በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 10/2017 ዓ.ም ልዩ ልዩ ድርጂታዊ ሀገራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።
ተቋማዊ አሰራርን በተመለከተ
ተቋማዊ አሰራር ስርዓትን ለማጠናከር በቀረቡ እቅዶች ዙሪያ የተወያየ ሲሆን በተለይም የፖርቲውን ስትራቴጂክ ግቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከምሁራን፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና ከአጋር ተቋማት ጋር ውይይቶችን እና ምክክሮችን ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር መርሃግብር ወጥቶ ተግባራዊ እንዲደረግ እና ከጉባዔ በኋላ በተከናወኑ የፖለቲካ ስራዎች ዙሪያ ተወያይቶ ለአመራሩና አባላቱ የስራ ስምሪቶችን ሰጥቷል።
በአማራ ክልል ውስጥ ያለውን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ
በአማራ ክልል ውስጥ ባለው የጸጥታ ችግር የተነሳ የአማራ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ የመከራ ቀንበር ተጭኖበት ሞትን እና ጉስቁልናን እንዲላመድ፤ የህይወትና የንብረት ዋስትና እንዲያጣ፣ አርሶ፣ ነግዶ እና በአጠቃላይ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ሰርቶ እንዳይኖር መደረጉ ሊሰመርበት ይገባል። የአማራ ህፃናትና ታዳጊ ልጆች የመማር መብታቸው ተገፎ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል፤ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እና የልማት እንቅስዋሴዎቹ በከፍተኛ ደረጃ ተገድበዋል።
በተለይ መሰረተ ልማቶቹ በየእለቱ እየፈረሱና እየወደሙ ይገኛሉ። በዚህም የአማራ ህዝብ አስቀድሞ ጥያቄ ያነሳባቸው የነበሩ በህይወት የመኖር፣ የአካልና የንብረት ከለላ የማግኘት እንዲሁም ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዳያገኙ፣ የትግል ሂደቱ እንዲወሳሰብ እና የተጨማሪና ተከታታይ ጉዳት ሰለባ እንዲሆን ተደርጓል።
በክልሉ ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ከስጋት ነፃ ሆነው ስራቸውን እንዳያከናውኑ በየእለቱ ለእገታና እንግልት ተዳርገዋል። ከሁሉም በላይ የአማራ ህዝብ ነባር እሴቶች በመጣስ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ላይ ያልተገራና ነውረኛ ወከባ እየተፈፀመ ይገኛል። እነዚህ ዘመን እና ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ የአማራ ህዝብ ማህበራዊ እሴቶች ላይ የተከፈተው የስም ማጥፋት ፕሮፖጋንዳ እና አካላዊ ጥቃት በህዝባችን የማህበረ-ፖለቲካ ውቅር ላይ ምናልባትም ለረጂም ጊዜ የሚቆይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊፈጥር የሚችል ተግዳሮት ነው።
በተለይም የአማራ ተወላጅ በሆኑ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ለህዝብ በወገኑ ፖለቲከኞች ላይ የሚፈጸሙ አጉል ድፍረት የተሞላባቸው ፍረጃዎች እና በስብዕና ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የአማራን ህዝብ ነባር እሴቶችና የወደፊት ተስፋ ለማጨለም የሚደረግ ዝቅ ሲል አላዋቂና ኃላፊነት የጎደለው ከፍ ሲል የእኩይና የጠላትነት ተግባር በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል::
በመሰረቱ ባለፉት ጥቂት አመታት እንደታዘብነው፤ በሀገር ውስጥና በተለይም መሠረታቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ጽንፈኛ አመለካከትን ያነገቡ ሀይሎች በጥምረት ህዝባችንን ትኩረት እንዳይኖረውና እረፍት እንዳያገኝ በማያባራ አጀንዳ ውስጥ ከዚህና ከዚያ ሲወዘውዙት ቆይተዋል። የነዚህ ሀይሎች ጥምረትም ምንም እንኳ አበክሮ በአማራ ህዝብ ስም የሚምል ቢሆንም ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ባልዘለለ የአማራን ህዝብ ተለዋዋጭ የጠላት ከጀንዳ ግብዓት ለማድረግ አስቻይ ሁኔታን ሲፈጥሩ ቆይተዋል። ይህም ሁኔታ መራር ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም ዘግይቶ ቢሆን