የኬንያው ኬሲቢ ግሩፕ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ “ቅርንጫፍ ለመክፈት ወይም አዲስ ለማቋቋም” ሳይሆን በሥራ ላይ ከሚገኙት አንዱን መግዛት ይፈልጋል። በታኅሳስ 2018 ገደማ የውጪ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። መጪዎቹ ወራት የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በርከት ያሉ ለውጦች የሚያይበት ይመስላል።
ኬንያዊው ፖል ሩሶ ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ የተገኙት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ኬሲቢ ግሩፕ አዲስ ወደሚከፈተው ገበያ ለመግባት እንደቆረጠ ለማሳወቅ ጭምር ነበር። ኩባንያቸው በሥሩ በሚገኙ ድርጅቶች በኩል በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በኢንቨስትመንት እና በባንክ ሥራ ላይ የተሠማራ ነው።
ኬሲቢ ግሩፕ ባለፉት ዓመታት ዐይኑን በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ጥሎ ቆይቷል። ፖል ሩሶ “እዚህ የተገኘሁት ኬሲቢ በኢትዮጵያ እንደሚገባ ለመግለጽ ነው” ሲሉ ኩባንያቸው ያሰበውን የሚያሳካበት ጊዜ ለመድረሱ ጥቆማ ሰጥተዋል። በቀጠናው ትልቁ አበዳሪ የሆነው ኬሲቢ ግሩፕ 15.5 ቢሊዮን ዶላር ጥሪት ያለው ግዙፍ ኩባንያ ነው። በችርቻሮ የባንክ ሥራ ከደንበኞቹ በተጨማሪ ለግዙፍ የመሠረተ-ልማት እና ኢንዱስትሪ ግንባታዎች፣ ለንግድ እና ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብድር ያቀርባል።
ፖል ሩሶ የሚመሩት ኬሲቢ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት የኬንያ ንግድ ባንክ እና የኬንያ ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል። በደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ታንዛኒያ የባንክ ሥራዎች የሚያከናውኑ ኩባንያዎችም በሥሩ ይገኛሉ። ኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኝበት በኬንያ፣ በርዋንዳ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዳደረገው ሁሉ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ከሚገኙ ባንኮች አንዱን መግዛት ይፈልጋል።
“ቅርንጫፍ ለመክፈት ወይም አዲስ ለማቋቋም እንደማንፈልግ ግልጽ ነን። በተደነገጉት ደንቦች መሠረት ግዢ ለመፈጸም እያሰብን ነው” ሲሉ የኪሲቢ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፖል ሩሶ ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ገበያ የሚሰጠውን ዕድል እየተመላለሱ መታዘባቸውን የገለጹት ፖል ሩሶ “ለውጥ አይቻለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢትዮጵያ የባንክ ገበያዋን የምትከፍትበት መጪው ጊዜም ብሩህ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
እንደ ኬሲቢ ግሩፕ ያሉ ኩባንያዎች ወይም ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የባንክ ሥራ አዋጅ የጸደቀው ታኅሳስ 8 ቀን 2017 ነበር። የውጪ ባንኮች በኢትዮጵያ ተቀጥላ በማቋቋም፣ በሥራ ላይ ከሚገኙ ባንኮች ድርሻ በመግዛት፣ ቅርንጫፍ በመክፈት አሊያም የውክልና ጽህፈት ቤት ከፍቶ መሥራት በአዋጁ ተፈቅዶላቸዋል።
“ብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ በአግባቡ የተቋቋሙ፣ መልካም ሥም እንዲሁም ጤናማ የፋይናንስ አቋም ያላቸው የውጪ ባንኮች በግዢ አማካኝነት ነባር የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲይዙ ሊፈቅድ ይችላል።” ይህ የሚሆነው “ለኢኮኖሚው ጠቀሜታ ያላቸው ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና ወይም ችግር ውስጥ ላለ ባንክ እልባት ለመስጠት የፋይናንስ መረጋጋትን ለማስጠበቅ” እንደሆነ በአዋጁ ሠፍሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጪ ባንኮች ፈቃድ የሚሰጥበት መመሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ ጆቴወርቅ ጉደታ “እጅግ በቅርቡ ይጸድቃል” ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ጆቴወርቅ ባለፈው ሣምንት በተካሔደው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ እንዳሉት የሀገሪቱ ባንኮች አጠቃላይ ትርፍ ባለፉት ዓመታት ከ10 እስከ 20 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ የባንክ ተጠቃሚው 65 በመቶ ብቻ ቢሆንም ባለፈው ዓመት ኢንዱስትሪው 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንዳተረፈ ጆቴወርቅ አስረድተዋል።
