የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ወደ ዋሺንግተን በማቅናት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተወያይተዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካረረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ በሚል ነው ውይይት ያደረጉት።
በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ንብረታቸው የመቀማትና የዘር ጭፍጨፉ እየተካሄደ ነው በሚል አሜሪካ ደቡብ አፍሪካን ስትከስ ቆይታለች።
በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ግፍ እየደረሰ ነው የሚለውን ሀሳብ ያቀረቡትና አሜሪካ ፊቷን በደቡብ አፍሪካ ላይ እንድታዞር በብርቱ የሰሩት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ውልደት እና እድገታቸው የሆነው ቢሊየነሩና የዶናልድ ትራምፕ የተሾሙት ኤሎን መስክ ናቸው።
ከዚህ ክስና ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በኋላ ባለፈው ጊዜ 60 ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ እንደተጓዙና አቀባበል እንደተደረገላቸው ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ በሌላ ጎን በነጮች ላይ የደረሰ አንዳች የዘር ጭፍጨፉም ሆነ መድሎ የለም፤ የሀሰት መረጃ ነው። የሸሹትም ቢሆን ፈሪ ናቸው ስትል ክሱን ስታጣጥል ቆይታለች።
ይህንን ውዝግብ ለማርገብ ታዲያ በራማፎሳና ትራምፕ መካከል ውይይት ተደርጓል።
የሚዲያ የቀጥታ ሽፉን ባገኘው በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‘ግፍ ደርሶብናል’ የሚሉ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በየመንገዱ ሲቃወሙ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልና ‘ተገድለዋል’ ያሏቸውን ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ገበሬዎች ምስል ለሚዲያና ለራማፎሳ በማሳየት ፕሬዝዳንቱን ለማሸማቀቅ ሞክረዋል።
ይህም ሳያንስ ይህ የተፈፀመው የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የዘር ጭፍጨፉ በትክክል የት እንደሆነ ባላቅም ማብራሪያ ግን እፈልጋለሁ ሲሉ ራማፎሳን አፉጠዋል።
ራማፎሳ በተቃራኒው በትራምፕ በዚህ ሁሉ ድርጊት ሳይደናገጡ በመረጋጋት ምላሽን ሰጥተዋል።
“ይህ የተመለከቱት በቪዲዮም የነበረው ንግግር የመንግስታችን ፖሊሲ አይደለም፤ ሁሉንም አካታችና ባለብዙ ወገን የዲሞክራሲያዊ ስርአት ባለቤት ነን። በዚህም ሁሉም እራሱን በነፃነት የመግለፅ መብት ተሰጥቶታል” ብለዋል።
ከዶናልድ ትራምፕ በኋላ በጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ‘ነጮች የተይተው ተጨፍጭፈዋል’ እንዲሁም ;መሬታቸው ተነጥቋል’ የሚሉ ጥያቄዎች የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዝዳንት ለማፋጠጥ ሙከራ ሲያደርጉ ታይቷል።
የዶናልድ ትራምፕና የሲሪል ራማፎሳን ውይይት በዚሁ በኦቫል ቤተመንግስት በወረሃ የካቲት የተደረገውን የትራምፕና የዘለንስኪ ውይይት ጋር በርካቶች እያመሳሰሉት ይገኛሉ።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ከነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ጉዳይ በዘለል በሁለቱ ሀገራት የንግድ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት አልመው ነበር የተጓዙት።
የዶናልድ ትራምፕ የ30 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ከተደረገባቸው ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ መሆኗ ይታወሳል።
ዘገባው የቢቢሲና አልጀዚራ ነው። ኢቲቪ ዜና