የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ” ባለቤት ‘ ወይም ” ባለይዞታ ” የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ይህ ” የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት ” ወይም ” ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሚያገኙበትን ” ህጋዊ አሰራር ለመዘርጋት ነው።
ረቂቅ አዋጁ ምን ይላል ?
- ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ መሬትን፣ የመኖሪያ ቤትን ወይም ተያያዥ ግንባታዎችን በባለቤትነት ለመያዝ፤ ቢያንስ 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሊመድቡ እንደሚገባ ይደነግጋል።
- በውጭ ዜጋ ” በሊዝ ባለይዞታነት ” ወይም ” ባለቤትነት ” የሚያዝ መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት፤ ” የማይንቀሳቀስ ንብረት ” ተደርጎ ይወሰዳል። ” ሊዝ ” ማለት ” አግባብነት ባለው ህግ መሰረት በጊዜ በተገደበ ውል ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ዓላማ የሚውል የከተማ ወይም የገጠር መሬት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት ” ነው።
- ማንኛውም የውጭ ዜጋ በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ሊሆን የሚችለው በአዋጁ የተዘረዘሩ ቅደመ ሁኔታዎችን ሲያሟላ ነው።
እነዚህም ፦
° የውጭ ዜጋው ስም፣ ዜግነት እና ሌሎችን ማንነትን የሚገልጹ ህጋዊ ሰነዶችን ማቅረብ አለበት።
° የውጭ ዜጋው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለመብት ለመሆን የሚያስፈልግ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለማሟላት የሚያስችል በቂ አቅም ያለው መሆን አለበት።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ለመሆን፤ የሊዝ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ ዋጋ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግዢ የሚመድበው አነስተኛ የገንዘብ መጠን ከ150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ሊሆን አይችልም።
° የውጭ ዜጋው የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆን ይገባዋል።
እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ አንድ የውጭ ዜጋ ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚሰጥ ፈቃድ ሊያገኝ ይገባዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ” የፈቃድ ይሰጠኝ ” ማመልከቻ ላቀረበ የውጭ ዜጋ፤ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ በ15 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።
- የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከውጭ ዜጎች የሚጠበቀውን የአነስተኛ ገንዘብ መጠን ከፍ ወይም ዝቅ የሚያደርግ የእያንዳንዱን የሊዝ ቦታ ወይም ቤት ስፋት እንዲሁም የሊዝ ይዞታዎችን ወይም ቤቶችን አጠቃላይ ቁጥር የሚወስን መመሪያ የማውጣት ስልጣን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቶታል። መመሪያውን የሚያወጣው፤ የቤቶች ገበያ ወቅታዊ ሁኔታን፣ የከተሞች የማይንቀሳቀስ ንብረት አማካይ ዋጋን፣ የውጭ ዜጎች በቤቶች ገበያ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እና የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ ሌሎች ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ነው።
- የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ፤ የተወሰኑ ሀገራት ዜጎችን ወይም ዜግነት የሌላቸው የውጭ ሀገር ሰዎችን በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ #ሊከልክል ይችላል።
- ለውጭ ዜጎች የተገደቡ ልዩ ቦታዎች እና የድንበር አካባቢዎችም እንዲሁ በሚያወጣ መመሪያ ይወሰናሉ።
- በውጭ ዜጎች ላይ የተጣሉ ሌሎች ገደቦችም አሉ።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ ለመሆን ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ አይችልም።
° የውጭ ዜጎች ይህን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የሊዝ፣ የቤት ግዢ፣ የግንባታ ፈቃድ ወይም ተያያዥ የመንግስታዊ አገልግሎት ክፍያዎችን መክፈል ያለባቸው በኢትዮጵያ ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሬ ብቻ ነው።
° ማንኛውም የውጭ ዜጋ በመንግስት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሰሩ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን አይችልም። ይህ ገደብ በግል እና በመንግስት አጋርነት ወይም በተመሳሳይ የቤቶች ልማት ማዕቀፍ በፌደራል ወይም በክልል መንግስታት የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችን አያካትትም። ለውጭ ዜጎች የተቀመጠው ገደብ በእነዚህ አካላት አማካኝነት ለትርፍ ዓላማ ተገንብተው ለሽያጭ የሚቀርቡ ቤቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ነው።