በከፍተኛ ደረጃ ወደ ኤርትራ ሸቀጥና ነዳጅ በስፋት እንደሚጋዝ የሚወጡ መረጃና ማስረጃዎችን ተከትሎ በአፋር ታዘው የነበሩ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች መለቀቃቸው ተገለጸ። ስምምነት የተደረሰው የክልሉ መሪና የፌደራል ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር ጋር ውይይት ከተደረገ በሁዋላ ነው።
ወደ ትግራይ ክልል ሲጓዙ አፋር ላይ ለቀናት ክልከላ የተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች እንዲለቀቁ የተደርገውውን ስምምነቱን ተከትሎ ተሽከርካሪዎቹ መለቀቃቸውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት አሰታውቋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ከውጭ አገራት ጋር መርህ አልባ ግንኙነት ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው በደብዳቤ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። እሳቸው ይህን መመሪያ ቢሰጡም የኤርትራ ኃይሎች ሸቀጥ ከማጋጋዝ በተጨማሪ በትግራይ በይፋ በሚባል ደረጃ እንደሚንቀሳቀሱ ምስል አስደግፈው ዜጎች ከትግራይ መረጃ እያሰራጩ ነው። በራማና ሽሬ አቅጣጫ ሸቀጥ ሲጋዝም የሚያሳይ ፎቶም እየለቀቁ ነው።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ውሳኔው ተግብራዊ መሆኑን ጽህፈት ቤታቸው አመልክቷል። ሌ/ጄነራል ታደሰ ከኮሚሽነር ጋር ውይይት ያደረጉት ግንቦት 23ቀን 2017 ዓ.ም ነው።
ከግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ሲጓዙ ክልከላ የተደረገባቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች የተከለከሉበት ምክንያት የጫኑት የንግድ እቃ ከትግራይ አልፎ በኮንትሮባንድ መልክ ወደ ኤርትራ ሊሻገር ይችላል ከሚል ጥርጣሬ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
ሁለቱም ኃላፊዎች በውይይታቸው የመረጃው እውነትነቱ ምን ድረስ እንደሆነ የሚያጣራ ከፌደራል ፖሊስ እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ኮሚቴ ጉዳዩን እንዲመረምረው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመልክቷል።
የኮሚቴው የምርመራ ውጤት መሰረት በማድረግ የቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጋ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይህን የማከናወን ተግባርና ኃላፊነት ደግሞ በዋናነት የጋራ ኮሚቴው እንዲሆን ተወስኗል።
በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ኃላፊዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤታ ያሰራጨው መረጃ አመልክቷል።