ሰሞኑን ከሚሰማው የሐኪሞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጎን ለጎን የተሰማው ዜና ሰፊ አድናቆት እየተቸረው ነው። ዶክተር ብሩክ ወይሻ ሙሽራነቱን አቋርጦ ነብስ ታድጓል፡፡
” ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን ለአከባቢውም ብቸኛ ስፔሻሊስት ስለነበርኩ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም ” – የራሱን ሰርግ አቋርጦ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ሕይወት የታደገዉ ዶክተር
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን በሌ ከተማ አስተዳደር የበሌ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ብሩክ ወይሻ የራሱን ሰርግ አቋርጦ ቀዶ ሕክምና በማድረግ የሰው ህይወትን መታደጉን ተከትሎ በርካቶች አድናቆትን እየቸሩት ይገኛሉ።
ዶክተር ብሩክ ትላንት በወላይታ ሶዶ ከተማ በሰርጉ ፕሮግራም ላይ እያለ ከሆስፒታል ተደዉሎለት አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገዉ ታማሚ እንዳለና ሪፈር ለማድረግም ታካሚዉ የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው ይነገረዋል።
ይህን በሰማ ጊዜም ወደ ሆስፒታሉ ሲበር ማቅናቱን ተናግሯል።
” ‘ በሰርግህ ዕለት የትም አትወጣም ‘ ብለዉ በጥብቅ የከለከሉኝ የቤተሰብ አባላት ነበሩ ” ያለን ዶክተር ብሩክ ” ነገር ግን ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን ለበሌና አከባቢዋም ብቸኛዉ ስፔሻሊስት እኔ ስለሆንኩ በሆስታሉ ተገኝቼ ቀዶ ሕክምናዉን በተሳካ ሁኔታ አድርጊያለዉ ” ብሏል።
” ሕመሙ ጊዜ የማይሰጥና አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገዉ ስለነበር ሙያዊ ግዴታዬን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአግባቡ ተወጥቻለሁ ” ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ዶክተር ብሩክ ወይሻ በአሁኑ ወቅት ታካሚዉ ቀጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተናግሮ ” በእኔ ምክንያት የታማሚዉ ሕይወት ቢያልፍ የሕይወት ዘመን ፀፀጥ ነበር የሚሆንብኝ ” ሲል ገልጿል።
የበሌ ከተማ አስተዳደር ከወላይታ ሶዶ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደ ዳዉሮ ጂማ መስመር የሚትገኝ ከተማ ናት።