እነ አቶ ልደቱ አያሌው “ጦርነት ይቁም” በሚል ባዘጋጁት የአየር ላይ ትዕይንት ዋና ተሳታፊ የሆነውና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ /ትህነግ እያለ የሚጠራው ቡድን በሸራሮ ደደቢት፣ በደርባ አባይ፣ በአዲ ገብሩና በዛና በኩል ሰራዊት ማስጠጋቱን በመጥቀስ የጠለምት አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አቀረበ።
ከዝግጅት ባለፈም በጠለምት በርሃ አርማ ደጋ ደልዲማና መሰል ቦታዎች የታጠቁ ሀይሎች እንዲገቡና በህዝባችን ላይ እገታ፣ ስርቆት፣ ግድያንና ድብደባ እንዲፈጽሙበት ስምሪት የተሰጠ መሆኑን፣ ይህንንም ከተባዳይ ወገኖች መረጃ ማሰባሰቡን የገለጸው ኮሚቴው አድራጎቱ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበት ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል።
መግለጫው ባያነሳውም ለአማራ ሕዝብ ህልውና እንደሚታገሉ የሚገልጹ የፋኖ አደረጃጀቶች አቋም እያነጋገረ ነው። ትህነግ ጠለምትን ብቻ ሳይሆን ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራን የማስመለስ ዕቅድ እንዳለው እየታወቀ በአማራ ሕዝብ ስም ብረት ያነሱ በምን ውል አብረው ለትህነግ ጋር ለመስራት እንደተስማሙ ገሃድ የተነገረ ነገር የለም። ትህነግም ለአማራ መብት እንደሚታገሉ ለሚናገሩት አቋሙን ስለመቀየሩ በግልጽ ያስታወቀው ነገር የለም። ይህን አስመልክቶ ጥብቅ ጥያቄ የሚቀርበበትን ህብረት አስመልክቶ በተለይ የጎጃም ፋኖ በገሃድ አቋሙን አለማስታወቁ ቅሬታና መከፋፈልን እያስከተለ መሆኑ ይታወቃል። ገለልተኞች በህዝበ ውሳኔ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ ደጋግመው ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ይታወሳል። ሙሉ መግለጫውን ከስር ያንብቡ።
ጦረኛው እና ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ለዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት አጥብቀን እንቃወማለን፤ ለዘላቂ ሰላም እንታገላለን !!
(ከጠለምት አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዩች ላይ የተሰጠ መግለጫ)
የጠለምት አማራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት የሚሻገር የመከራ ጊዜ፣ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ተጭኖበት መቆየቱ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡
የ1987ቱ ሕገ-መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በኃይልና በጭፍለቃ ተይዘን ከእናት ግዛታችን ስሜን በጌምድር አማራ ተነጥለን ለመኖር ተገደን ነበር፡፡ በዚያ የሕወሓት አገዛዝ ዘመን፣ አማራዊ ማንነታችን የጥቃት ምንጭ ሆኖብን ዛሬ ይቅር ብንል እንኳ መቼውንም ልንዘነጋው የማይቻል በደል በትሕነግ ተፈጽሞብናል፡፡
ይህም ሆኖ ከበርካታ የሕዝብ ትግልና ውጣ ውረድ በኋላ እዚህኛው የትግል ምዕራፍ ላይ ብንደርሰም አሁንም ግልጽና ቀጥተኛውን ጥያቄችንን ወደኋላ የሚመልስ ውስብስብ መሰናክል እያጋጠመን በሰላማዊ መንገድ መታገላችንን ቀጥለናል፡፡
የጠለምት አማራ ሕዝብ፣ በጎረቤታችን ትግራይ ያለውን ጦረኛ እንቅስቃሴ በአንክሮ በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ አብሮነት፣ እንደተወሳኝ ጎረቤት በትግራይ ያለው ሁኔታ ያሳስበናል፡፡ በተለይም ሁኔታው እንደጠለምት የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝባችንን የዘመናት ሕዝባዊ የትግል ጥያቄ መሠረታዊ ጥቅሞቹን የሚነካ ከመሆን አልፎ ህልውናውን ለአደጋ የሚጥል ነው፡፡
በተለይም ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ለዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያደርገው ዝግጅት እንደጠለምት አማራ ብቻ ሳይሆን አጠቃለይ እንደ አማራ ሕዝብና እንደ ኢትዮጵያ ሁኔታው እጅግ ያሳስበናል፤ የሕገወጥ ቡድኑን አሁናዊ የጦረኝነት እንቅስቃሴዎችም አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሕግና አዋጅ ጠቅሶ ከግንቦት 6/2017 ጀምሮ ከፓርቲነት የሰረዘው ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን የፖለቲካና የታጣቂ ስምሪቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በክትትላችን በሸራሮ ደደቢት፣ በደርባ አባይ፣ በአዲ ገብሩና በዛና በኩል ሰራዊት አስጠግቶ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡
በተጨማሪም በጠለምት በርሃ አርማ ደጋ ደልዲማና መሰል ቦታዎች የታጠቁ ሀይሎች እንዲገቡና በህዝባችን ላይ እገታ፣ ስርቆት፣ ግድያንና ድብደባ እንዲፈጽሙበት ስምሪት የተሰጠ መሆኑን፣ ይህንንም ከተባዳይ ወገኖቻችን በሳባሰብነው መረጃ አረጋግጠናል፡፡
በተለይም በምዝክር፣ አምበል (ጻዕዳ ቀርኒ)፣ ማይተክሊት፣ ውህደትና እምባማድሬ በተሰኑ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ አከባቢዎች በሙሉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከሕወሓት የሚረዱ የቡድኑ ህገወጥ ታጣቂዎች የአካባቢው ስጋት ሆነዋል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል እንደሚፈጸምም የክትትል መረጃ ያሳያሉ፡፡ በእነዚህ የጠለምት አማራ ግዛቶች ላይ ይኖር የነበረው ነባሩ ባለርስት አማራ ላይ እየደረሰ ባለው ዳግም የተነሳ እየተፈናቀለብን ይገኛል፡፡ እኛ እንደ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ተፈናቃይ ተቀብለን ባለበት ሁኔታ ባለርስቱ አማራ ግን ዳግም ከቀየው እየተፈናቀለ ይገኛል።
በአጠቃላይ ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን በወታደራዊ፣ መረጃና የፖለቲካ ኃይሉ የየራሱን ስምሪት ወስዶ እየሰራ በመሆኑ፣ ይህም ዳግም ወደ ደም አፋሳሻ ጦርነት የመግባት፣ የጥፋት ስምሪት የቅድመ ዝግጅት አካል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
ስለሆነም ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ለዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት አጥብቀን እየተቃወምን፤ ለዘላቂ ሰላም እንደሚታገል ሰላማዊ የማንነት ታጋይ እንደጠለምት አማራ ሕዝብ ያለንበት ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የሚከተለውን ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡-
- ሕወሓት ፕሪቶሪያ ላይ ከፈረመው ባለ 15 አንቀፅ ሰነድ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታና ተዋጊዎቹ በሙሉ ወደ ተሃድሶ (ማሰልጠኛ) ካምፕ እንደሚገቡ ስምምነቱ አስገዳጅ ቢሆንም ይህ በአግባቡ አልተፈፀመም፡፡ አሁንም ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ሰራዊት እያስጠጋ፤ ተከዜን አሻግሮ ባስገባቸው ሕገወጥ ታጣቂዎቹ ሕዝብ ላይ ማንነት ተኮር በደል እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ይህም የስምምነቱን መሠረታዊ ዓላማ ግጭትን በዘላቂነት ማቆም የሚለውን ፍሬ ነገር በተጨባጭ የሚቃረን ጦረኝነት ነው፡፡ በመሆኑም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት፤ ሰራዊት መበተንና ከማኀበረሰቡ ጋር መልሶ የማዋሃድ (DDR) ዕቅድ ያለአንዳች መጓተት እንዲፈጸም እንጠይቃለን፡፡
- የሕወሓት ወታደራዊ ስልጠናዎች መቀጠል፣ የታጣቂ ቡድኑ እንቅስቃሴ ለሌላ ዙር የጦር ወረራ የሚያደርገው ዝግጁነት ነው፡፡ ድርጅቱን ከዚህ መሰል የዳግም ጥፋት መንገድ የማስቆም ስራ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል እንቅስቃሴዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሁኔታዎች ሊያመጡ በሚችሉት አደጋ ልክ መፍትሔ ካልተሰጠ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ የከፋ አደጋ ያመጣል የሚል ስጋት አለን፡፡ ቡድኑ ዳግም ለደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያደረገው ዝግጅት ለኢትዮጵያ ሐገረ-መንግሥት አደጋ፣ ለአካባቢውም ጠንቅ በመሆኑ ጦረኛ እንቅስቃሴዎቹን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
- የጠለምት አማራ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን በሚጨፈልቅ መልኩ ወደ ዳግም የባርነት አገዛዝ ለመውሰድ ሁኔታዎችን የማወሳሰብ፣ ሴራ፣ ሸፍጦች አሁንም ቀጥለዋል፡፡ በተለይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) ስም የሚፈጸሙ ተግባራት አሳስበውናል፡፡ በአካባቢያችን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ መያዶች በወረቀት ከሰፈረው ከምስረታ ዓላማቸው በሚቃረን መልኩ የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ ሆነው መታየት ላይ ናቸው፡፡ ይህም የዘመናት የማንነት ትግላችን እያወሳሰበው በመሆኑ የፌደራል መንግሥት የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በሚመለከተው አካል እንዲፈጸምና እንዲታረሙ እንጠይቃለን፡፡ አካባቢው ሰላም እንዳይሆን እያባባሱ የሚገኙ መያዶችን ማሳያ ከተፈለገ በዝርዝር እንደምናቀርብ እናሳውቃለን!
