በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ በዋለው የእስራኤልና ኢራን ግጭት ጥቃቱ ማምሻውንም በሁለቱም ሀገራት በኩል ተጠናክሯል። ኢራን የእስራኤል አየር ኃይል ጦር ሰፈሮችን በሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤሎች መደብደቧን አስታውቃለች።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያገለግሉ ናቸው ባላቸው በእነዚህ የአየር ኃይል ጦር ሰፈሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል። በመግለጫውም ድብደባው እስራኤል በኢራን ሉዓላዊነት በመድፈር በግዛቷ ውስጥ ለፈፀመችው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ ነው ብሏል።
በምሽቱ የሚሳኤል ድብደባ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ትጠቀምባቸዋለች ያላቸው በርካታ የአየር ኃይል ጦር ሰፈሮችን መደብደቡን መግለፁን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የጂ7 አገራት ኢራን ላይ ተመሳሳይ አቋም ያዙ
ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የቡድን ሰባት አባል ሃገራት “ኢራን በፍጹም የኑክሌያር ቦምብ ልትታጠቅ አይገባም – Iran can never have nuclear weapon” በሚል ሃሳብ ዙሪያ መስማማታቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይ አባል ሃገራቱ “በእስራኤል እና ኢራን መካከል ያለው ግጭት ሊረግብ ይገባል (Israel-Iran de-escalation) የሚለውን አንቀጽ ቢያሰፍሩም ዶናልድ ትራምፕ አሻፈረኝ ብለዋል።
አሜሪካን ጨምሮ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን የሚገኙበት የቡድን 7 አባል ሃገራት በአልበርታ ካናዳ ሲሳተፉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤል ኢራንን ግጭት ለመከታተል ስብሰባው ሳይቋጭ ወደ ሃገራቸው ተመስለዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራንን የአየር ክልል ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነዋል አሉ
የጂ7 ስብሰባን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማምሻውን ትሩዝ በተሰኘ ማህበራዊ ገፃቸው ባጋሩት ጽሁፍ፥ የኢራንን የአየር ክልል ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነዋል ብለዋል።
ትራምፕ አያይዘውም ኢራን ጥሩ የተባለ የአየር ክልል መቆጣጠሪያ እና ሌሎች ወታደራዊ መሳሪያዎች በብዛት አሏት፤ ነገር ግን አሜሪካ ከሰራቻቸው አይበልጡም ብለዋል።
ማንም ሀገር አሜሪካ ከምትሰራቸው የላቁ ወታደራዊ መሳሪያዎች ሊሰራ አይችልም፤ የአሜሪካ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች የትኛውም ሀገር ከሚሰራቸው የተሻሉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የጂ7 አባል አገራት በዶናልድ ትራምፕ አዘኑ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የበለጠ ለማጠናከር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የቡድን 7 (G7) መሪዎችን ማሳዘናቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ሰኔ 16 በተካሄደው የቡድን 7 መሪዎች የእራት ላይ ውይይት ወቅት የተደረገው ምክክር የፕሬዝዳንት ትራምፕን አቋም ሊያስቀይር አልቻለም። ፕሬዝዳንቱ በውይይቱ ላይ ደጋግመው እንደተናገሩት ማዕቀቡ “ለዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ነው” ማለታቸው አጋሮቻቸውን የበለጠ እንዳሳዘነ ተገልጿል።
ምንም እንኳን የትራምፕ አቋም ይህ ቢሆንም ከስብሰባው በኋላ በሚወጣው የመጨረሻ መግለጫ ላይ መሪዎቹ የጋራ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።
በዚህም መሰረት መግለጫው፦ አሜሪካ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ፣ ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታገኝ ያላትን ፍላጎት እውቅና እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም በሩሲያ ላይ የሚደረገው የማዕቀብ ጫና እንዲቀጥል ጥሪ እንደሚያቀርብ እንደሚጠበቅ አስቀድሞ ተገልጾ ነበር።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የእስራኤልን የደኅንነት መስሪያ ቤት ማጥቃቱን ገለጸ
ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ሁለቱም ሀገራት በርካታ ጉዳት ያስተናገዱ ሲሆን፣ ዛሬ ከማለዳው በጀመረው ግጭት ኢራን 30 ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏ ታውቋል።
ይህን ተከትሎም የኢራን ወታደራዊ ምንጮች፣ የእስራኤልን የደኅንነት ቢሮ ማጥቃታቸውን ገልጸዋል። ይህ ከተሰማ በኋላም እስራኤል የቴህራንን ከተሞች መደብደቧን እንደቀጠለች ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አዲስ የተሾሙትን የኢራን የጦርነት ጊዜ ዋና አዛዥ መግደሉን አስታወቀ
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የኢራን የጦርነት ጊዜ ዋና አዛዥ እና ከአገዛዙ ከፍተኛ የጦር አዛዦች አንዱ የሆኑትን አሊ ሻድማኒ መገደሉን አስታውቋል።
ዋና አዛዡ የተገደሉት በማዕከላዊ ቴህራን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ላይ በተደረገ የአየር ድብደባ መሆኑም ተዘግቧል። ጥቃቱ የተፈፀመው የእስራኤል ጦር በደረሰው መረጃ መሰረት፤ በኢራን ወታደራዊ ተዋረድ ውስጥ ካሉት ከፍተኛ ባለስልጣኖች አንዱ የሆኑትን የኢራን የጦርነት ጊዜ ዋና አዛዥን ዒላማ በማድረግ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
አሊ ሻድማኒ በዚህ ወር መጀመሪያ እስራኤል የጥቃት ኦፕሬሽን ውስጥ የተገደሉትን የቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አላም አሊ ራሺድን ተክተው ሚናውን መረከባቸው ይታወሳል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ግድያው በኢራን ወታደራዊ እዝ መዋቅር ላይ ወሳኝ ጉዳትን የሚያደርስ ሲሆን፤ የኢራንን የጦር ኃይሎች ከፍተኛ አመራሮችን እስራኤል በተደጋጋሚ ዒላማ አድርጋ እያጠቃች ትገኛለች።