወሰን ነው። ባደጉት ሀገራት የሕክምና ሙያ ትልቅ ክብር የሚሰጠውና ሙያተኛውም ትልቅ ተከፋይ ናቸው። የአቅም ጉዳይ ሆኖ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ያለው የተለየ ነው። ለሙያው የሚሰጠው ክብር ብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ ባይሆንም የተከፋይነታቸው እውነታ ግን በብዙ የተለየ ነው።
ለእዚህ ከአገልግሎት ጥረት ጀምሮ የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀርቡም ገዥው ምክንያት ግን ቀደም ሲል ለማንሳት እንደሞከርኩት የሀገራት ኢኮኖሚ የመክፈል አቅም እንደሆነ ይታመናል። የአገልግሎት ክፍያውም ቢሆን፤ የዛኑ ያህል ልዩነት እንዳለው የሚታወቅ ነው።
የኢትዮጵያም ሁኔታ ከእዚህ እውነታ የራቀ አይደለም። አሁን ላይ ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለሕክምና ባለሙያዎች አሁን ካለው ክፍያ የበለጠ ደመወዝ መክፈል የሚያስችል አቅም አለው ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም። ልክፈል እንኳን ቢባል አጠቃላይ የሆነውን የሀገር ኢኮኖሚ ሊጎዳ በማይችል መንገድ መሆን አለበት።
በርግጥ እንደ ሀገር የክፍያ ችግሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሆነው የመንግሥት ሠራተኞች መሆኑንም አብሮ ማስተዋል ተገቢ ነው።የትኛውም ሙያ እንደ ሙያ ለሀገር እና ለሕዝብ ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ የሚሰላ ጠቀሜታ አለው። ለእዚህ ጠቀሜታው የሀገርን አቅም ያገናዘበ ክፍያ ይጠይቃል።
ከእዚህ ጎን ለጎን (ከኢኮኖሚው) ባለፈ እየጨመረ የሚሄደው የሕዝብ ቁጥርም በሕክምናው ዘርፍ ለሚስተዋለው ችግር ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። በሚጨምረው የሕዝብ ቁጥር ልክ ተመጣጣኝ የሆነ የሕክምና ባለሙያዎችን ለማፍራት እና የጤና መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት መንግሥትን ተጨማሪ ወጪ ይጠይቀዋል።
አሁን ላይ የተነሳውን የሕክምና ባለሙያዎች ጥያቄ ለመመለስ ከሁሉም በላይ አሁናዊ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቅጡ መረዳት ይጠይቃል። ሀገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ እውነታም ማስተዋል ተገቢ ነው። ይህንን እውነታ የጤና ባለሙያው አይመለከተኝም፤አያገባኝም የሚለው አይደለም።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የትኛውንም ደረጃ ላይ ይገኝ የሕክምና ባለሙያዎች ያነሱት ጥያቄ በመርህ ደረጃ ተገቢ እንደሆነ ይታመናል ። ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ ግን በአግባቡ በተጠና እና ዘላቂነት ባለው መንገድ መሆን አለበት። ዛሬ ለነገ ተብሎ የሚሰላም አይደለም።
አሁን ላይ ባለው ሀገራዊ ተጨባጭ እውነታ በኑሮ ውድነት ምክንያት ያልተፈተነ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፤ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግሥት ከፍተኛ ሀብት በድጎማ መልኩ እያፈሰሰ ይገባኛል የጤና ባለሙያዎችም የእዚህ ድጎማ ተጠቃሚ መሆናቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ተጠቃሚ ናቸው።
ይህም ሆኖ ጥያቄው በአብዛኛው የጤና ባለሙያው በሰላማዊ መንገድ ያቀረበ እና በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ከመሆኑ አኳያ መንግሥት አሁን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ታሳቢ ያደረገና የኑሮን ሁኔታ ያገናዘበ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ማሻሻያዎችን ለሕክምና ባለሙያዎች ደረጃ በደረጃና በሂደት ማድረግ እንደሚኖርበት ይታመናል።
የሕክምና ባለሙያዎች ያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት የራሱ የቤት ሥራዎች እንዳሉበት ሁሉ የሕክምና ባለሙያውም ያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃና በሂደት እያቀረበ በትእግስት መጠባበቅ ይኖርባቸዋል ። በተለይ ከገባው ሙያዊ ቃልኪዳን አንፃር በፍጹም ሥራውን ሊበድል አይገባም።
ዘር፣ቀለም፣ ፆታ፣ሃይማኖትና ሌሎችንም ቅደመ ሁኔታዎችን ከግምት ሳያስገባ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ የተነሳ ነውና ይህንኑ ሙያዊ ግዴታውን አክብሮ ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ይጠበቅበታል። የዘርፉን የእለት ተእለት ሥራ የሚያደናቅፉ ተግባራትን ማከናወን ከሞራል ተጠያቂነት ባለፈ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን በአግባቡ መገንዘብም ተገቢ ነው።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕዝባችን የጤና እክል ሲገጥመው መዳረሻው የመንግሥት ጤና ተቋማት በመሆኑ የሕክምና ባለሙያው የቱንም ያህል የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርበት እርሱን አምኖ ለመጣው ለእዚህ ማህበረሰብ በፍጹም ትህትናና ሙያዊ ሥነ ምግባር አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል።
እንዲህ ዓይነቱ የሕክምና ባለሙያዎች የደመወዝና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ ጥያቄ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ጥያቄው የሚቀርብበት መንገድ ቢለያይም ካሁን ቀደምም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ነበሩ። በየዘመኑ የነበሩ መንግሥታትም ከሕክምና ባለሙያው የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በየራሳቸው መንገድ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። የአሁኑ መንግሥትም አሁን ላይ ከሕክምና ባለሙያዎች በኩል እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን ለመመለስ ዝግጁነቱን አሳይቷል።
የሕክምና ባለሙያውም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሥራውን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም፤ ያሉበትን ጥያቄዎች ለመንግሥት ሲያቀርብ ለሙያው የገባውን ቃልኪዳን ተፈፃሚ እያደረገ ሊሆን ይገባል። ሥራውን ትቶ መንግሥትን በመቃወምና በአድማ የደመወዝና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ እንዲደረግለት መጠየቅ አንድም ራሱን ሁለትም እርሱን ብሎ የሚመጣውን ታካሚ ማህበረሰብ የሚጎዳ ነው !!
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በአስናቀ ፀጋዬ አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም