የፌደራል ፖሊስ ባለፉት 7 ዓመታት ባደረገው ሪፎርም በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የተደራጀ፤ ፖሊሳዊ ተልእኮን መወጣት የሚችል ጠንካራ ተቋም መሆን ችሏል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ።
116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምሥረታ ቀን የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመርኃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ እንደ ሀገር የሚያስመሰግኑ ስራዎችን ሰርቷል ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የ24 ሰዓታት ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ያወሱት ኮሚሽነሩ፤ ተቋሙ ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚችል ተቋም መሆን ችሏል ሲሉም ገልፀዋል።
ተቋማዊ የወንጀል ምርመራ የማጣራት አቅም ማሳደግ በመቻሉ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ መሆን መቻሉንም ጠቁመዋል።
የፌደራል ፖሊስ ለሀገሪቱ ሁለንታናዊ እድገት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፤ ማንኛውም ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ተቋም መሆን መቻሉን ገልፀዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለፖሊስ እያደረገ ላለው ድጋፍም ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።
በላሉ ኢታላ etv
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter