የትህነግ ቃል አቀባይ በመሆን ጦርነቱን በፕሮፓጋንዳ ሲያቀጣጥሉት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ የሆነው ሁሉ እረፍት እየነሳቸው ያሉ ይመስላል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ሲነገሩ የነበሩ ቁልፍ ሚስጢሮችን ሲከላከሉና ሲያመክኑ ቆይተው አሁን ላይ ራሳቸው ይፋ እያደረጉ ነው።
ከትግራይ ጊዜያዊ መንበራቸው በአመጽና በጠመንጃ ኃይል እንዲወገዱ የተደረጉት አቶ ጌታቸው ውስን ያሉዋቸውን ጄነራሎች ስም እየጠቀሱና በጥቅሉ ተጋባራቸው “የብረሃን ስራ በብርሃን ነው” እንደተባሉ ጠሰው ይፋ አድርገዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በውጊያ ወቅት ያፈገፈጉ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ዘጠና ሜትር ረቀት ላይ ሆነው በሚያዋጉ ጄነራሎች መረሸናቸውን መስክረዋል፡፡ “ውሸት በቃኝ” በማለት የሚያውቁትን እየዘረገፉ ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህን የሚያደርጉ ውስን የጦር መኮንኖችና የፖለቲካ አመራሮች ተቧድነው በወርቅ ዝርፊያ ላይ መሰማራታቸውን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ትህነኝ ወንጀለኛ ድርጅት እንደሆነ አመልክተዋል።
በትግራይ ያለው ህገወጥ የወርቅ ንግድ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኃላ የጀመረ ሳይሆን በጦርነቱ ጊዜም ሳይቀር ሲሰራ የነበረ ወንጀል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ዛሬ ድረስ ይኸው ዘረፋ አሁንም በቡድን መቀጠሉን አስታወቀዋል።
አቶ ጌታቸው፤ ብዙ ሰው የወርቅ ንግድ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈራረምን በኃላ የጀመረ እንደሚመስለው አመልክተው ሃቁን ገልጠዋል። ጦርነቱም እየተካሄደ፣ የትግራይ ልጆች እየተማገዱ የወርቅ ዝርፊያውና ንግዱ ይካሄድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በዚህና በበርካታ ምክንያቶች “እኔ የማምንበትን ትግል ነው ያካሄድኩት ብዬ አምናለሁ” ያሉት አቶ ጌታቸው ይህን ሲሉ ዛሬ ድረስ አማራና አፋር ክልልን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የወረረው ፓሪታቸው የፈጸመውን ግፍ ይሁን ሌላ ጠያቂው አልጠየቃቸውም።
“… በማምንበት ትግል ውስጥ የትግራይን ህዝብ አጀንዳ ይዘው የታገሉ ብዙ የጦር መኮንኖች አሉ፡፡ ለሰሩት ስራ ያለኝ ክብር በፍጹም አይቀንስም፡፡ ግን ደግሞ ገና ገና ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ይበላ በነበረበት ወቅት ሳይቀር ምሽግ ለመቆፈር ብለን የወሰድነው ኤክስካቫተር ወርቅ ለመልቀም ይጠቀሙበት የነበሩ አዛዦችም ነበሩ” ሲሉ ሁለት መልክ ያለውን አመራር ተግባር ለይተው አሳይተዋል።
“ሲዋሹ በጣም ነው የሚገርመኝ” ያሉት አቶ ጌታቸው “እኔ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል እስካሁን የታገስኩትም ይበቃኛል” ከሚል እሳቤና እምነት የሚያውቁትንና የደበቁትን ሚስጢር ለሕዝብ መግለጻቸውን አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸው “የኤርትራን ሰራዊት እናፍርሰው” በሚል ዓላማ ዘመቻ የጀመረና ዘመቻውን የሚመራው አመራር ሰዎችን እያፈነ ገንዘብ ሲሰበስብ እንደነበር ተናግረዋል። የሰው ልጅ ይሸጡ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ይህን ሲሉ የትህነኝ ቁንጮዎች ወነጀለኛነት ደጋግመው በመግለጽ ነው።
