“የህክምና አገልግሎት ተቋርጦ ወይንም ተስተጓጉሎ ጥያቄ ማቅረብ የጤና ተቋማቱም ሆነ ጤና ሙያተኛው ማዕከል የሆኑትን ታካሚዎች ለሞት ለእንግልት የሚዳርግ በመሆኑ የምንቀበለው አይደለም ” የኢትዮስፕየ ነርሶች ማህበር አስታወቀ። ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን በማለክተ መፍትሄ እንዲፈለግና የታሰሩ እንዲፈቱ አሳስቧል።
ነርሶችም ሆኑ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ችግሮችን ለመፍታት በሚዘጋጁ መደረኮች ተሳታፊ በመሆን ለመፍትሄ እንዲተባበሩ ያመለከተው ማህበሩ የባለሙያዎቹን ችግርም አጽንዖት ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር ፥ የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በገለጸበት መግለጫው የነርስነትን ቅድሚያ ምህላ መርህ አመላክቷል። በሽተኞችን ለሞትና ለእንግልት የሚዳርግ የስራ ማቆም አድማን እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል። የጤና ሚኒስቴር የህክምና ዘርፍ በህግ አድማ ማድረግ እንደማይችል የተደነገገ መሆኑን ጠቅሶ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል።
ማህበሩ በመግለጫው ጥያቄ ስለጠየቁ የታሰሩ ባለሙያዎች እንዲፈቱ እንዲሁም ዛቻና ማስፈራሪያዎች እንዲቆሙ ተማጽኗል። ማህበሩ ለሚዲያዎች በላከው መግለጫ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ አንስቷል።
ማህበሩ በጤና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉት ጥያቄዎች ማለትም የተቋማት ግብዓት እጥረት መኖር፣ የደመወዝ ማነስ፣ የጥቅማጥቅም አለመኖር፣ የትምህርት እድል እና የደረጃ እድገት አለማግኘት ፣የስራ ቦታ ደህንነት አለማግኘት … የመሳሰሉትን አስታውሷል። መፍትሄ እንዲበጅም ጥሪ አቅርቧል።

ለረዥም ጊዜያት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለውይይት ሲቀርቡ እና አጀንዳ ሆነው የቆዩ መሆናቸውን መግለጫው ገልጿል። ስራቸውን ያቆሙ ባስቸኳይ ወደ ስራቸው እንዲመለሱም ሙያዊ ማሳሰቢያ አቅርቧል። ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑም ሁኔታው የመንግስትን ትኩረት እንዲያገኝ ጥሪ አቅርቧል።
” የህክምና አገልግሎት ተቋርጦ ወይንም ተስተጓጉሎ ጥያቄ ማቅረብ የጤና ተቋማቱም ሆነ ጤና ሙያተኛው ማዕከል የሆኑትን ታካሚዎች ለሞት ለእንግልት የሚዳርግ በመሆኑ የምንቀበለው አይደለም ” ያለው ማህበሩ አክሎም ” ስራዎቹ በአስቸኳይ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ሙያተኞቹ፣ የተቋማት ሃላፊዎችም ሆነ ጤና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ውይይት እና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ” ሲል ጠይቋል።
” ጥያቄ ጠይቃችኋል ” ወይም ” አስተባብራችኋል ” በሚል ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እንዲፈቱ ፤ በተቋማትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ዛቻና ማስፈራሪያዎችም እንዲቀሙ ጠይቋል።
ጥያቄ ያላቸው ነርሶችም ሆነ ሌሎች ሙያተኞች ለውይይት በሚዘጋጁ መድረኮች በመገኘት ጥያቄአቸውን እንዲያቀርቡ እና ለመፍትሄ ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቋል።