ልክ የዛሬ 20 ዓመት አቶ መለስ ዜናዊ ነጻ እርምጃ እንዲወሰድ ህዝብ ፊት ቀርበው በሰጡት ትዕዛዝ መነሻ የአጋዚ ጦር አዲስ አበባን በደም ነከራት። “ድምጻቸን መነጠቅ የለበትም” በማለት በሰላማዊ መንገድ የተቃወሙ ግንባራቸው እየተመረጠ ተወጉ።
የአጋዚን ጥይት በቅድሚያ የተቀበለው ታዳጊ የ14 ዓመቱ ነብይ አለማየሁ ነበር። ነብይ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ አንድ የአጋዚ ቀይ ለባሽ መሳሪያ ደቀነበት። ነብይ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚሄድ ጠቅሶ ለመነው። የመለስን መመሪያ የተቀበለው አንጋች ተኩሶ ገደለው። በኮተቤ ኮሌጅ ፊት ለፊት እነ ሽብሬ ተደፉ። አዲሱ ገባያ እናት ልጃቸው አስከሬን ላይ እንደተጣበቁ ተገደሉ። የዛሬ ሃያ ዓመት ሆስፒታሎች በደም በተነከሩ ዜጎች ተሞሉ። ዋይታ ሆነ። ሚኒሊክ ሆስፒታል አስከሬን ሞላ። በዚህ ቀን ዋዜማ ነው የዚህ ጭፍጨፋ አባት የሆነው ስብሃት ነጋን የሰላም ኃዋሪያ አድርገው የጋበዙልን። የፈረሰውን የፌደራል ኃይሎች በሳይበር ሰብስቦ ትህነግ በልደቱ አምሳል ብቅ እንዲል የተደረገው።

አቶ መለስ ሰኔ አንድ ቀን ህዝብ ሲፈጅ እሳቸው የልጃቸውን ልደት ሸራቶን አዲስ ያከብሩ ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች “ለሕዝብ ዕልቂት ደንታ የሌላቸው” በሚል በወቅቱ ዘልፈዋቸው ነበር። የዛን ሰሞን ነበር አቶ ልደቱም ከስብሃት ነጋ ጋር እዛው ሸራቶን የታዩት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኝነት ላይ የተተከለውን የወያኔ አገዛ ለመንቀል በቅንጅት ባካሄዱት ምርጫ ኢህአዴግ ተሸንፎ ነበር። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ከዘረኝነትን የጸዳ ዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ለመትከል ወስነው አገዛዙን በድምጻቸው ከከተማቸው ዘረሩት። ፍጹም ሰላማዊ በሆነ አግባብ ሕዝብ ኢህአዴግን ካሰናበት በሁዋላ ነገሮች መልካቸውን ለወጡ።
የሕዝብን ውሳኔ በጠብ መንጃ ለመቀልበስ መለስ ቅልብ ጦራቸውን “ተነስ” አሉ። ቀይ ለባሹ አጋዚ የጸጥታውን አካሄድ ከፖሊስ ተረክቦ አዲስ አበባን ወረር። እነ ሽብሬን ጨምሮ በመላው አገሪቱ በጥቅሉ ሁለት መቶ የሚጠጉ ንጹሃንን ጨፈጨፈ። ከአንድ ቤት ሁለት ሰዎች፣ እናትና ልጅ ተገደሉ። ከ14 እስከ 67 ዕድሚ ክልል ውስጥ ያሉ ንጹሃን
አለቁ። ይህ በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ፍትሃዊ ፍርድ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ በዋዛ ፈዛዛ ተረሳ። የዚህ ግፍ ተዋናዮችና ከሃጂዎች እንዲሁም ሽፋን ሰጪ ሚዲያዎች በዚህ ቀን ዋዜማ “የሰላም አባት ነን። ጦርነት ይቁም” ብለው በአዲስ ማሊያ መጡ።

