ዶክተር ጽዮን ተስፋ በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ናቸው።
በራሳቸው ተነሳሽነት ደግሞ «አለርት ጉርሻ» በሚል በኦን ላይን ፕሮግራማቸው «ትኩረት ያልተሰጣቸው» በሚባሉ የበሽታ አይነቶች ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በዘፈቀደ ከምንንከባከባቸው አለያም ጭልጥ አድርገን ከምንረሳቸው የአካል ክፍሎችችን አንዱ መታወቂያና መለያችን የሆነው ፊታችን ነው።
የፊት ቆዳ ተጋላጭ ከመሆኑም በላይ ሲቻል ሳይንሳዊ እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ትኩረት የሚሻ የአካል ክፍል ነው።
ዶክተር ጽዮን እንደሚሉት በአለርት ሆስፒታል በተመላላሽ ህክምና ክፍል በብዛት የሚታከመው ታካሚ ወደ ሆስፒታሉ ብቅ የሚለው በቆዳ ህመም ምክንያት ነው።
የቆዳ ድርቀት፣ በፈንገስ፣ በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት ኢንፌክሽን፣ ብጉር፣ ለምጽ፣ የቆዳ ካንሰር፣ የጸጉርና የጥፍር በሽታዎች፤ ስጋደዌ እና የተዘነጉ የሚባሉ ሌሎች ህመሞችም ጭምር ናቸው።
እነዚህ በቆዳ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች መነሻ ምክንያታቸው የተለያየና በርካታ መሆኑን ዶክተር ጽዮን ይናገራሉ።
ዋነኛው መነሻው ግን በፈንገስ፣ በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ኢንፌክሽን ነው ይላሉ።
የራሳችን ሴሎች በራሳችን ላይ ጉዳት በሚያመጡበት ጊዜ እንደ ቆዳ ድርቀት እና ለምጽ ሊከሰት ይችላልም ይላሉ።
የአኗናር ዘይቤችን፣ የጸሀይ ብርሀን፣ የጸሀይ ጨረር፣ አለርጂ፣ የሆርሞን መዛባት እንዲሁም በተፈጥሮ የሚመጡ በከፍተኛ ጭንቀት የሚከሰቱ የቆዳ በሽታዎች እንዳሉም ይጠቅሳሉ።
አብዛኛው የቆዳ በሽታ የሚከሰተው በአንድ ምክንያት ሳይሆን የተለያዩ ምክንያቶች በአንድ ላይ በመደራረብ መሆኑን የሚያስረዱት ዶክተር ጽዮን፤ በተለይ የሴቶችን ፊት የሚያበላሹ እንደ ቡጉር፣ ማዲያት እና የፊት መቃጠል የሚባሉ በሽታው ምንነትና ህክምና ማወቅ ይገባል ይላሉ።
ብጉር በሴቶች ላይ በብዛት የሚታየው የቆዳ በሽታ በማለት ዶክተር ጽዮን የገለጹት፤ በተለይ በታዳጊ ሴቶች ላይ በብዛት የሚከሰተው ብጉር እና የቡጉር ጠባሳ ወይም ሁለቱም አንድ ላይ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።
ሁሉም አይነት ቡጉር ተመሳሳይ አይደለም። ስለዚህ በተመሳሳይ ህክምናም ሊታከም አይችልም። ብጉር ሶስት አይነት ደረጃ አለ። ይሄውም አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ደረጃ የሚባል ነው።
አነስተኛ የሚባለው የብጉር አይነት ፊት ላይ ብቻ የሚታይ፣ ትናንሽ ሽፍታ፣ እንዲሁም በጠቅላላው ከ30 በታች ቁጥር ያለው ሲሆን ይሄን አይነቱ በቀላሉ በቤት ውስጥ መታከም የሚችል መሆኑን ይጠቅሳሉ።
መካከለኛ የሚባለው የቡጉር አይነት ደግሞ ጥቁር ወይም ነጭ ሽፍታዎች፣ እብጠት፣ ከ30 እስከ 125 ቁጥር ያለው ሲሆን ይሄም ከፊት አልፎ ጀርባ ላይ ይገኛል።
የዚህ አይነት ብጉር በመታጠቢያ እና በሚቀባ መድሀኒት መታከም ያለበት በመሆኑ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።
ከፍተኛ ደረጃ የሚባለው መጠኑ ትላልቅና መግል የያዘ ሲሆን ከፊት ላይ አልፎም በሌሎች ቦታዎች ላይ ይገኛል።የጠለቀ የቆዳ ላይ ጠባሳንም የሚያስቀር ነው።