የውጪ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የብሔራዊ ባንክ ሹማምንት የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ ፈጠራ እና ቅልጥፍናን ማፋጠን እንዲሁም የኢትዮጵያን ገበያ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ጋር ማስተሳሰር ይፈልጋሉ።
ኢትዮጵያ በገበያዋ የውጪ ባንኮችን ለማስተናገድ ስትዘጋጅ ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ የብድር አሰጣጥ እና የኮርፖሬት አደረጃጀትን ጨምሮ በበርካታ የባንክ ሥራ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ አድርጓል። ብሔራዊ ባንክ ከዓለም እንኳ ባይሆን ቢያንስ በአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ተቋማት አንዱ ሆኖ ለመገኘት ራሱን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ምክትል ገዥው ሰለሞን ደስታ ተናግረዋል።
የባንኩ ባለሙያዎች በሥመ-ጥር ተቋማት ስልጠና ማግኘታቸውን የገለጹት ሰለሞን የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባልደረቦች እያማከሯቸው መሆኑን ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ “መሠረቶቹ ጠንካራ ናቸው፤ ዘርፉም በስሏል። ጥቅማችንን በማሳደግ እና ጉዳቱን በመቆጣጠር ማሻሻያውን በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ የእኛ ፋንታ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
መጪዎቹ ወራት የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በርከት ያሉ ለውጦች የሚያይበት ሊሆን እንደሚችል የመንግሥት ባለሥልጣናት ባለፈው ሣምንት ጥቆማ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ባንክ የሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ በመስከረም 2018 በዋጋ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስከ ታኅሳስ 2018 ባለው ጊዜ የመጀመሪያውን ፈቃድ ለውጪ ባንክ ይሰጣል ተብሎ ይጠቃል።
ኢትዮጵያ የውጪዎቹን ባንኮች ስትጠብቅ የዓለም ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት (FSSP) ባለፈው ሣምንት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። በዚህ ፕሮጀክት ዓለም ባንክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት 700 ሚሊዮን ዶላር ብድር ይሰጣል። በፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው ብድር አብዛኛው ኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥትን ፋይናንስ ለማድረግ የተጠቀመበትን የንግድ ባንክ ከገባበት ቀውስ ለመታደግ የተደለደለ ነው።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገቢራዊ የሚደረግ ነው። ሦስቱን የመንግሥት ተቋማት በማጠናከር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ለማሳደግ የተዘረጋው ፕሮጀክት አራት አላባዎች አሉት።
የባንክ ዘርፉን የቁጥጥር እና አስተዳደራዊ ማዕቀፍ እንዲሁም የብሔራዊ ባንክን ተቋማዊ አቅም ማጠናከር የመጀመሪያው ዓላባ ነው። ሁለተኛው የፕሮጀክቱ ዓላባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለማሻሻል፣ መልሶ ለማዋቀር እና የመሥሪያ ካፒታሉን ለማሳደግ የታቀደ ነው።
ባለፈው ሣምንት በተካሔደው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ ላይ በዓለም ባንክ ከተፈቀደው ብድር ውስጥ 253 ሚሊዮን ዶላር ወደ ንግድ ባንክ ገቢ መደረጉን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል። “ከሰኔ መጨረሻ በፊት ተጨማሪ 400 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይለቀቃል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ንግድ ባንክ ተሸክሞት የቆየውን 845 ቢሊዮን ብር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ በአስር ዓመታት ውስጥ ግብር ሰብስቦ ለመክፈል ገንዘብ ሚኒስቴር ተረክቧል። ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የዕዳ ሠነድ አማካኝነት የንግድ ባንክን የመሥሪያ ካፒታል ለማሳደግ 316 ሚሊዮን ብር ገደማ መድቧል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢራዊ የሚደረገው የዓለም ባንክ ፕሮጀክት ክፍል በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ባንኩ የተፈቀደለትን የገንዘብ መጠን ከእጁ ለማስገባት ጥብቅ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅበታል። አቶ አቤ ሳኖ በፕሬዝደንትነት የሚመሩትን ባንክ አስተዳደር ማሻሻል ቀዳሚው ሥራ ነው።
