የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ላይ ከግለሰቦች ጀምሮ እስከ ድርጅት ከፍተኛ ተቃውሞና ጥቆማ ሲቀርብባቸው ነበር። በተለይም ጠብ መንጃ ካነሱና፣ የጠብ መንጃ ትግሉን በሰላማዊ ትግል ስም ከሚያራምዱ ኃይሎች ጋር ልዩ አደረጃጀት በመፍጠር ክልሉን አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ የሚከሷቸው ጥቂት አልነበሩም። መሳሪያ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይም ስማቸው ይነሳ ነበር።
ከሌብነት ጋር በተያያዘ፣ በኮንትሮባንዳና በህገወጥ የመሳሪያ ዘውውርና ተመሳሳይ ወንጀሎች መረጃ ተሰብስቦ የቅርብ ክትትል ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል።
የሲዳማ ብሄራዊ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የአቶ አለማየሁ ጥሞቴዎስን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን ያስታወቀው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው። በበርክታ ወንጀሎች ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የተጠረጥሩበት ወነጀሎች በክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቶ ማሩ አማካይነት በዝርዝር ከቀረበ በሁዋላ ነው ምክር ቤቱ ውሳኔውን በሙሉ ድምጽ ያሳለፈው።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር ምርጫ 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ሰኔ 05/2017 ሲካሄድ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስን አስመልክቶ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጥያቄ ሲቀርብ የቀርበባቸው ክስ ተዘርዝሯል።
ላለፉት ዓምስት ዓመታት የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ጢሞቴዎስ ሃጢያታቸው ሲነበብ ከአንቱነት ወደ “አንተ” የተቀየሩት ወዲያው ነው።
በዚሁ አግባብ “እሱ” እየተባለ በቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ኃላፊነት በነበሩበት ጊዜ ስልጣናቸውም ያለአግባብ በመጠቀም ግለሰቦችን በግፍ አስረዋል። አሰቃይተዋል። እስረኞችን ለማስለቀቅ ከፍተኛ እጅ መንሻ ተቀብለዋል። ህገ ወጥ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ፈቃድ ሰጥተዋል። ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ግዥና ዝውውር እንዲካሄድ ፈቅደዋል። የግል ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው በክልሉ ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ አድርገዋል የሚሉና ተጨማሪ ማስረጃዎች መሰበሰቡ በዝርዝር ቀርቦባቸዋል።
ከሁሉም በላይ ሁሉንም ያነጋገረው በክልሉ መንግስት ላይ መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ ጥረት ማድረጋቸው የቀረበባቸው ዋንኛ ህገወጥ ተግባር ነው። በጠቅሉ ይቀረበባቸው ይህ የመንግስት ግልበጣ ዕቅድ ከማን ጋር፣ እንዴት ሲቀነባበር እንደነበር በፍርድ ቤት ዐቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርት የሚቀርብ እንደሆነ ይታወቃል። ኃላፊው እነ ጃዋር ሲያደራጁትና ሲደግፉት ከነበረው ኤጄቶ ከሚባለው ቡድን ጋር ትስስር እንዳላቸውና ሰሞኑን ድርጅቱ የፈረሰውን አድረጃጀቱን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያዎች አልፎ አልፎ የሚሰራጩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ መወጠር በሚለው የሻዕቢያ የውክልና ዕቅድ መነሻ በሶማሌ ክልልና በደቡብ ክልል ሲዳማ፣ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ አካባቢ ረብሻ ለማስጀመር ውርውር ከሚታየው ግር ግር ጋር አቶ ጢሞቴዎስ ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው ለጊዜው የተባለ ነገር የለም።
በተለያዩ ህገ ወጥ መንገዶች በርካታ ገንዘብ መሰብሰባቸው መረጃ የቀረበባቸው አቶ ጢሞቴዎስ በምክር ቤት አባላት በኩል የግለሰቡ ያለመከሰስ መብቱ እንዲነሳ ከመቅረቡ በፊት በግለሰቡ ወንጀል ድርጊቶች ጥርጣሬ ዙሪያ ከተለያዩ አካላት መረጃዎች ተሰብስበው ተገቢው የማጣራት ስራ መሰራቱን ተገልጿል።
ምከር ቤቱም አቶ አለማየሁ ጥሞቴዎስ በቀረበባቸው ያለመከሰስ መብት ላይ መወያየቱን ያስታወቀው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት፣ በስተመጨረሻ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳው በሙሉ ድምፅ ነው። በዚሁ አግባብ ቀጣዩ ጉዳይ የፍርድ ቤት ይሆናል።
የሲዳማ ክልል በተደጋጋሚ በሌብነት፣ መልካም አስተዳድር፣ አይን ያወጣ ነው በሚባል ኮንትሮባንድ፣ የነዳጅ ስርቆትና ማጭበርበር፣ ሙስና በስፋት ስሙ የሚነሳ ክልል ነው። ፕሬዚዳንቱም በዚሁ ዙሪያ ስማቸው ይነሳል።