በቁጥርም ከ125 በላይ በመሆኑ የዚህ አይነቱ የቡጉር አይነት ከሚቀባው መድሀኒት በተጨማሪ የሚዋጥ መድሀኒት ሊሰጥ ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሆርሞን የሚከሰት የቡጉር አይነት መኖሩን ዶክተር ጽዮን ይጠቅሳሉ። ይሄ በመንጋጋ አካባቢ ከ30 ዓመት በላይ በሆነች ሴት ላይ ሲከሰት የተለየ ህክምና ያስፈልገዋል።
በቤት ውስጥ ብጉርን ለመቀነስ የሚደረገው ጥንቃቄ በማለት ዶክተር ጽዩን የነገሩን ደግሞ ፊትን በቀን አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ለሰስ ባለ ውሀ መታጠብ፣ ሀይለኛ የሚባሉ ሳሙናዎችን አለመጠቀም፣ በምትኩ ሳሙና ያልሆኑ የፊት ማጽጃዎችን እንደ ክሌንዘር አይነት መታጠቢያዎችን መጠቀም ተመራጭ መሆኑን ይመክራሉ።
ሌላው ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ሰውነት ላብ ሲኖረው መታጠብ ፣ፊትን ደጋግሞ አለመነካካት ፣ ፊትን ፈትጎ አለመታጠብ ፤ ብጉርን አለመነካካትና አለመጭመቅ ሲሆን ብጉርን ማፍረጥ የበለጠ ያባብሳል፤ቆዳን ሊጎዳና ወደ ኢንፌክሽን ሊያደርስ ይችላል።
ሰዎች ከልክ በላይ ብጉርን የመነካካትና የማፍረጥ ልምድ ይኖራቸዋል። ይሄ የታከከ ብጉር የሚባለው ነው። ቆዳቸው በሚመረመርበት ጊዜ ብጉር የላቸውም ነገር ግን ብጉሩን በማፍረጥ ጠባሳ እንዲቀር ሆናል። ይሄ አንዳንድ ጊዜ ከአእምሮ ህሙማን ጋር ይገናኛል።
በመስታወት ፊት ለፊት ብዙ ሰዓት ማሳለፍ ሰዎች ብጉርን ለማፍረጥ ያላቸውን ፍላጎት ይጨምራል። ስለዚህ ይሄ መጥፎ ልማድ ሊቀር የሚገባው መሆኑን ዶክተር ጽዮን ይገልጻሉ።
እንዲሁም ወዝ ላይ የተመሰረተ ሜካአፕ እና የቆዳ ማሳመሪያዎችን ማስወገድ ያስፈልጋል። ፊት ላይ የሚደረግ ሜካፕ ወዝ የማያመጣ፤ ብጉር የማያባብስ መሆን አለበት። ስለዚህ ሜካፕ መጠቀም የሚፈልግ ሰው በጣም በጥንቃቄ መሆን አለበት።
የውበት ማሳመሪያ ምርቶች ከወዝ (ኦይል) ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። «ይህም ሲባል የፊት ቅባት መጠቀም የለብንም ለማለት አይደለም።
ወዛም ቆዳ፣ ቡጉር ያለበት ሰው የሚጠቀመው የፊት ቅባት ለወዛም ፊት ተብለው የተሰሩትን መሆን አለበት። ወዛም ቆዳ ያለው ሰው ቅባት አይጠቀምም የሚለው የተሳሳተ ነው።
ወዝ አለው ማለት እርጥበት አለው ማለት አይደለም።ወዝ ያለውን ፊት ድርቀትም ሊያጠቃው ይችላል። ስለዚህ የፊት ቅባቶችን መጠቀም ይኖርብናል።
የፊት ቅባት መጠቀም ሰውነታችን ከልክ በላይ ወዝ እንዳያመርት ይረዳዋል። በተለይ ደግሞ የቡጉር መድሀኒቶችን በሚጠቀሙ ወቅት ፊትን ስለሚያደርቀው ሰውነታችን ብዙ ወዝ ያመርታል።ስለዚህ ድርቀትን ሊከላከል የሚችል ቅባት መጠቀም ያስፈልጋል።»በማለት ሙያዊ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ሌላው መረሳት የሌለበት ጉዳይ በማለት ዶክተር ጽዮን የነገሩን፤ የመኝታ ትራስ ጨርቅና የፊት ፎጣዎችን ማጽዳት ነው። የትራስ ጨርቆችን በየሳምንቱ ማጠብና መቀያየር እንዲሁም የፊት ማድረቂያ ፎጣዎችንም ጽዳት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
«ብዙ ጊዜ የትራስ ላይ ቅባት የተለያዩ ቆሻሻ (ባክቴሪያ) ይስባል። ይሄ ደግሞ ቡጉሩ ድጋሚ እንዲከሰት ያደርጋል። በመሆኑም ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግና ንጽህናን መጠበቅ ያስፈልጋል» ብለዋል።
