መግቢያ
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ስር ነቀል የሚባል ለውጥ ለማምጣት ያለመ ሕግ ነው። ይህ አዋጅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ዘመናዊ የካፒታል ገበያ እንዲቋቋምና እንዲዳብር የሚያስችሉ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ዋና ዋና ዓላማዎቹም የካፒታል ፍሰትን ማሳለጥ፣ የቁጠባና የኢንቨስትመንት ባህልን ማሳደግ፣ እንዲሁም ቀልጣፋና ፍትሀዊ የገበያ ሥርዓት መፍጠር ናቸው። በዚህ አጭር ጽሁፍ አዋጁ የያዛቸው ቁልፍ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ።
የካፒታል ገበያ ምንነት
በአዋጁ አንቀጽ 2(5) እንደሰፈረው የካፒታል ገበያ ማለት እንደ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ተዛማጅ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ወይም እነዚህን የመሰሉ የተለያዩ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይት የሚደረግበት ገበያ ነው።
የካፒታል ገበያ ታሪካዊ ዳራ በኢትዮጵያ
የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በ1889 ዓ.ም የኢትዮ ጂቡቲን የምድር ባቡር ለመዘርጋት የ40 ሚሊዮን ፍራንክ አክሲዮን በፈረንሳይ አገር መሸጡን በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቧል። በአጼ ኃይለ-ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማቋቋም ሙከራዎች አድርጋ ነበር፤ በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቄራዎች /Ethiopian Abattoirs/ የተባለው ድርጅት የመጀመሪያውን አክሲዮን ለአደባባይ ምዝገባ አውጥቶ ነበር፤ይህ በሀገሪቱ የፋይናንስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።በ1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ የአክሲዮን ንግድ ማህበር /Addis Ababa Share Dealing Group/ የተቋቋመ ሲሆን ይህ ቡድን ብሔራዊ ባንክን እና ሌሎች ግለሰቦችን በማቀፍ የዋስትና ገበያን ለመቆጣጠር ዓላማ አድርጎ ነበር። ምንም እንኳን እነዚህ ጥረቶች ቢኖሩም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች እና የቁጥጥር አካላት ባለመኖራቸው የተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ሊኖር አልቻለም። ግብይቶች የሚካሄዱት በንግድ ባንክ በኩል በከፊል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ነበር።
አዋጁ የያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል ፡-
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (Ethiopian Capital Market Authority) መቋቋም አዋጁ በአንቀጽ 3(1) ስር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያውን የሚቆጣጠር፣ የሚመራና የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ህጋዊ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግስት ተቋም ሆኖ እንደተቋቋመ ይደነግጋል።
የባለስልጣኑ ዓላማዎች በአዋጁ አንቀጽ 5 ስር የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡-
- ኢንቨስተሮችን መጠበቅ ወይም ከለላ መስጠት፣
- ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የማውጣትና የግብት ስርዓት ፍትሀዊ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽነት በሰፈነበት ሁኔታ የሚካሄድበትን የካፒታል ገበያ ስነ ምህዳር እንዲኖር ማድረግ፣
- መዋቅራዊ የአደጋ ስጋቶችን በመቀነስ የካፒታል ገበያው ተአማኒ እንዲሆን ማድረግ፣
- የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን የሚያበረታታ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የካፒታል ገበያን ማስፋፋት ናቸው።
የባለስልጣኑ ስልጣንና ተግባራት ፡- ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለማሳካት የሚያስችሉ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 6 ስር ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፤ እነዚህም የገበያ ተዋናዮችን መመዝገብ፣ ከምዝገባ መሰረዝና ፈቃድ መስጠት በአንቀጽ 6(1)፣ 6(18))፣ የገበያውን ህግና ደንብ ማውጣትና ማስከበር በአንቀጽ 6(16)፣ የኢንቨስተሮችን ጥቅም ማስጠበቅ በአንቀጽ 6(27))፣ እንዲሁም የገበያውን ግልጽነትና ቀልጣፋነት ማረጋገጥ በአንቀጽ 6(17))፣ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የሚያከናውነው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይት ወይም የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክ የግብይት መድረኮች የሚካሄድበትን አግባብ መቆጣጠር በአንቀጽ 6(15)) ስር ሰፍረው የምናገኛቸው ናቸው።
የካፒታል ገበያ ተዋናዮችና ፈቃድ አሰጣጥ
አዋጁ በካፒታል ገበያው ውስጥ የሚሳተፉ የተለያዩ ተዋናዮችን ይለያል፤ በአዋጁ አንቀጽ 2(6) እንደተደነገገው የካፒታል ገበያ ተዋናዮች ማለት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ ተገቢነት ያላቸውን ውሎች ያደረጉ ብቁ የሆኑ ተጓዳኝ ወገኖች፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች አስቀማጭና ክፍያ አጣሪና ፈጻሚ ኩባንያዎችን እንደሚያካትት ይደነግጋል። እነዚህ ተዋናዮች በገበያው ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከባለስልጣኑ ፈቃድ የማግኘት ግዴታ አለባቸው (አንቀጽ 6(1))። ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ ዝርዝር መስፈርቶች በአዋጁ አንቀጽ 39 ስር የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አስቀማጭና ክፍያ አጣሪና ፈጻሚ ኩባንያ ፈቃድ አሰጣጥ የሚገልጽ ሲሆን በአንቀጽ 55 እስከ 58 ደግሞ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የሚሰጥበትን መስፈርት ይደነግጋል። ለሁለቱም አካላት የጋራ የሆኑ መስፈርቶችን ስንመለከት ዝቅተኛ የካፒታል መጠን፣ የተገቢነት መስፈርት፣ የብቃት ማረጋገጫ፣ መልካም ስም ወዘተ… ይገኙበታል፤
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ/Security/ ምዝገባና ግብይት
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ምዝገባ እና ግብይትን ከማየታችን በፊት ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ምንድን ነው የሚለዉን ማየቱ ስለጽንሰ ሃሳቡ ለመረዳት ያግዘናል። በአዋጁ የትርጉም ክፍል በአንቀጽ 2(62) በስፋት እንደቀረበው ሰነደ መዋዕለ ንዋይ /security/ ማለት በማንኛውም ህጋዊ መልክ ያለ በገንዘባዊ ግብይት የድርሻ ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ እና በባለስልጣኑ ፈቃድ የሚተላለፍ ሆኖ የሚከተሉትን ማለትም፡-
- በኩባንያ ካፒታል ውስጥ የወጡ ወይም የሚወጡ አክሲዮኖችን፣
- በኩባንያ የወጡ ወይም የሚወጡ ባለዕዳነትን የሚፈጥሩ ወይም የሚያረጋግጡ ማናቸውም ሰነዶችን፣
- ብድሮች፣ ቦንዶችና ሌሎች ወደ ኩባንያ ካፒታልነት ሊቀየሩ የሚችሉ ሰነዶችን፣
- ሁሉም በመንግስት እና በመንግስት የልማት ድርጅቶች የወጡና ለግብይት የሚውሉ የህዝብ የብድር ሰነደ መዋዕለ ንዋዮችን እንደሚያካትት ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ቼክ፣ የተስፋ ሰነድ፣ የሀዋላ ወረቀት፣ የንግድ ወረቀቶች፣ ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ጥሬ ገንዘብ ማስተላለፍ እና በባንኮች መካከል እርስ በርስ ብቻ የሚተላለፉ ሰነዶችን፣ የመድን ፖሊሲዎችን እና ለተጠቃሚዎች ከጡረታ ክፍያዎች የሚመነጩ መብቶችን እንደማያካትት በዚሁ ድንጋጌ ስር ተመላክቷል። ከዚህ በመቀጠል የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ምዝገባ እና ግብይት ሂደትን እንመለከታለን። ይኸዉም፡-
* ለህዝብ የሚሸጥ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ለሽያጭ ወይም ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በባለስልጣኑ መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 75(1) ስር ተደንግጓል።
* የሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጭ ማንኛውንም ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ለህዝብ ለሽያጭ ከማቅረቡ በፊት ትክክለኛ፣ ግልጽ እና የተሟላ የደንበኛ ሳቢ መግለጫውን በባለስልጣኑ ማስፀደቅ እንዳለበት በአዋጅ አንቀጽ 76(1) እና (2) ስር ተደንግጎ እናገኘዋለን ።
* የገበያውን ግልጽነት ለማረጋገጥ ኩባንያዎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለባለሀብቶችና ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ ይጣልባቸዋል።
የኢንቨስተሮች ጥበቃ
* አዋጁ የኢንቨስተሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ይህም ከታች በተጠቀሰው መልኩ ቅጣት የሚያስከትሉ ድርጊቶችን በመደንገግ ይገለፃል።
* የገበያ ማጭበርበርን /Fraudulent transaction/ በአንቀጽ 98፣ የውስጥ አዋቂ ንግድን (Insider Trading) በአንቀጽ 95 እና ሌሎች ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ተካተዋል። - ቅጣትና አስተዳደራዊ እርምጃዎች
- አዋጁንና በአዋጁ መሠረት የሚወጡ ደንቦችን የሚተላለፉ አካላት ላይ የሚጣሉ የእስራት እና የገንዘብ ቅጣቶች በአዋጁ አንቀጽ 106 ስር እና ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች በአዋጁ አንቀጽ 107 ስር ተደንግገው እናገኛቸዋለን። ይህም የሕግ ተገዥነትን ለማረጋገጥና የገበያውን ሥርዓት ለማስጠበቅ ያግዛል። ከቅጣቶች መካከል ለምሳሌ ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳያገኝ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ያቋቋመ ከ100,000.00 እስከ 150,000.00 የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ5 ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በአንቀጽ 106/2/ ስር ተደንግጎ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ማንኛውም ሰው ፈቃድ በሌለው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ የሌለው መሆኑን እያወቀ የተገበያየ እንደሆነ ከላይ በንዑስ አንቀጽ 2 የተደነገገው ቅጣት እንደሚወሰንበት በአዋጁ አንቀጽ 106/3/ ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን። ከአስተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል በአንቀጽ 107 ከተመለከተው ጠቅላላ እርምጃ ባሻገር በአንቀጽ 33 ስር የተመላከተው በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያና የግብይት መድረኮች ላይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች የሚዘረዝረው ሲሆን እነዚህም፡-
- ዋጋን ማመላከት እንዳይችል የሚያደርግ ከፍተኛ የግብይት መስተጓጎል ሲከሰት
- ተጨባጭ ወይም ተገማች የሆነ ገበያን የማዛባት ተግባር ሲፈጸም
- ለህዝብ ጥቅም ሲባል ወይም ኢንቨስተሮችን ለመጠበቅ ጠቃሚ ወይም አስፈላጊ ነው ብሎ ባለስልጣኑ ሲያምን ባለስልጣኑ በጽሁፍ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ለተወሰነ ጊዜ ገበያው እንዲዘጋ ሊወስን ይችላል፣ ይህም በአንቀጽ 33/1/ ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን።
- በተጨማሪም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ስር የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ባለስልጣኑ የገበያ ፈቃዱን ለተወሰነ ጊዜ ወይም አንድ ተግባር እስከሚፈጸም ድረስ ሊያግደው እንደሚችል ተመላክቷል። ይኸውም፡-
- ከተሰጠው የስራ ወሰን ወይም ከተፈቀደለት የስራ ዘርፍ ውጪ የሆነ ተግባር ከፈጸመ
- ከተሰጠው ፈቃድ ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ቅድመ ሁኔታዎች ከጣሰ ወይም ካላከበረ
- ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ ከሰጠ የሚሉት ናቸው።
የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት መቋቋም
አዋጁ በአንቀጽ 64 ስር የካፒታል ገበያ አስተዳዳራዊ ፍርድ ቤት መቋቋሙን ይደነግጋል። በአዋጁ አንቀጽ 65 ስር እንደተመላከተው አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ በባለስልጣኑ ወይም የባለስልጣኑን ስልጣንና ተግባር በሚያስፈጽም ሰው በተላለፈ ውሳኔ ላይ የቀረበን ይግባኝ የመስማትና የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል። አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ይግባኝ ከተመለከተ በኋላ፡-
- የመጀመሪያውን ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ እንዳለ ሊያፀናው፣ ሊያሻሽለው ወይም ሊሽረው፣
- ትክክለኛ ነው ብሎ በወሰነው አቅጣጫ ጉዳዩን እንደገና እንዲያየው ወደ ባለስልጣኑ ሊመልሰዉ ወይም
- ትክክለኛ ነው ብሎ ያመነውን ማናቸውም ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 73(5) ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን።
ሌላው በአዋጁ የተካተተው ነጥብ በአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተከራካሪ አካል ውሳኔዉን ባወቀ በ30 /ሰላሳ/ ቀናት ውስጥ በህግ ጉዳይ ላይ ብቻ ይግባኙን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 74 ስር ተደንግጎ እናገኘዋለን።
ማጠቃለያ
የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የካፒታል ገበያ እንዲፈጠር፣ እንዲያድግና እንዲጠናከር የሚያስችል ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ በማቅረብ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። አዋጁ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመሳብ፣ የንግድ ድርጅቶች የፋይናንስ አማራጮችን እንዲያገኙ ለማድረግና የሀብት ክፍፍልን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን እንደሚያስችል ታምኖበት በስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። በመሆኑም ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለአዋጁ መከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል።
የፍትሕ ሚኒስቴርን