የድፍረታቸው ድፍረት “መለስ ማረን” የሚሉ ዘረኞችና በዘረኝነት ቅስቀሳ ላደረሱት ጥፋት በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸው ግፈኞች አንድ ላይ ተሰባስበው ተኮለኮሉ። ዓላማው ሳይሆን የዓላማው አመንጪና አስፈጻሚ ሆነው ብቅ ያሉት የትህነጉ ልደቱ አያሌውና የትህነግ ሚዲያ ርዕዮት ማንነት ነው።
እነዚህ ኃይሎች ቀላቢያቸው ትህነግ በሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም ንጹሃን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ዋዜማ ቀን ዓይናቸውን በጨው አጥበው የዚህኑ ድርጅት ጦርነት ጠማቂዎች፣ ሴራ ጠንሳሾች፣ የዘረኝነት አዋላጆች፣ አሸርጋጆችና ተላላኪዎች፣ ከዚያም በላይ ትናንት አማራና አፋር ክልል ሲወረ “ ግፋ በለው፣ ጦርነት ባህልህ” በሚል ቀረርቶ ሲያወርዱ የነበሩትን የደም ነጋዴዎችን ይዞ የሰላም መዝሙር አሰሙ። የሰማዕታት ደም በሚጮህበት ቀን ዋዜማ የንጹሃንን ደም የጠጡ የሰላም ካባ ለብሰው ታዩ።
ለደቱ ትህነግን የሰላም ኃዋሪያ አድርጎ ከች ፟ አባቱን ስብሃትን ይዞ
ቅንጅት ላይ ስቅላት የተፈረደው ሸራተን አዲስ ውስጥ ነበር። በወቅቱ አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ስብሃት ነጋ ነበር ቅንጅት የሚሰቀልበትን ገመድ ሲገምዱ የነበሩት። በወቅቱ አዲስ ነገር ላይ ይጽፍ የነበረው አብይ ተክለማሪያም በዓይነ ብረቱ ያየውን ለሕዝብ ይፋ አደረገው። እዛው ሆቴል ውስጥ የሚሰሩ እማኞችም በየፊናቸው ዜናውን አሾለኩት፡፡ እንግዲህ ይህ ልደቱ ነው የያኔው አልበቃ ብሎት ዛሬ ትህነግን ዳግም ለመጠገን ደፋ ቀና የሚለው።

አቶ ልደቱ ማህተም ከልክለው ቅንጅቱን በትነውታል። እንደ ሱናሚ ግልብጥ ብሎ ወያኔን በሙሉ ድምጽ የዘረረውን ሕዝብ በጠራራ ጸሃይ ክደውታል። “ጀግና” ብሎ ያሞካሻቸውን ሕዝብ በሽልንግ ቸብችበውታል። እጥፍ ብለው ፓርላማ ገብተዋል። ጊዜ ደርሶ በቅርቡ ፍርድ ቤት ተከሰው “ደህንነት ለህይወትህ መጠበቂያ ብሎ መሳሪያ ሰቶኛል” ሲል ራስን በመከላከል ስም ትክክለኛ ማንነታቸውን ተናግረዋል። ይህቺን ያንብቡልኝ ልደቱ የ98 ምርጫ ወቅት ከህወሓት ደኅንነት ሽጉጥ መቀበሉን ለፍርድ ቤት አመነ
በክህደትና በበደል የተነከሩት አቶ ልደቱ ይህን ሃጢአታቸውን ለማጠብ መጥሐፍቶችን ጣፉ፣ በጋዜጣዎች ሳይመርጡ ለፈለፉ። ዩቲዩቡንና ሁሉንም ማህበራዊ አውዶች ተጠቀሙ፣ ሬዲዮኖች ቲቪ ወዘተ ተጠቅመው “ጲላጦስ ነኝ” አሉ። ምን አለፋችሁ ራሳቸውን ለማጽዳት ያልገቡበት የፕሮፓጋንዳ ማጀት አልነበረም። እስቲ ይህቺን ያንብቡልኝ ልደቱ አያሌውን ስድስት ነገሮች ሆነው ይሆናል በሉት
አሁን አሜሪካ ልባቸውን እየታከሙ ጎን ለጎን በጀመሩት አክቲቪዝም የሳይበሩ ጫካ ቋሚ አባል ሆኑ። በተለይም የትህነግ መክሰም እየተቃረበ ሲሄድ የፊት ተሰላፊ ሆኑ። በዚሁ ግለት ከርዕዮት ጋር ሆነው፣ የአቶ ጌታቸው አሰፋን የቀደመ ኔት ወርክ ድሩን ጠርገው “ ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይምጣ፣ አገዛዙ ይፍረስ” የሚል አጀንዳ አራጋቢ ሆኑ። እስኪ ይህቺን አንብቡልኝ ልደቱ ትህነግን ለማዳን ጥሪ አቀረበ፤ አማራ የኅልውና ችግር አልገጠመውም
ለአማራው የሃምሳ ዓመት መከራ መነሻ ትህነግ መሆኑን የባጉናው ልደቱ አይቀበሉም። አማራውን ፀረ ጭቁን ህዝብ፣ ደም መጣጭ፣ ነፍጠኛ፣ አውሬ ተደርጎ በትህነግ ሲፈረጅ የልደቱ ለቅሶ ጨበጣ ነበር። ትህነግ አማራዉን ፈርጆ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲያስገድለው፣ እንዲፈናቀሉ ሲያደርጋቸው፣ ማንነታቸውን ገፎ በግድ ብሄራቸውን ሲያስቀይራቸው፣ መሬታቸውን ወስዶ ሲዛበትባቸው አቶ ልደቱ የሚታያቸው የበሉበት ገል እንጂ ሌላ ጉዳይ አልነበእረም። አማራ ላይ መርዘኛ ትርክት የቀቀመውን ስብሀት ነጋን ዛሬ የሰላም ዘማሪ አድርጎ ሲያቀርብ ልደቱ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ሸራተን ቅንጅት ላይ ያሴረበትን ቀን የሚያስታውስ ሆኗል። የዚሁ ሴራ ሰለባ የሆኑቱ ደም ይጮሃል።
በታህሳስ 1996 ዓ.ም 426 የአኝዋክ ብሄረሰብ አባላት በቄያቸው ተጨፍጭፈዋል። በሕይወት ተርፈው ሜኖሶታ የሚኖሩ ታሪኩን ሲዘክሩት ያማል። የዚህ ጭፍጨፋ ደራሲዎች ስብሃት ነጋ የሚነዱት ትህነግ የተባለው ድርጅት መሆኑን በማስረጃና መረጃ አቅርበዋል። በወቅቱ የተፈጸመውን የረሱት ኢንጂነር ኦባንግ ኦማን ምን ፈልገው እዚህ ጉባኤ ላይ እንደተገኙ የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው። ግን አዘጋጆቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የሚዘነጋ ይመስላቸዋል? እባክዎን አሁንም ይፈለጋልን ያንብቡልኝ።
የሚኖሴታው ኢስማኤል ኢዳክስ ይህን ጉባኤ ሶማሌም ወኪሉ እንደነበር ለማሳየት የሰማይ ላይ ሰልፉን እንዲታደሙ ተደርገዋል። ለመሆኑ አቶ ኢስማኤል የኦጋዴን እስር ቤትን ማን እንዳቋቋመው፣ በውስጡ ምን እንደተሰራ ዘንግተው ይሆን? ወይስ ምን ዓይነት አበል ቢከፈልዎ ነው ለአውሬ እየተሰጡ ሲታረዱ የነበሩ ቤተሰቦችዎን የረሱት? አዘጋጆቹስ ብትሆኑ ካሁን በሁዋላ የሶማሌ ሕዝብ ልደቱ ለሚገጣጥመው ትህነግ ዳግም የሚገዛ ይመስላችኋል? እስኪ ይህቺን አንብቡልኝ The Shame of Ogaden ትህነግ ‘የሰው ልጆች’ መብት ተቆርቋሪ ሆነ፤ እኛም አፈርን።
ከስዊዲን አዲሱ ጎጆው የታደመው አቶ ጃዋር ጎሮጉቱ ወረዳ ካራሚሌ ጀርጀርቱ ውስጥ እምብርቱን ተክሎ የሚላወሰውን ታጣቂ እንዴት እንደሚያደራጅ ወደፊት እንነጋገራለን። ራስህ በቅርቡ በኤክስ ገጽህ ላይ “ከምዕራብ ሐረርጌ በቅርቡ ይነሳል” ያልከው አክራሪ ኃይል ሳትበትን የሰላም አዝማች ሆነህ በተዘጋጀው የሰማይ ላይ ትዕይንት ተጋብዘሃል።
“ጠሪ አክባሪ” በሚለው መርህ የታደምክበት ሚዲያ አር እንደነካው እንጨት ከወር በፊት በጄኖሳይደር ፈርጆ የቀጠቀጥህን እያስታወስኩ ለጋባዥህ ትህነግ፣ ተግባርህ የተረሳ መስሎህ ከሆነ ለራስህ፣ ጃዋር ያስፈጀውና የፈጸመው ወንጀል እንዲሁም ሲተፋ የነበረውን የዕልቂት አዋጅ ታስታውሱ ዘንድ እባካችሁን ይህቺን አንብቡልኝ ደም ጠጥቶ “አልጸጸትም” – የጃዋር አዲስ መጽሐፍ እናም ወገን ስብስቡን አስቡት። ይህቺንም አክሉልኝ 160 ሰዎች የሞቱበት፣ 360 ሰዎች የተጎዱበት፣ ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት የወደመበት የነጃዋር ክስ ጎበዝ እንዴት ቢንቁን ነው? በዚህ ደረጃ በደምና በወንጀል የተጨማለቁ ሰዎች ተሰባስበው የሰላም ኃዋሪያ የሚሆኑት? የምድሩን ሁሉ ጨርሰው፣ ታንክና ሮኬት ተኩሰው ሲያቅት የሰማይ ላይ ሰልፍ ጠሩ !! እነሱ ባያፍሩም እኛ አፈርን።
ስለ አቶ ገዱ ብዙ አልልም። ወልቃይት ጠገዴን ለትህነግ በአደባባይ ሸጦ በኩራት እያሽካካና እየገለፈጠ ታሪክ ላይ የተጎለተ ነውረኛ ነው። ትህነግ ይህ ዕቃውን ወልወል አድርጎ በልደቱ አማካይነት የሰማይ ላይ ነውጡ መሪና የሰላም ዘማሪ አድርጎ አቅርቦታል። እባካችሁን ይህቺን አንብቡልኝ። ትህነግ ገዱን በዘር ማጥፋት አንከሰውም፤ ባለውለታችን ነው አለ፤ እንግዲህ እንዲህ ያለ እንደ በግ የሚነዳ ሰው ነው የሰላም ኃዋሪያ ሆኖ ዳግም እንዲሾም እየታጨልን ያለው።
በዚሁ የዓየር ላይ ትዕይንት ከተጋበዙት መካከል ርዕዮት ዓለሙ የተናገረችውን ላንሳና ልቋጭ። እንደው ሁሉም ቢቀር የአገር መከላከያ ላይ በክህደት ጦር አንስቶ ለዛ ሁሉ ቀውስ ምክንያት የሆነው ትህነግ የዚህ ጥሪ አስተባባሪ መሆኑ አስገራሚ መሆኑን ገልጻለች።
ሃያ ሰባት ዓመት ስልጣን ላይ ግፍ ሲፈጽም የኖረ፣ ሰባቱን ዓመት የማዕከላዊ መንግስትን አልቀበልም ብሎ ትግራይ የከተመ፣ የአገር መከላከያ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ጦርነት የጀመረ፣ ብልጽግናን በመቃወም ሰበብ ይህን ድርጅት ተናጋሪ አድርጎ መጋበዝ ለርዕዮት የሆነ መዛባት እንዳለ አመላካች እንደሆነላት ነው የተናገረችው።
