በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚደርሱ ጥቃቶችን ተከትሎ የባህር ትራንስፖርት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ተመድ አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደተናገሩት፤ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በንግድ መርከቦች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ እያወኩ ነው።
በዚህም ለዓለም አቀፍ ደህንነት ጠቃሚ የሆነው የባህር ትራንስፖርት ስጋት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
የባህር ደኅንነት ከሌለ ዓለም አቀፋዊ ደኅንነት ሊኖር አይችልም ያሉት ጉቴሬዝ፤ በአሁኑ ወቅት የባህር ቦታዎች ከተለያዩ አካላት ስጋቶች እና ድንገተኛ አደጋዎች ተደቅኖባቸው ስጋት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተለያዩ ድንበሮች ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶች፣ በባህር ላይ የተፈጥሮ ሀብቶች መሟጠጥ፣ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶችን እያባባሰ የፉክክር፣ የግጭት እና የወንጀል ድግግሞሽን እየተጨረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ በ2025 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተመዘገበው የባህር ላይ ዘረፋ እና የታጠቁ ዘረፋዎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ገልፀዋል።
የአለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት (አይኤምኦ) በወጣው ዘገባ፣ የባህር ላይ ዘረፋና ውንብድና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል።
በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ሁቲዎች በንግድ መርከቦች ላይ ያደረሱት ጥቃት ዓለም አቀፉን የንግድ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል በአካባቢው ውጥረቱ እንዲጨምር ማድረጉ ተገልጿል።
የኤደን ባህረ ሰላጤ እና የሜዲትራኒያን ባህር ለስደተኞች ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላማዊ፣ አስተማማኝ የባህር ዳርቻዎች እንዲኖሩ በማረጋገጥ ረገድ ሀገራትን መደገፉን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ዋና ፀሐፊው፤ የባህር መዳረሻዎችን ሰላም ለመጠበቅ ሀገራት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል ሲል አነዶሉ ዘግቧል።
ጋዜጣ ፕላስ
ኢትዮ ሪቪው ኦንላይን - በሰው ልጆች ዕልቂት መነገድ ይቁም!