ብጉርን ለማጥፋት ወይም ለመቀነስ በሚል ሰዎች የተሳሳተ መንገድን እንደሚከተሉ ዶክተር ጽዮን ይጠቅሳሉ። ይሄውም አንዳንድ ጊዜ ሎሚን ለብጉር ማጥፊያ ተጠቀሙ ሲባል ይሰማል። ሎሚ ግን ፊትን የበለጠ ያደርቃል። እንደነዚህ አይነት ነገሮችን ከባለሙያ ምክር ውጪ መጠቀም ተገቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላው ፊት በማበላሸት የሚታወቀው በሴቶች ላይ ጎልቶ የሚታየው የቆዳ ቀለም ለውጥ ሲሆን ይህም እንደ ማድያት ፣ የፊት ቃጠሎ የሚባለው ነው።የዚህ መነሻ ምክንያቱ ቅባቶች፣ የጸሀይ ብርሀን፣ የቆዳ ድርቀት እንዲሁም ከመድሀኒት ጋር ተያይዞ የሚመጣ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለምሳሌ ማዲያት የቆዳ ቀለም በሽታ ሲሆን ቡኒ ወይም ግራጫ ቡኒ የሚመስል በጉንጭ፣በአፍንጫ፣ በግንባር እና በላይኛው ከንፈር ላይ የሚወጣ ነው።
ማዲያት የሚነሳው በጸሀይ ብርሀን ወይም በሆርሞን መዛባት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ጽዮን ይናገራሉ። ለምሳሌ በእርግዝና እና የእርግዝና መከላከያ መድሀኒት በመውሰድ ወይም ደግሞ በዘር የሚመጣ አለ።
ዶክተር ጽዮን ማዲያትን መከላከያ ዋነኛው መንገድ በማለት የገለጹት ጸሀይን መከላከል ሲሆን ጸሀይንና የጸሀይ ጨረር ለመከላከል አንድ ላይ የተሰራ መድሀኒት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
የጸሀይ መከላከያ መድሀኒት ከመጠቀም ባለፈ ሰፋፊ ኮፍያ ማድረግ ፣ጃንጥላ መያዝ እንዲሁም ሀይለኛ ጸሀይ በሚኖርበት ወቅት ከቤት አለመውጣት የመሳሰሉት የመከላከያ መንገዶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ማድያትን ማከም እንደሚቻል ነገር ግን ጊዜ የሚወስድና ከፍተኛ ክትትልና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው ።ለህክምናውም ተቀምመው የሚቀቡ መድሀኒቶች ይታዘዛሉ።
ማዲያቱ እንዳይመላለስ ለማድረግ ሜንቴናንስ የሚባለው ህክምና በጣም ወሳኝ ነው።ይሄ በህክምና አንዴ ከተሻለ በኋላ መልሶ ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ ድጋሚ እንዳይነሳ የሚሰጠው መድሀኒት ተከታትሎ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።
ዶክተር ጽዩን እንደሚሉት፤ማዲያት ብዙ ጊዜ ፊት ላይ ይወጣል፤ በእርጉዝ ሴቶች ላይም የተለመደ ነው። ይሄ ማለት ግን እርጉዝ ያልሆኑት ላይ አይከሰትም ማለት አይደለም።
በተለይ ጸሀይ ላይ የሚውሉ ሰዎች ላይ በርከት ብሎ ይታያል።ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ወንዶችም ላይ ይታያል።
ማዲያት ሶስት አይነት ነው። ይሄውም የላይኛው ቆዳ ላይ፣ የውስጠኛው የቆዳ አካል ላይ ወይም ደግሞ በሁለቱም ላይ ሊከሰት ይችላል። የመጀመሪያ ቆዳ ላይ የሚወጣው በቀላሉ የሚታይ ነው።
ቀለሙም ደመቅ ያለ ቡኒ ሲሆን በህክምና ለመመለስም ቅርብ መሆኑን ያስረዳሉ። የውስጠኛው የቆዳ አካልን በሚያጠቃ ጊዜ ነጣ ያለ ቡኑ ወይም ወደ ግራጫ ቀለም የሚሆን ሲሆን፤ ለመድኃኒት የሚሰጠው ምላሽ ግን አነስተኛ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ የላይኛውንም የውስጠኛውንም የቆዳ ክፍል አንድ ላይ በሚጎዳበት ጊዜ ምላሹም ግማሽ በግማሽ እንደሚሆን ይናገራሉ።