የሰው ልጅ ሽያጭን ሲያስረዱ “ሰው ሲሸጡ የሚኖሩ ሰዎች አሉ” ቀጥለው የሽያጩን ምደባ ሲገልጹ የሚሸጠው ሰው ኤርትራዊ ከሆነ ወይም ኤርትራዊ የሚሸጥ ከሆነ “ንብረት ” በሚል ስያሜ ይጠራል። እናም ሽያጩ መከናወኑን ለመለየት “ንብረቱ ወርዷል ወይ ? ይባላል።
አቶ ጌታቸው የድርጅታቸውን ውንብድና ሲገልጹ ምስኪኖች ይታፈኑና ቤርተሰቦቻቸው ውጭ ሀገር ያሉት ክፍያ በውጭ አገር አገር ባሉዋቸው ሰዎች አማካይነት ገቢ እንዲደረግላቸው ይደረጋል፡፡ ይህ አገር ሲመራ የነበረ የማፍያ ቡድን በእያንዳንዱ ሰው በትንሹ አራት ሺህ ዶላር ነው የሚጠይቀው።
ለምሳሌ ሲያስረዱ ሃያ ሰው ካፈኑ ሰማኒያ ሺህ ዶላር ያገኛሉ፤ በዚህ የውጭ አካውንት ከፍተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየሸጡ፣ እያገቱ ገንዘብ ከሚሰበስቡት መካከል ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ይህ ተግባር መጀመሪያ በኤርትራውያን መጀመሩን ከዛም ወደ ትግራይ ተወላጆች መዞሩን አስታውቀዋል። የትህነግና ሻዕቢያ ፕሮፓጋንዲስቶች ይህን ጉድ ተኝተውበት መኖራቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
እዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ተደርጎ አመራሮቹ ለህግ እንዲቀርቡ ሙከራ ቢደረግም ማቅረብ እንዳልተቻለና ጥናቱም ከተሰራ ሁለት ዓመት እንደሆነው ጠቁመዋል። አቶ ጌታቸው “ይሄን የሚመራ የመረጃ መምሪያ ኃላፊ እርምጃ እንዲወሰድበት ወይ ከስራ እንዲነሳ ብለን ወስነን ስናበቃ ለማስፈጸም ኃላፊነት የሚሰጣቸው የፀጥታ አመራሮች አላስፈጸሙም” ማለታቸውን ይፋ አድርገዋል።
የፀጥታ አመራሮች በባህሪያቸው ጥፋት ያጠፋውም ያላጠፋውም የመተጋገዝ ባህሪ እንዳላቸው አቶ ጌታቸው በንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በወርቅ ንግድ ውስጥ ስለተነከሩ አመራሮች ዝርዝር አብራርተዋል።
“ወርቅ ንግድ ውስጥ የገባ ለትግራይ ነጻነት እስከመጨረሻው እሰዋለው እያለ የሚፎክር ጀነራል አለ አሁንም፤ እንዲህ አይነቱን የወርቅ ንግድ ቀጥሏል” ብለዋል። ስም ጠቅሰውም ማስረጃቸውን ዘርዝረዋል።
እነ ጀነራል ምግበ በወርቅ ንግድ ውስጥ ተሰማርተው እንደሚገኙ በስም ጠቅሰው ይፋ ያደረጉት አቶ ጌታቸው ይህ በውል የሚታወቅ፣ በቡድን የሚሰራ እንደሆን ጠቅሰው እርምጃ ለመውሰድ አጋጋች ያደረገውም ይኸው ቁርኝት መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ጌታቸው ” … ወጣቶች ለስደት በሚዳርግ ደረጃ ወደ ተራ የወርቅ ንግድ ገብተው ሲያበቁ የስርቆት ተግባራቸውን የትግራይ ግዛት አንድነት የማረጋገጥ አርገው እየገለጹ እንደገና ይሄን ወጣት ለሌላ መስዕዋትነት ሊዳርጉ እየተንቀሳቀሱ ነው” ሲሉ በስም የጠቀሷቸውን ጨምሮ ቡድናቸው ለዝርፊያው የሚሰጠውን ምክንያት ጠቁመዋል።
“እነ ኃይለስላሰም አሁን በትግራይ ህዝብ አንድነት ስም የትግራይን ወጣት ከኤርትራም ጋር ቢሆን አብሬ ለማገዶነት እንዳርገዋለው በሚል በጀግንነት ስም እየፎከረ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም እነ ምግበ ፣ እነ ኃይለስለሰን “በወንጀል የተነከሩ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።
ድንገት ሰላም ቢፈጠር “ተጠያቂ እሆናለሁ፤ አደጋ ውስጥ እገባለሁ” ብለው ስለሚያስቡም ግርግር እንዲያልቅ አይፈልጉም” ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይን ህዝብ ለሌላ ጦርነት ለማስገባት እያሰቡ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ” የፌዴራል መንግሥት ድንገት ውጊያ ይገጥመናል በሚል ስጋት ሻዕቢያ ውጊያውን ትግራይ ውስጥ እንዲያካሄድ የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀይሶ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
” ሰላም መስፈን አለበት፤ በኢትዮጵያም በኤርትራም መካከል ጦርነት መፈጠር የለበትም፣ የኤርትራ ህዝብ ለአደጋ መዳረግ የለበትም” የሚል ዕምነት እንዳላቸው የገለጹት አቶ ጌታቸው “መምረጥ ካለብኝ የትግራይ ህዝብ ድጋሚ የጦር አውድማ የሚሆንበት ሁኔታ እስከመጨረሻው ድረስ እንዳይሆን እታገላለሁ ” ሲሉ ለአገራቸው እንደሚያደሉ አስታወቀዋል።
በዚህ አግባብ እንቅፋት የሆኑት የወርቅ ንግድ ላይ የተሰማሩት ዘራፊዎች ናቸው ሲሉ ደጋግመው አመልክተዋል። ” የግንባር አዛዥ ነኝ ይላል ኝ ወርቅ ሲዘርፍ ነው የሚውለው ” ሲሉ የስብዕናቸውን መቆሸሽ አሳይተዋል።
“በ2014 ወጣቶች በየግንባሩ ሲተናነቁ በርቀት ዳባት፣ደባርቅ ፣ሊማሊሞ ሆኖ ውጊያ ይመራ የነበረ ሰው በተመሳሳይ ሰዓት በኤክስካቫተር ወርቅ እየቆፈረ ይሸጥ ነበር” ሲሉ የነበረውን የሃፍረት ደረጃ አሳይተዋል። አዋጊዎቹ ብቻ ሳይሆኑ በዚህ የዝርፊያ ኔትዎርክ ፖለቲከኞችም እንዳሉበት አመልክተዋል። አክለውም በመቶ ሚሊዮን ዘርፏል ስላሉት ኃይለስላሰም ተናግረዋል።
” ኮምቦልቻ issue account ነበር፤ በዛ ሰዓት ጦርነት ላይ ገንዘብ ስለሚያስፈልገን ትክክለኛ ውሳኔ ነው” በማለት በወቅቱ የተፈጸመውን ወረራ ያሞካሹት አቶ ጌታቸው፣ ገንዘብ እንዴት ከባንኮች እንደሚዘረፈ የተነደፈውን እቅድ አስታውሰዋል።
በዕቅዱ መሰረት “የወሰነው የግል ባንኮች ሳንነካ የመንግሥት ባንክን ብቻ እንውሰድ ብለን ፓለቲካሊ ወሰንን” ሲሉ ዛሬ የሚያበሻቅጡትን ደርጅታቸውን ገበና የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፣ ከዘርፋው ውሳኔ በሁዋላ እሳቸው እስከሚያውቁ ትድረስ አራት ቢሊዮን ብር መወሰዱን አመልክተዋል።
መጠኑ issue account ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ይሄን ከብሔራዊ ባንክ ማረጋገጥ እንደሚቻል አመልክተዋል። ” ጊዜያዊ አስተዳደር ከሆንኩም በኃላ ወረቀት መጥቶልኛል ምን እንደተፈጠረ ባንኮች ውስጥ ግለጹልን የሚል እና issue account ውስጥ ያለውን ገንዘብ እንዲሰበስቡ ከተመደቡት ሰዎች መሃል አንዱ የግምባር አዛዥ የሚባለው ኃይለስላሰ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው የወሰደው ወደ አንድ ቢሊዮን አካባቢ ገንዘብ ነው የወሰደው እሱ ስር ተፍ ተፍ የሚሉ የሱ አገልጋዮች የተወሰነ ድርሻቸው የወሰዱ አሉ ” ብለዋል። ሲል ዝርፊያው አግባብ መሆኑን ጠቁመው፣ የተዘርፈውን ሃብት ዳግም የዘረፉትን ኮንነዋል።
አብዛኛው ሰው ትግሉን ለትግራይ ህዝብ ካለው የህልውና ጥቅም አንጻር እንጂ “ገንዘብ አገኝበታለሁ” ብሎ አይደለም የተሳተፈው ብለዋል። “እኔ በማውቀው ባረጋገጥኩት በሰነድ ጭምር እነ ኃይለ የወርቅ ማሽኖችን ሲያስገቡ ነው የሚውሉት” ብለዋል። የፖለቲካ አመራሩም አብሮ የወርቅ ንግድ ውስጥ መሰማራቱን ጠቁመዋል።
