እድሜው ለጋ ሀሳቡ ትልቅ ነው። ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን አሻግሮ ማየት ችሏል። ኃይለሥላሴ አበራ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ቀጨብራ ወራዳ ነው። ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በትምህርቱም ከቀለሜዎች መካካል ነው።
ፍላጎት ካለ የማይቻል ነገር የለም የሚል መርህ አለው። ህልሙና ስራው ኃያል ነው። ህልሙ ኢትዮጵያ በልጆቿ እጅ የተሰራ አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ እንዲኖራት ነው። ህልሙ በምኞት አልቀረም፤ በለጋ እድሜው ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ በመስራት መቻልን በተግባር አሳይቷል።
ኢንተርኮንቲኔንታል ባልስቲክ ሚሳኤል ወይም አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ በመስራት በ4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድርና አውደርዕይ ላይ ለዕይታ አቅርቧል።
ሚሳኤሉን ለመስራት መነሻ ያደረገው በሰሜን ኮሪያ ህዋሶንግ 19 ሞደል መሆኑን ገልጾ፤ እነሱ በሰሩት ሚሳኤል ደካማ ጎኖችን ለይቸ እኔ አሻሽዬ ሰርቻለሁ ይላል።
ወላጆቹ በግል ትምህርት ቤት ከፍለው ያስተምሩታል። የቤት ኪራይ፣ የስንቅና የተለያዩ ወጪዎች እንዳሉበት ይናገራል።
ይህንን የፈጠራ ስራ በሚሰራበት ወቅት የፋይናንስ ችግር በእጅጉ እንቅፋት እየሆነበት እንደነበር ያብራራል።
አርቆ አሳቢው ታዳጊ ሀይለሥላሴ ለስንቅ ከሚሰጠው ገንዘብ በመቆጠብ ለፈጠራ ስራው ግብዓቶችን የሚገዛ ቢሆንም ለዚህም በቂ አቅም የሌለው በመሆኑ በቀላሉ ከአከባቢው የሚያገኛቸውን ቁሳቁሶቸ ለመጠቀም መላ ዘየደ።
ሚሳኤሉን ለመስራት ከህንጻ መሳሪያ፣ ከኤሌክትሮኒክስ ጥገና ቤቶች፣ ከሞተር ጋራዥ፣ ከፈርኒቸር ቤቶችና በሰፈር የወዳደቁ ዕቃዎችን ተጠቅሚያለሁ ሲል ያብራራል። እንዲሁም አብረው ከሚማሩት የቀለም ጓደኞቹ ገንዘብ በማሰባሰብ ለስራው ግብዓት የሚሆን ኬሚካል ገዝቶ ተጠቅሟል።
ሚሳኤሉን ለመስራት ያነሳሳው የሀገርን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት በዘመናዊና ቅንጡ የጦር መሳሪያ ለመጠበቅ መሆኑን ይናገራል። ዘጠኝ የሚደርሱ የአውሮፓ ሀገራት ሚሳኤሎችን እንደሚያመርቱ አንስቶ፤ ኢትዮጵያም የተኛውንም ነገር መስራት እንደምትችል ለማሳየት ሚሳኤሉን ሰርቻለሁ ይላል።
የይቻላል መንፈስ ስንቁ የነገ ተስፋው ትጥቁ የሆነለት ወጣት ሀይለሥላሴ፤ ያለማንም እርዳታ ይህን የፈጠራ ስራ ለመስራት አምስት ወር ፈጅቶበታል።
በርካታ ሀገራት የዘመናዊ የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ኢትዮጵያም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማይፈታ ችግር ቢገጥማት መመከት ያለባት ቀደም ባሉት ጊዜያት በተጠቀመቻቸው ጦርና ጋሻ ሳይሆን በዘመናዊ መሳሪያ ሊሆን ይገባል ሲል ያስረዳል።
ሚሳኤሉን በራሴ ጥረት ሰርቼ እዚህ አድርሻለሁ። በቀጣይ የሚመለከታቸው በለድርሻ አካላት ድጋፍ ካደረጉልኝ ለሀገሪቱ ትልቅ ሀብት ማበርከት እንችላለን ይላል።
ሚሳኤልን በሚመለከት ተተኪ ትውልድ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው መጽሀፍ መጻፉንም ያብራራል።
ታዲያ ፅንስ ሀሳቡን ከበይነመረብ በቀላሉ ማግኘት ቢቻለም ተግባራዊ ክህሎትን ማግኘት አዳጋች እንደሆነ የሚገልጸው ተማሪ ሀይለሥላሴ፤ የሚመለከተው መንግስታዊ አካል ተነሳሽነቱን በመመልከት ድጋፍ ካደረጉለት በቅርቡ ወደምርት የማስግባት ውጥን ይዟል።
አሁን ላይ ያለው ወጣቱ ትውልድ ቴክኖጂን በአግባቡ በመጠቀም እራሱንና ሀገሩን መቀየር ካልቻለ መጥፊያው ልሆን እንደሚችል ያወሳል።
በዚህም ታዳጊዎች ምኞታቸውንና ህልማቸውን ተከትሎ መራመድ አለባቸው። ለፈጠራ ስራ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች መመህራንን ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው መመራመር አለባቸው ይላል።
በቃልኪዳን አሳዬና ሄለን ወንድምነው
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter