“የሚያሳዝነው” አሉ ሚኒስትሯ፣ “የሚያሳዝነው እንደ አገር እንኳን ልንጠራቸው የሚያስቸግር …” በማለት ነው መከላከያ ክንዱን ካነሳ የማያዳግም ምላሽ እንደሚሰጥ ያስጠነቀቁት። ዜጎቹ በፍርሃት ተሸብበው የሚኖሩበት አገር የሜመሩ ስለ ኢትዮጵያ አንስተው መናገራቸው እንደሚያስገርማቸው የተናገሩት የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር ወ/ሮ አይሻ ስም ሳያነሱ ነው ለኤርትራው መሪ ሃፍረት እንደሚሰማቸው የገለጹት።
በተደጋጋሚ ሲነገር እንደነበረው የመከላከያ ሰራዊት እጅግ ዘመናዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መደራጀቱን ሲገልጹ፣ ሪፎርሙ የዓለም አቀፍ የጦርነት ስልቶች መለወጣቸውን ኝዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን በማለከትና ተጨባጭ ማብራሪያ በማስከተል ነው።
ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትንም ዘመናዊ ትጥቅን በማሟላት የሀገርን ተጋላጭነት ማስቀረት የሚችል አስተማማኝ ኃይል ሆኖ መደራጀቱን ሲያስታውቁ፣ በኢትዮጵያ ላይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን ከሩቅ የሚያስቀርና የሚመክት የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የባሕር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻ እና የሳይበር ኃይል መገንባቱን በመግለጽ ነው።
እንግዲህ በዚህ ደረጃ የተደራጀውን ኃይል ነው “መከላከያ ሰራዊታችን የተዘጋጀው ቤታችን ላሉ የሌሎችን ምክር እየሰሙ እዚም እዛም ላሉ ለሰፈር ትናንሽ ቡድኖች አይደልም” ያሉት። እነዚህ እዛም እዚህም የሚሹለከለኩት ሳይሆን የአገር መከላከያ ዝግጅት በተሳሳተ ስሌት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ለሚዳፈሩ ሀገራት መሆኑን በግልጽ አስታውቀዋል። አክለውም እዛና እዚህ ለሚራወጡት ለእነዚህ ትናንሽ የሰፈር ቡድኖች ሚሊሻ በቂ መሆኑን አምልክተዋል።
በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት የኢፊድሪ ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ ጦርነትን እንደማትፈልግ፣ ከተነኮሷት ግን ምላሹ የከፋ እንደሆነ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የአገር መከላከያ ዋናውና ምክትል ኤታማዦር ሹሞችም በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህንኑ ማለታቸው አይዘነጋም። ዝግጅታቸውም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ለመንደር ዘራፊዎች እንዳልሆነ ደጋግመው ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
“ኤርትራን ሀገር ነው ብሎ ለመጥራት የማይቻል ህዝቡ በፍርሃት ተሸብቦ ሚኖርበትና ተሰዶ ያለቀበትን ሀገር መሪ ነኝ የሚለው (ኢሳያስ) በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር መድፈሩ የተለመደ የነሱ ባህሪ ነው” በማለት ምላሽ ሳይሆን መገረማቸውን ያስታወቁት ኢንጂነር አይሻ፣ አገላለጻቸው ሌተናል ዮሐንስ ገብረመስቀል በቅርቡ በኢቲቪና በአንድ አፍታ ላይ ” እኛ ነን ዝሁን ያደረኛቸው እንጂ እዚህ ግቡ የሚባሉ ኣይነት አይደሉም” ካሉት ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።
እንደ አገር የውድቀት፣ የጨለማ፣ የቆመ ሰዓት፣ ቴክኖሎጂ ብርቋ፣ ቀለም ብርቋ፣ ኢንተርኔት ብርቋ፣ ሚዲያ ብርቋ፣ ዳውን ሎድ የተደረጉ የቲክቶክ መረጃዎች በስልፍ የሚሸጡባት፣ ዜጎች በነጻነት መውጣትና መግባት የማይችሉባት፣ ምርጫና ካቢኔ የማታውቀው፣ ህግ አውጪና አስፈጻሚ የሌላት፣ በጀትና ዓመታዊ ዕቅዷ ይፋ የማይሆን፣ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ኢትዮጵያ የተጠጉ፣ መላ ዓለምን እድሜ ሳይለዩ በስደት ያጥለቀለቁ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር ሁሉ የተዋጋችና የደቀቀች አገር የሚመሩት ኢሳያስ አፉወርቂ ” የኢትዮጵያ ሕዝብ ተነስቷል” በማለት እሳቸው ያደራጁት የሰሜኖቹና የኩሾች ጦርነት ሊፈነዳ መቃረቡን በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም። የመከላከያ ሚኒስትሯም ዝርዝሩን አይናገሩ እንጂ እዚህ ማቅ ውስጥ የሚኖሩት ኢሳያስ፣ እንዲህ ያለ ሕዝብና አገር የሚያስተዳድሩ መሪ በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያን መዳፈራቸው እንዳስገርማቸው ከንግግራቸው ለመረዳት ተችሏል።