በሁለተኛው ምዕራፍ የተበላሹ ብድሮችን ለማስወገድ እና የሥጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የባንኩን የሒሳብ መዝገብ መልሶ ማዋቀር ያስፈልጋል። ሦስተኛው እና የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ማሳደግ ይሆናል። ዓለም ባንክ በፕሮጀክቱ ለንግድ ባንክ የሚሰጠው ገንዘብ ለሌላ የብድር አገልግሎት መዋል እንደማይችል መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም ስለ ፕሮጀክቱ ያሠፈረው ማብራሪያ ይጠቁማል።
ዓለም ባንክ በዚህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ 700 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያበድር የተገለጸው በሐምሌ 2016 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ባደረገበት ወቅት ነው። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚደጎመው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር መንግሥት የሚከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ በማዘመን የዋጋ ግሽበትን የመግታት ዓላማ ጭምር አለው። በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን የቀጥታ ብድር በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማቆም ወስኗል።
በምትኩ መንግሥት የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ፊቱን ከሀገር ውስጥ አማራጭ የብድር ምንጮች ወደ ማፈላለግ አዙሯል። በብሔራዊ ባንክ በኩል ለሽያጭ የሚቀርበው የግምዣ ቤት ቤት ሰነድ ወይም ትሪዠሪ ቢል አንዱ የመበደሪያ መሣሪያ ነው። እስካሁን በነበረው አሠራር ባንኮች እና የጡረታ ፈንዶች ይህን የዕዳ ሠነድ ሲገዙ ቆይተዋል።
ባለፈው ሣምንት የመንግሥት የመዋዕለ-ንዋይ ክንድ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሰባት ቢሊዮን ብር የግምዣ ቤት ሰነድ መግዛቱ ይፋ ተደርጓል። ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸመውን የግምዣ ቤት ሠነድ ግዢ “የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የዋጋ ግሽበት ወደ ማያስከትሉ የብድር ምንጮች” መዘዋወሩን እንደሚያሳይ የገለጹት አቶ ማሞ “እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ታሪካዊ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ባንኮች የግምዣ ቤት ሠነድ በመግዛት ለመንግሥት እንዲያበድሩ የተጣለባቸው ግዴታ በሰኔ ወር ይነሳል። አቶ ማሞ ምኅረቱ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግምጃ ቤት (Central Securities Depository) በቅርቡ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰው ዘመናዊ የፋይናንስ መሠረተ ልማት እንዳላቸው ሌሎች ሀገሮች “ወደፊት” የግምዣ ቤት ሰነድ ለግለሰብ ኢንቨስተሮች ለሽያጭ መቅረብ እንደሚጀምር ይፋ አድርገዋል።
እርምጃው “እጅግ ጠቃሚ” መሆኑን የገለጹት አቶ ማሞ መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ከባንኮች እና የጡረታ ፈንዶች ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት የንግድ ኩባንያዎች፣ የኢንሹራንስ ተቋማት እና የችርቻሮ ኩባንያዎች ጭምር ለመበደር እንደሚፈቅድለት አስረድተዋል።
ባንኮች የግምዣ ቤት ሠነድ በመግዛት ለመንግሥት እንዲያበድሩ የተጣለባቸው ግዴታ በሰኔ ወር ይነሳል። ገንዘብ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባንክን የቀጥታ ብድር ቢያቆምም መንግሥት የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በተጨማሪ ሌሎች አበዳሪዎች ያስፈልገዋል። አቶ ማሞ ከባንኮች እና የጡረታ ፈንዶች በተጨማሪ ወደፊት የግምዣ ቤት ሠነድ ለመንግሥት የንግድ ኩባንያዎች፣ የኢንሹራንስ ተቋማት እና ግለሰቦች እንደሚሸጥ ተናግረዋል።
DW amharic