ኢትዮጵያን የባህር አልባ አድርጎ ሃብቷን ለጅቡቲ እንድትገብር የፈረደ የታሪ ውርጃ የሆነ ፓርቲ፣ በባድመ ሕዝብና የኢትዮጵያን ልጆች ካስጨረሰ በሁዋላ የድሉ ጫፍ ላይ ውሃ ቸልሶ ለሻዕቢያ ባርነትን የመረጠ ከሃጂ፣ 200 የሚጠጉ ንጹሃንን የረሸነበት ቀን ዋዜማ ላይ አቶ ልደቱ ክንፍ አበጅተውለት የሰላም ኃዋሪያ አድርገው ሲያቀርቡት ነገሩ አክትሟል።
በዚሁ የሳይበር ዲስኩር ከተጋበዙት መካከል ስለ ጃል ጠሃ አብዲና፣ ዘመነ ካሴ፣ የኢህ አፓዋ ሚስጥረ ስላሴ፣የወላይታው ተወካይ የተባሉት የአማኑኤል ሞጊሶ፣ እና እነ ፕሮፌሰር ህዝቅኤልና በሟሟቅ የሚታወቁት አጋፋሪዎች አንድም ነገር ማለት አልፈልግም።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ምን እያለ እንደሆነ መስማቱ በቂ ስለሆነ እዛ ላይ ማከል ማበላሸት ስለሚሆን አንባቢያን የዚህን ሕዝብ ብሶትና ለቅሶ አድምጡ። ከዚህ በዘለለ ግን በግል አሰላለፉና አወቃቀሩ መሪውን ማን እንደያዘው ፍንትው አድርጎ ስላሳየኝ እሱ ላይ ሌላ ቀን የምለው ይኖረኛልና ለዛሬ አልፈዋለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ የሰማይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ያገኘችው ቁልፍ ጉዳይም ይኸው የአሰላለፍ ጉዳይ ጥርት ብሎ መታየቱና ከዚህ በሁዋላ ሌላ ካባ ለብሶ ማምጣት ማክተሙን ነው። “ለተገፉ ሁሉ ድምጽ ነን” እያሉና ትህነግ ላይ መርዝ የሆኑ ቃላቶች በመሰንዘር ተከታይ በመሰብሰብ አድብቶ ትህነግን ዳግም የሞመሸሩ የርዕዮት ቲዩብ ድራማም እንዲህ እርቃን መሆኑ ተመስገን የሚያሰኝ ነው።
ሌሎቹን ማህበረተኞች አስመልክቶ አንባቢያን የራሳችሁን ግምት ውሰዱ። አንድ ነገር ግን ጠይቁ። በዚህ የትህነግ ስብስብ ወይም ከሰባት ዐመት በፊት ተጀምሮ የከሸፈው የፌደራል ኃይሎች ጥምረት ውስጥ የሻዕቢያ ወኪሉ መሳይ መኮንን፣ ፋሲልና ደረጄ እንዲሁም የኢትዮ360 ሃብታሙ አያሌው ምነው “ በራብን” አሉ። ኢሳያስ ስላልተጋበዙ? ወይስ ምን? አንዳርጋቸው ጽጌን ጠይቁልኝ።
ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ወይም ቅድሚያ ኦሮሚያ፣ አማራ ተራራው የኢትዮጵያ ፈጣሪ፣ አማራ የሰው ውሃ ልክ፣ ትግራይ ተስርይ ወይም አሸናፊ ናት ከሚሉ ጋር ሕብረት የፈጠሩትን ደግፈን “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያዊ” የሚሉትን እናጥፋ? ይህ የአቶ ልደቱ ድግስ ብዙ አስተምሮናል። ነገ ከነገ ወዲያ እርስ በርሳቸው ሲባሉ ሴራውን እስኪዘከዙልን ሰላም ሁኑ።
በዚሁ መነሻዬ “ትህነግ በልደቱ በኩል ‘የሰው ልጆች’ መብት ተቆርቋሪና የሰላም ሐዋሪያ ሆኖ የሰማይ ላይ ሰልፍ አዘጋጀ ፤ እኛም አፈርን” ብል ጥፋተኛ ነኝ? አጋነንኩ? አጠፋሁ? ብልጽግና ነኝ?