ሁሉም የተረዳው ሃቅ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ አካላት አብዛኞቹ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ስም በማጥፋት፣ በማስፈራራት እና በማጥቃት ከአማራ ህዝብ ባህል፣ ታሪክና ስነልቦና እንዲሁም ከዴሞክራሲ እሳቤ ተቃራኒ የአፈና ተግባራትን ይፈፅማሉ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ መድረኩን በወከባ እና በሃይል በተናጠል በመቆጣጠር “የተለየ ሃሳብ” እንዳይቀርብ የሚንቀሳቀሱ አካላት በመሆናቸው በሂደት “የተሻለ ሃሳብ” ያመጣሉ ተብሎ አይገመትም።
የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ለረጂም ዘመን የተደረገውን ዘርፈ ብዙ ትግል ከማክሸፍ ባለፈ ተጨማሪ ጉዳት እና ጥያቄዎችን ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በዚህ መሰረት ከላይ የተገለፀው እና መሰል የቀውስ አዙሪቶች አሁን ላይ ከሚፈጥሩት አሉታዊ ጫና እና ጉዳት በተጨማሪ ዳፋቸው ለመጭው ዘመን የሚተርፍ መሆኑን አብን ይገነዘባል።
በሌላ በኩል የህዝባችን ጠላቶች በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ክልሉን ዘላቂ ለሆነ የሰብአዊና ማህበረ-ኢኮኖሚ ቀውስ ለመዳረግ አበክረው እየሰሩ መሆኑ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። በተለይ የአማራን ህዝብ ህይወት እና ሃብት የቡድን ፍላጎት ግብአት ለማድረግ አበክሮ የሚሰራው ጠባብ ሃይል የአማራን ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሞችና አካባቢዎች በጓድነት ለመረጠው የአማራ ጠላት በመታያነት አሳልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ያለንን ስጋት መግለፅ እንፈልጋለን።
በመሆኑም ህዝባችን ከዚህ የቀውስ አዙሪት እንዲላቀቅ እንሰራለን ስንል አሁን ከሚደረገው እንቅስቃሴው ባህሪ እና አብን ከሚያራምዳቸው መሰረታዊ መርሆዎች አንፃር ብቻ በመቃኘት ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒ ያለውን የጥፋት አሰላለፍ በመገምገም እና በመጨረሻ የሚያስከትለውን መዘዝ በመስጋት ነው። ህዝባችን የተነጠቀው ሰላም ይመለስለት ዘንድ አብን ይበጃሉ ያላቸውን የሰላም አማራጮች የሚያመላክቱ ጥሪዎችን እንደሚከተለው ያቀርባል።
ለኢፌዴሪ መንግስት
የኢፌዴሪ መንግስት በአማራ ክልልና በህዝቡ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በውል በመረዳት እና በሆደ-ሰፊነት ጭምር ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ረጅም ርቀት በመጏዝ እንዲሰራ ሁሉንም አማራጮች እንዲጠቀም እና የእንደራሴዎች የሰላም አዋጅ እስከማወጅ የደረሰ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን። በተጨማሪም የህዝባችን ጥያቄዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እና የተጀመሩ ጥረቶችን በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ፖለቲካዊ መረጋጋት የማስፈን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እናሳስባለን።
ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ የሰላም ስራዎች ላይ ማህበረሰቡን እስከታች ድረስ የማወያየት ጅምር ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን እየገለፅን ትላንት መንግስታዊ ኃላፊነቱን ባለመወጣት ህዝቡን አሁን ወዳለበት አዘቅት እንደከተተው በማመን፣ የትላንቱን ስህተት ላለመድገም እና ለመካስ በመታደስ እና ችግሮቹን ከውስጥ ወደወጭ በመመልከት የተጀማመሩ ስትራቴጅካዊ የመፍትሄ ርምጃዎች ላይ እንዲያተኮር ጥሪ እናስተላልፋለን ::
ለመላው የአማራ ህዝብ
ከአማራ ህዝብ የምንግዜም ጠላቶች የአማራ ክልልን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በህዝባችን ላይ የማይሽር ሁለንተናዊ ጠባሳ ለመፍጠር ከሚሰሩ የፍላጎት እና የተግባር ጥምረት ያላቸው አካላት የአማራ ህዝብ የህልውና አደጋዎች ስለሆኑ በፅናት እንዲታገላቸው ጥሪ እናቀርባለን። እንዲሁም ህዝባችን አማራዊ የሞራል /የግብረ-ገብነት/ እሴትን፣ የግልግል ስርዓትን፣ የሽምግልና እሴቶችን ወዘተ በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለመመለስ አይተኬ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ እናስተላልፋለን::
በትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ለምትገኙ እህቶችና ወንድሞች
እንደሚታወቀው ህዝባችን መሸከም ከማይችለው በላይ የሰብአዊ እና የማህበረ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እየማሰነ ይገኛል። ስለሆነም በዚህ ወቅት የሰላም አማራጭን ተቀብሎ ክልሉን ከከፋ ቀውስ አዙሪት ማላቀቅ ለአማራ ህዝብ እጅግ የከበረ ዋጋ የማይተመንለት ስጦታ እንደማበርከት የሚቆጠር በመሆኑ ሁሉም የነፍጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ቡድኖች ወደ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲመጡ እናሳስባለን::
በቅርቡ የሰላም አማራጭን በመቀበላቸው ሊደርስ የሚችልን ተጨማሪ ቀውስ እንዲቀር ያደረጉ የታጠቁ ኃይሎችን ውሳኔ እያበረታታን ሌሎች ቡድኖችም ይህን መሰል አዎንታዊ ውሳኔዎች በአፋጣኝ በማሳለፍ ከሀሳብ እና ቡድናዊ ቅንጅት አኳያ አስተማሪ የሆነ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ባለ ተሞክሮነት ጭምር ሊዘከር የሚችል ስልጡን የሰላም ድርድር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሚዲያ ተቋማት እንዲሁም ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች እና የሙያ ማህበራት
አብን የኃይል አማራጭን እንደአዋጭ የትግል ስልት አድርጎ ከሚወስድ የፖለቲካ ባህል አዙሪት መውጣት የሚያስችሉ ሁለገብ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ይህ የድርጅታችን ህዝቡን ከቀውስ አዙሪት እንዲወጣ የሚያደርገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው የመላው ኢትዮጵያዊያን፣ የዲያስፖራ ማህበረሰብ እና የልዩ ልዩ ሀገራዊና ብሄራዊ አደረጃጀቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑን በፅኑ ያምናል። በመሆኑም ህዝባችን ወደ ተሟላ ሰላም በሚመለስበት ሁኔታ ላይ ቁርጠኛ ድጋፍ እና ትብብር እንድታደርጉ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
ግንቦት 12፣ 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
TIPS
ሱዳን ያለባትን የኤሌክትሪክ እዳ ለመፍፈል 1 ዓመት ከ6 ወር እንዲሰጣት ጥያቄ አቀረበች
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታላቅ የምረቃ ሥነስርዓት ፤ የሁለተኛው ግድብና ዘመናዊ ከተማ መሰረት ይጣላል፤
በተለይ ወንዶች ላይ የሚከሰተውን የፕሮስቴት ካንሰርን በተመለከተ ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች
የአፍ ምሬት ከምን ይመጣል?
በደህንነት ስጋት ለጊዜው ማንኛውም የዳኝነት አገልግሎት መስጠት አቁመናል ” መቐለ ፍርድ ቤት
” የቅድመ ክፍያ መጠን ከ5 ሺህ ወደ 50 ሺህ ዶላር ከፍ ተደርጓል ” ብሔራዊ ባንክ
ይድረስ ለክቡር ገና…. ስለወርቃማ አክሲዮንና ዲጅታል ሉዓላዊነት የራሴን ምልከታ
የውጭ ዜጎችን የመሬት ባለይዞታ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ነገ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል
ሞኝን እባብ ሁለቴ ነደፈው – አንዴ ሳያይ፣ ሁለተኛ ደግሞ ሲያሳይ <br>(ክቡር ገና)
አሌክሳንደር ኢሳክ ከኒውካስል ሊለቅ ይችላል ተባለ
ኢዜማ የህክምና ባለሙያዎችና መንግስትን መከረ፤ ሰላማዊና ሕጋዊ የመብት ጥያቄ ብቻ
የሻዕቢያና የወያኔ ሶስት የቢሆን ዕቅዶችና ወቅታዊ ግምገማዎች፤ ያኮረፈው አርሚ ስጋት ሆኗል
የውጭ ባንኮች 2018 አጋማሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ
“ሾልኮ ወጣ” የተባለው የዝርፊያ ሰነድና ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳር የቀረበ ምላሽ
የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር ታካሚዎች ለሞትና እንግልት እንዳይዳረጉ አስጠነቀቀ