የሱዳን ፈጣኖ ደርሽ ሃይል መሪ ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ/ ሄሜቴ ኤርትራን እንደሚበቀሉ አስታውቀዋል። ከፊል ሱዳንን የሚቆጣጠሩት ሃምዳን ደጋሎ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰራጩት የፊልም መረጃ በሱዳን ጦርነት የተሳተፉትን አገራት ዘርዝረዋል። ኢትዮጵያም አለችበት፡፡
ጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ “ኤርትራ ከድርጊቷ የማትቆጠብ ከሆነ እንበቀላታለን” ሲሉ በተድመጡበት ቪዲዮ የሱዳን ጦር ኃይሎችን ይደግፋሉ ሲሉ ግብጽ፣ ኤርትራና ኢትዮጵያን አንስተው ከሰዋል።
የኤርትራ መንግስት ደጋፊ የሆኑ የፕሮፓጋንዳ አውታሮች ሄሜቴ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨታቸውን በመጥቀስ ሊያጣጥሉ ሞክረዋል። መረጃ የማይቀርብበት እንደሆነም ገልጸዋል።
የኤርትራው አገዛዝ በቅጥረኛ የውጭ ፖሊሲው እንደሚታወቅ የሚገልጹ ቅጥረኛነቱ እንደ ዋና የገቢ ምንጩ እንደሚወሰድ ያመልክታሉ። ተገንጣዮችን ማደራጀት፣ ጽንፈኞችንና የጦር አበጋዞችን በማሰልጠን እና በማስታጠቅ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያመርት የሚነገርለት ሻዕቢያ በወኪሎቹ አማካይነት ቢያስተባብልም የሄሜቲ ክስ ሚዛን እንደሚደፋ ይናገራሉ።
ምንም ይሁን ምን በቅርቡ በጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ወታደራዊ ኃይል መቀመጫ በሆነችው ፖርት ሱዳን ለሦስት ተከታታይ ቀናት በድሮን የደረሰው ዓይነት ጥቃት ሊከተል እንደሚችል በመጥቀስ ስጋት የገባቸው ኤርትራዊያን ጥቂት ዓይደሉም።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት ፖእርት ሱዳን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የሱዳን ጦር ኃይል ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ጦር የከሰሰ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን እስካሁን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ ኃላፊነቱን እንዳልወሰደ ይታወሳል።
የፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ የሆኑት ሄሜቴ የኤርትራን ስም ጠቅሰው ጣልቃ ገብነቷን የማታቆም ከሆነ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ መግለጻቸውን ተከትሎ እየተዘዋወረ ያለው መረጃ ፖርት ሱዳን ላይ የደረሰው ጥቃት ነው፡፡ ዳጋሎ ኤርትራን ከተበቀሉ የሚጠቀሙት አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች በመሆኑ ኤርትራ እንዴት ትቋቋመዋለች የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ማንሳታቸው ዜናውን ከፍ አድርጎታል።
“ይህ ጦርነት የሱዳናዊያን ብቻ አይደለም።ኤርትራና ግብፅም ጣልቃ ገብተው እየተዋጉን ነው ” ካሉ በኋላ “ኢትዮጵያውያን ሳይቀር እየወጉን ነው” ሲሉ “ስለ ማን ነው የሚናገሩት” ሲሉ የጠየቁ ቀደም ሲል ሲወጡ የነብሩ መረጃዎችን ማገላበጥ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡
በሱዳን የሚገኘው የትህነግ ታጣቂ ኃይል ወልቃይትን ከሁለት አቅጣጫ ለማጥቃት ታስቦ ሱዳን እንዲቀመጥ የተደረገ፣ በማይካድራ ንጹሃን ግድያ የተሳተፈና ወደ ሱዳን የሸሸ የወጣቶች አደረጃጀት የተካተቱበት፣ በስደት ካምፕ የነበሩ ተፈናቃዮች ወዘተ በሚል የተለያዩ ስያሜ የሚጠሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሌተናል ጄነራል ዮሐንስ ገ/መስቀል በቅርቡ ባካሄዷቸው ቃለ ምልልሶች ትህነግ በሱዳን ሲያሰለጥነው የነበረ አንድ አርሚ እንደነበረው መግለጻቸው ይታውሳል። ሲያብራሩም ይህ አርሚ ትህነግ ጦርነት በከፈተበት ወቅት ተቆርጦ ሱዳን መቅረቱን አምልክተዋል። ይህ ኃይል ከጄነራል አልቡርሃን ጋር ወኞ የአር አር ኤፍ ኃይሎችን መውጋቱ ለኢትዮጵያ በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ጥቁር ጠባሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ ርዕሰ መስተዳድር ወንበራቸው ከመነሳታቸው በፊት “በሱዳን ያሉ ሰላማዊ የትግራይ ተወላጆች” ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂቅዎች በሱዳን ጦርነት ተሳትፈው የጄነራል አልቡርሃን ኃይሎች ድል ሲያደርጉ አብረው በጭፈራ ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ ቪዲዮ ሲሰራጭ ነበር። እናም ዳጋሎ የኢትዮጵያን ስም ያነሱት የትግራይ አንድ አርሚ ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጎን ሆኖ መዋጋቱን ለማመላከት እንደሆነ ዜናውን የሰሙ ተስማምተዋል።
በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስና በዩኤስ አሜሪካ እንደሚደገፍ የሚነገርለት የፈጣን ድጋፍ ሃይሎች/ አር ኤስ።ኤፍ አዛዥ ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ኃይላቸው ሳውዲ አረቢያን ለአርቡርሃን ወገንተኝነት ታሳያለች በሚል ወንጅለው የጅዳን የሰላም ድርድር ማቋረጡ መግለጹ ይታውሳል።
በሱዳን ጦርነት ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ግብጽና ኤርትራ ከሱዳን ጦር ሃይል ጎን በይፋ መሳተፋቸው የሚታወቅ ነው። ጄነራል አልቡርሃን ጦር ከግብጽ ያገኘችውን ክሎሪን ጋዝ መጠቀሟን ጠቅሰው ሄሜቲ ከሰዋል፡፡
“የሱዳን መንግሥት ሁሉንም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም እንዲያቆም እና የዓለም አቀፍ መርህ ስር ያሉትን ግዴታዎች እንዲወጣ ዩናይትድ ስቴትስ መጠየቋና ማዕቀብ እንደምትጥል ማስታወቋ ይታወሳል።
በሌላ የሱዳን ዜና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በፖርት ሱዳን ተገኝተው ከጄነራል አልብሩሃን ጋር መምከራቸው ሰፊ መነጋገሪያ ነው። ይህ ምክክር ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጎዳና በቀጭን ገመድ የምትራመድ እንደምትመስል የዘገቡም አሉ፡፡
መንግስት ትህነግን ከግራና ከቀኝ ወጥሮ የመያዝና በትግራይ ከተነሳባቸው ተቃውሞ ጋር አዳምሮ ለማክሰም ከጀመረው እንቅስቃሴ ጋር ያያዙትም አሉ፡፡ በተለይም ትህነኝ ወክለው ከሱዳን ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ የነበሩት አቶ ጌታቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪቃ ቀንድ ኃላፊ ሆነው ወደ ሱዳን ማቅናታቸው ጥርጣሬውን የሚያጎላ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከሁለቱም የሱዳን ተፋላሚዎች ጋር መጣላት እንደማትፈልግ የሚገልጹ፣ የአቶ ሬድዋንና አቶ ጌታቸው የፖርት ሱዳን ጉዞ የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ እንዳለበት ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ሁለቱንም እንዴት እንደምታስታምም ይፋ የማያደርጉ ክፍሎች ምን አልባትም የተባበሩት አረብ ኢምሬጽ የነሳችውን ዕውቅና እንድትመልስላት የማግባባት ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ። በተጨማሪም በምክክሩ ወቅት ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው የትግራይ አርሚ ኃይል ተላልፎ እንዲሰጣት ጄነራል አልቡርሃን መጠየቋን ያነሳሉ።
የትግራይ ሚዲያ ሃውስ /ቲኤምኤች በቅርቡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሱድን ጉብኝት አስመልክቶ ስጋቱን ገልጿል። በሱዳን ከጄነራል አልቡርሃን ጋር ሆነው የሐመቲን ተዋጊዎች ሲዋጉ የነበሩት የትህነግ ታጣቂዎ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችል ጠቁሟል። ቲኤም ኤች እነ ዶክተር ከሚመሩት ትህነግ ጋርም ሆነ ከታጣቂዎቹ አመራሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላው ዜናውን በስጋት ቢያቀርበውም ጉዳዩ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ያምናሉ።
በቅርቡ ከሻዕቢያ ጋር አዲስ ቅንጅት የጀመረው የትህነግ አንድ ስንጣቂ ህገ መግስቱን በመጣስ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሤ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበለትና እንደሆነ ቢሰማም መንግስት በይፋ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ያለው ነገር የለም።