ዶክተር ጽዮን እንዳሉት፤ የማድያት ህክምና በማጉያ መሳሪያ በባለሙያ የሚታይ ይሆናል። ከሌሎች አይነት በሽታዎች ( የቆዳ ጥቁረቶች) የተለየ መሆኑን ሀኪሞች ይለዩታል።
ህክምናው በዋነኛነት ግን ከጸሀይ ፊትን መከላከል ሲሆን ይሄ ደግሞ እድሜ ልክ የጸሀይ መከላከያን መጠቀም ነው።
በቤት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ መስታወት አጠገብ አለመሆን ተመራጭ ነው። ጸሀይ የመከላከል አቅሙ 50+ የሆነ ሰንስክሪን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ። ከሆርሞን ጋር የተገናኘ ከሆነም ያንን ያመጣውን መድሀኒት ማቆም ወይም መቀየር ይገባል።
የማዲያት ህክምና የተለያየ ሲሆን በባለሙያ የሚቀመም ፣ ታሽጎ የሚሸጥ እና የሚዋጥ መድሀኒት መኖሩን ይናገራሉ። ይሄ የሚሆነው በሀኪም ታዞና አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ መሆን እንዳለበትም ይጠቅሳሉ።
የማዲያት መንስኤው የተለያየና ውስብስብ ሲሆን ዋናው ነገር ግን በጸሀይ ጉዳት የሚመጣ ነው። በዘር የሚመጣም ይኖራል።
በቤተሰብ ደረጃ ካለ 60 በመቶ በማዲያት የመጠቃት አጋጣሚ ይኖራል። አንዳንድ ጊዜ ከስጋደዌ በሽታዎች ጋርም የተገናኘ ሊሆን ይችላል። ከሌሎች አዳዲስ መድሀኒቶች ፣ የካንሰር መድሀኒቶች ጋር ተያይዞም የመከሰት አጋጣሚው መኖሩን አስረድተዋል።
«የፊት መቃጠል» የሚባለውም ሌላው በሴቶች ፊት ላይ ጎልቶ የሚታየው በሽታ ነው። ይሄ በሽታ የሚመጣው በፋርማሲ ውስጥ ወይም በሱቅ ደረጃ እየተሸጡ በሚገኙ «ፊት ማሳመሪያ» የሚባሉትን ፤ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የተዘጋጁ መድሀኒቶችን ወይም ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ የመዋቢያ ምርቶችን በመጠቀም የሚመጣ ነው።
በተለይ ደግሞ ለፊት ጥራት እየተባለ የሚወሰድ መድሃኒት ዘላቂ የሆነ ጉዳት እንደሚያስከትል ይገልጻሉ።
የተቃጠለ ፊት ምልክቱ ፊት ቀይ ቀይ የመሆን ፣ ቀጫጭን ደም ስር የማውጣት፣የመቀንቀን በተለይ ጸሀይ ላይ በሚቆዩበት ጊዜ የሚያቃጥል ስሜት ያስከትላል።
ጸሀይ ላይ በሚኮንበት ሰዓት በጣም የማቃጠል ስሜት ይኖረዋል። ይሄንን ለመከላከል የሚቻለው ከውጪ የሚመጣን መድሀኒቶች በማቆም ብቻ ነው።
ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ለሰው ልጆች ጤና መቃወስ ምክንያት የሆኑ ምርቶች ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባና ህብረተሰቡም እንዳይጠቀማቸው ተገቢውን ትምህርት መስጠት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ «ስቶይሪድ » የሚባል የቆዳ መድኃኒትን ካለ ሀኪም ትእዛዝ መጠቀም ትርፉ ጉዳት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
« እነዚህ መድሀኒቶች የተሰሩትም ለፊት ተብሎ አይደለም። ማንኛውንም መድሀኒት ከሀኪም ጋር ምክክር ሳይደረግ ፊት ያጠራል ስለተባለ ብቻ መጠቀም ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ዘላቂ ችግር ያስከትላል።
ይሄ ፊትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳና ዘላቂ የሆነ የፊት መሳሳት የሚያስከትል ነው» ሲሉ የተናገሩት አጽንኦት ሰጥተው ነው።
Via በአልማዝ አያሌው GazettePlus
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter