ኦሮሚያ ባንክ ያለ ምንም የዋስትና ማስያዣ ብድር መስጠት የሚያስችል ሚልኪ የተሰኘ አዲስ ዲጅታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ ስራ ላይ ማዋሉን ግንቦት 20/2017 ዓ.ም በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል በተከናወነ የማብሰሪያ ስነ ስርዓት ተገልጿል።
ኦሮሚያ ባንክ ከኳንተም ቴክኖሎጂ አ.ማ ጋር በመሆን ያበለፀገዉን ሚልኪ የተሰኘ ዲጂታል የብድር አገልግሎት መተግበሪያ፤ በቀላል መልኩ ብድርን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ የዲጂታል አገልግሎት መሆኑ ተነግሯል።
ይህ ዲጅታል የብድር አገልግሎት የባንኩን የዲጅታል ባንኪንግ ተደራሽነት ከማስፋቱም በተጨማሪ የፋይናንስ አካታችነትን በተግባር በማረጋገጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለያዘችዉ የዲጅታይዜሽን እቅድ መሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲል የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን ተናግሯል።
ሚልኪ ዲጂታል የብድር አገልግሎት ከሚሰጣቸዉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች መካከል በወርሀዊ ደመወዝ ለሚተዳደሩ፣ የደሞዝ መዳረሻ ብድርን ጨምሮ የብድር አቅርቦት አስፈልጓቸው በዋስትና ማስያዢያ ምክንያት አገልግሎቱን ላጡ የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ዋስትና ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ አመቻችቷል፡፡
ሚልኪ ዲጅታል የብድር አገልግሎት ከሚሰጣቸዉ ግልጋሎቶች መካከል ሚልኪ ፉርቱ የተሰኘዉ አገልግሎት በዕለት ተዕለት ገቢ የሚተዳደሩና እና ንግዳቸዉን ለማሳደግ የብድር አገልግሎት ለሚፈልጉ ዜጎች እንዲሁም ስራ ፈጣሪዎች የማስያዣ ዋስትና ማቅረብ ሳይጠበቅባቸዉ ብድር ማግኘት የሚያስችል አሰራርም ዘርግቷል፡፡
በተለየ መልኩ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ሚልኪ ሀርሜ የተሰኘዉ የብደር አገልግሎት ከሌሎች የብድር አቅራቢዎች በተለየ አነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ብቻ በማስከፈል ያለምንም ማስያዣ ብድር በመስጠት ለባርካታ የሀገራችን ሴቶች አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦት ሆኖ መጥቷል፡፡
በተጨማሪ የጥቃቅንና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር፤ ለሞባይል ፣ ለኤሌክትሮኒክስ እና የቤት ቁሳቁስ መግዣ ብድርእንዲሁም ሌሎች አጓጊ ጥቅሎችን በዉስጡ አካቷል፡፡
ሚልኪ ዲጅታል የብድር አገልግሎትን ከሌሎች መሰል አገልግሎት ከሚሰጡ መተግበሪያዎች ለየት የሚያደረግዉ የነዳጅ ግብይትን ለማዘመን የተያዘዉን እቅድ ለማሳካት ፤ ነዳጅ ቀጂዎች በሂሳባቸዉ በቂ ገንዘብ ባይኖራቸዉም እንኳ፣ በሚልኪ ፈጣን የብድር አገልግሎት በመጠቀም ነዳጅ መቅዳት የሚያስችል አሰራር አካቷል።
ደንበኞች ወደ ባንኩ በአካል መምጠትም ሆነ የብድር ዋስትና ማስያዣ ማቅረብ ሳይጠበቅባቸው በእጅ ስልካቸዉ ላይ በሚያወርዱት ሚልኪ መተግበሪያ ላይ በመመዝገብ ብቻ በሴኮንዶች ዉስጥ ፈጣን የብድር አግልግሎት ማግኘት ይችላሉ።