ሚኒስትሯ በመከላከያ ሠራዊት የተከናወኑ ተግባራትን፣ የተገኙ ስኬቶችንና ቀጣይ ተልዕኮዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሲሰጡ መገረማቸውን ጠቆም አድርገው አለፉ እንጂ ዋና የንግግራቸው ትኩረት ሌላ ነበር።
የአገር መከላከያ በማህበራዊ ገሹ እንዳለው ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ስኬታማ ሪፎርም መደረጉን አንስተው፤ ውትድርና ጀግኖች የሚመርጡት ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት ዋጋ የሚከፈልበት የተከበረ ሙያ መሆኑን ሚኒስሯ መናገራቸውን አመልክቷል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገርና ህዝብ የሚመካበት ፕሮፌሽናል የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱንም ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል።
የዓለም አቀፍ የጦርነት ስልቶች መለወጣቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትንም ዘመናዊ ትጥቅን በማሟላት የሀገርን ተጋላጭነት ማስቀረት የሚችል አስተማማኝ ኃይል ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ሠራዊቱ በህበረብሔራዊ አንድነት የተዋቀረና ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ የቆመ የመጨረሻው ጠንካራ ምሽግ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መልከ ብዙ ግዳጆችን በብቃት በመወጣት በአደረጃጀት፣ በትጥቅ፣ በአስተሳስብና ስልጠና ነጥሮ የወጣ ዘመናዊ ሠራዊት ሆኗልም ነው ያሉት።
ሠራዊቱ ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚሞክሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ማፅናቱንም ገልጸዋል።
በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሰላም ችግር የሚፈጥሩ የታጠቁ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድና በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እንዲሰጡ በማድረግ የዜጎችን ሰላም እያስጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጽንፈኞችና የሽብር ቡድኖችን የስጋት አቅም በማክሰም ስኬታማ የህግ ማስከበር ስራ መሰራቱንም ሚኒስትሯ ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሠራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር በሰዎች እና በሸቀጦች እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል በሚፈጥሩ ጥቂት የጥፋት ኃይሎች ላይ ቀጣይነት ያለው እርምጃ በመውሰድ ሰላማዊ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍለውን ሰራዊት በማህበራዊ ሚዲያ በሀሰት ስሙን የሚያጠፉ አካላት መኖራቸውን በማንሳት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ እንዳይሳካ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
በተመሳሳይ መረጃ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ ከፎከሩ በሁዋላ “ድሮም የኢትዮጵያን ሰራዊት አላሸነፋችሁም። ሚስጥሩን እናንተም እኛም እናውቀዋለን፣ ጦርነት አስፈላጊ አይደለም፣ እሳቸው ከመረጡት ግን ጀኛው ይ፤ለያል” የሚሉ ድምጾች እየተሰሙ ነው።
መሳሪያውን እንዲያወርድ የታዘዘውን የአገር መከላከያ በግፍ መረሸናቸውንና የወርቅ ጥርስ ሳይቀር እየነቀሉ የዘረፉትን የሚያሳውሱ የቆዩ ጽሁፎችን በማዟዟር፣ በሴራ የኢትዮጵያዊያን አለኝታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት “የደርግ ” በማለት እንዴት እንደበተኑት በማስታወስ ያ ዘመን ማክተሙን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። በተቃራኒው “ኢሳያስ የሚያስደምም ንግግር አደረጉ” በማለት አገራቸው ላይ ሲዛበቱ የተደመጡ፣ የኢሳያስን ዛቻ በማስተንተንና በማሞካሸት ፕሮፓጋንዳ ሲሰሩ የታዩ “ኢትዮጵያዊ ነን” ባዮችም እየታዩ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በዋና በአጀንዳነት ሳይዘው በሳምንታዊ መግለጫው ላይ ድንገት ተጠይቆ “ኢትይጵያ ኃላፊነት የሚሰማት አገር ናት” በማለት ምልልስ ውስጥ እንደማይገባ መጥቀሱ አይዘነጋም። ሚኒስትሩ የባህር በር ፍላጎትን አስመልክቶ ኣለም ሁሉ ያመነበትና የዲፕሎማሲ ድል እየተገኘበት ያለ ጉዳይ መሆኑን አመልክቶ በሰላማዊ መንገድ፣ በህጋዊ መንገድ፣ በፍትሃዊ መንገድ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ማስታወቁም የሚታውስ ነው።