በግብይት ወቅት ከአስር ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብን መጠቀም፤ ለከፋዩ በወጪነት፣ ለተቀባዩ ደግሞ አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልበት ያደርጋል ተባለ። አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ሲጸድቅ ከ10,000 ብር በላይ ግብይትን በጥሬ ገንዘብ መፈጸም የሚያስቀጣ ይሆናል ተብሏል።
ረቂቅ አዋጁ ላይ ሃሳብ ለማዋጣት ከተሳተፉ ባለሙያዎች መካከል የተወሰኑት ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው አሰራር ላይ ጥያቄ አንስተዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊው አቶ ተወዳጅ መሐመድ እንዳሉት አዋጁ ተግባራዊ የሚደረገው በጥሬ ገንዘብ የሚፈፀም ግብይትን መገደብን ታሳቢ አድርጎ ነው።
በአንድ ግብይት የሚፈፀም የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ከ10ሺህ ብር ከበለጠ፣ ትርፉ ብር ለከፋዩ በወጪነት አይያዝም። ወይም ውድቅ ይሆናል። ገንዘቡን የተቀበለውም የትርፉን ገንዘብ እጥፍ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተቀምጧል።
ለምሳሌ የ20,000 ብር ግብይት በጥሬ ገንዘብ ቢፈፀም ለነጋዴው፣ ከ10 ሺህ ብር በላይ ያለው በወጪነት አይያዝም፣ ለተቀባዩ ደግሞ ከ10,000 በላይ ያለው ቀሪ 10,000 ብር እጥፍ ማለትም 20,000 ብር ይቀጣል እንደማለት ነው።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የተሳተፉ፣ በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዲፈፀም ምክንያት የሚሆነውን በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልና፣በሌሎች መመሪያዎች የጥሬ ገንዘብ ግብይት ስለሚፈቀድ አዋጁ የተናበበ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባሰናዳው ረቂቅ አዋጅ መሰረት ከ10,000 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዳይፈፀም የሚጣለው ግዴታ፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም ይላል።
ሌሎች አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ዝርዝራቸው ይፋ ይሆናል ይላል ረቂቁ። ዜናው የኢሳት ነው።