ሰዎቹ ማሽን ሲያዝባቸው የፌዴራል ሰዎች ጋር እየተደዋወሉ በመሞጋገስ እንዲለቀቅላቸው ሲማጸኑ እንደሚውሉ አቶ ጌታቸው በቃለ ምልልሳቸው አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል በጠቆሙት በጥናት እያንዳንዱ የዘረፈው ሃብት ተዘርዝሮ እርምጃ እንዲወሰድ ቢጠየቅም እንዳልተቻለ አመልክተዋል። የቀረበውን የጥናት ሰነድ እነ ደብረጽዮን (ዶ/ር) እንደሚያውቁት፤ በሳቸው ሰብሳቢነት ይፋ የሆነና አሁን ድረስ እጃቸው ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
“ትግሉ ውስጥ ትልልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ሰዎች ስም ሌሎችን ይዞ እንዳይጠፋና የውሸት አንድነት ለማስቀጠል ሲባል እምርጃ መውሰድ አልተቻለም” ሲሉ የሚቀርብላቸውን ሰበብ ተናግረዋል። አክለውም “የመረረኝ ሰዓት እርምጃ እንዲወሰድ ዶክመንት አቅርቤም ተግባራዊ አልተደረግም” ሲሉ ጉዳይ ከአቅማቸው በላይ እንደነበር ጠቁመዋል።
እነ ምግበን፣ እነ ኃይለስላሰን በስም ጠቅሰን መጠየቅ ስላልቻልን “ሁሉም የሰራዊት አመራሮች ዘርፈዋል” የሚል የጅምላ መልዕክት እያስተላለፍን ነው የመጣነው ይህ ትክክል አይደለም ብለዋል።
ተጠያቂነት እንዳይሰፍን የፖለቲካ መሪዎቹ እንቅፋት እንደሆኑ ይህን የሚያደርጉትም እነሱም ተጠያቂ ስለሆኑ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋ አድርገዋል። አብዛኛው የሰራዊት አመራር ግን ሰላም ፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጌታቸው ረዳ ጸረ ድሮን እንገዛለን በሚል 1.4 ሚሊዮን መዘረፉን ሲናገሩ በግርምት ነው። ሰዎቹ ይመጣሉ የተባሉ ከእስራኤል ሲሆን በአፋር በኩል ገብተው ላብቶፓቸውን በመዘርጋት ድሮን ሲመጣ ምልክት የሚሰጡ እንደሆነ ለዶር ደብረጽዮን ተነግሯቸው መዘረፋቸውን አመልክተዋል፤ ዝርፊያው በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን ዲያስፖራው ያዋጣው ሃብት እንዴት እንደተበላ ለማሳየት ያነሱት ምሳሌ ነው።
በትግራይ ከተደፈሩ ሴቶች 76 በመቶ የሚሆኑትን የሻዕቢያ ሰራዊት እንደፈጸመው ጥናት አጣቅሰው ካስረዱ በሁዋላ፣ በአንድ ትምህርት ቤት በተሰባበረ ሰሌዳ ላይ “ሰላሳ ዓመት ወደሁዋላ መልሳችሁናል፣ አርባ ኣመት ወደሁዋላ እንመልሳችኋለን” በሚል የሻዕቢያ ኃይሎች መጻፋቸውን ጠቅሰው ሁሉም ሲከናወን የነበረው በዕቅድና በፕላን መሆኑን አስረድተዋል። እንግዲህ የደብረጽዮን ትህነግ እያበረ ያለው ከዚህ ዓይነቱ የጥፋት ተቋም ሻዕቢያ ጋር መሆኑ ደርብ ሃዘን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው እየደጋገሙ የወንጀል ኢንተርፕራዝ እያሉ የጠሩት የትህነግ ቡድን ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ሊወገድ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአሁኑ ሰኣት እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና በውጭ አገር የድርጅቱ ከጥቂቶቹ በቀር ደጋፊ የሆኑት ሁሉ ፊታቸውን ትህነግ ላይ አዙረዋል። የአማራ ፋኖ ደግሞ ትህነግ ወይም ሞት በማለት የሸዕቢያን የበላይነት ተቀብሎ ኢትዮጵያን በማፍረሱ ዕቅድ ውስጥ ተሳታፊ መሆኑን በይፋ አስታውቋል፤