- የፌደራልና የክልል መንግስት ከዚህ በፊት በተስማሙት መሠረት ለዘላቂ ሰላምና ልማት ሲባል በትግራይና በአማራ ክልል ‹‹አወዛጋቢ›› ብሎ ከጠራቸው አንዱ የጠለምት አማራ ሕዝብ የሚኖርበት ሦስት ወረዳዎችን ነው፡፡ ችግሩ በዘላቂነት መፈታት አለበት በተባለበት መንገድ እስከሚፈታ ድረስ፣ በሦስቱም ወረዳ የሚገኘው ሕዝብ ጊዜዊ ሕዝባዊ አስተዳደር በማዋቀር፣ የአካባቢው የመልማትና የፍትህ ጥያቄ እንዲቀላጠፍ መንግስትም አምኖ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ የጊዜዊ ሕዝባዊ አስተዳደር ምስረታው እስካሁን ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ በእኛ በእኩል በጠለምት ሦስቱም ወረዳዎች ውስጥ፡- እውነተኛ ተፈናቃይ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች በቁጥር ድርሻቸው ልክ የሚሳተፉበት ሕዝባዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ከሕዝባችን የማንነትና ወሰን ጥያቄ ጎን ለጎን የመልማት ጥያቄዎቹ፣ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ሊያገኘው የሚገባ የበጀትና የልማት ማካካሻዎች እንዲሰጡት በድጋሚ እንጠይቃለን፡፡
- በፕሪቶርያ ስምምነት መሠረት ተፈናቃይ ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ይታወቃል በምላሹ ግን ትምህርት ባለመከፈቱ የጠለምት አማራ ህጻናት ትምህርት ፍለጋ ከቀያቸው ተፈናቅለውብናል። የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ መግለጫ፣ አንቀጽ 26 ማንኛውም ሰው የመማር መብት አለው (The Right to Access to Education) በሚለው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌና ሕገ-መንግሥታዊ መብት የመማር ዕድሉ ለልጆቻችን ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ በተመሳሳይ የመልማት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ በጠቅላላ የመሠረተ ልማት መብቶቻችን እንደ ማንኛውም የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ሊፈቀድልን የሚገባ በመሆኑ በቀጣይ ለ2018 ዓ.ም በጀት አመት እንዲያዝልን ከወዲሁ በጥብቅ እናሳስባለን።
በሕወሓት በኩል ጠለምትን በተመለከተ ይቀርቡ የነበሩ የጊዜዊ ሕዝባዊ አስተዳደር ምስረታው የ‹‹ይራዘምልን ጥያቄ›› ዓላማው ሂደቱን የማወሳሰብ ሴራ ወደ ኃይል ለማምራት የሚደረግ ጊዜ የመግዛት ድብቅ ፍላጎት ስለመሆኑ፣ አሁናዊ ግልጽ የጦርነት ዝግጅታቸው አስረጅ ምሳሌ ነው፡፡
በመሆኑም አማራነታችን የህልውና አደጋ ላይ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡
በመጨረሻም፣ የጠለምት አማራ ሕዝብ ለዘመናት ባሳለፈው የማንነት ትግል ነጻነት በነጻ እንደማይገኝ ከተግባር የተማረው እውነታ ነው፡፡ ጦረኛውና ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን የተገንጣይነት ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጨመረበት በዚህ ጊዜ የትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ተከዜን ማዕከሉ ማድረግ የፖለቲካ አልፋና ኦሜጋው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የጠለምት አልፎም ወልቃይት-ጠገዴን አማራ ዳግም በመውረር ሊያጠፋን ይፈልጋል፡፡ መቼውንም ቢሆን ሕዝባችን ይህ እንዲሆን አይፈቅድም፡፡
ትግላችን የማንነትና የወሰን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ከፍ ባለ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ አንድነትን መጠበቅ በመሆኑ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት አደጋ የሆነውን ጦረኛውና ሕገወጡን ሕወሓት የጦርነት ዝግጅት ለመቃወም፤ ለዘላቂ ሰላምና የአገር አንድነት ከጎናችን በእንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የጠለምት አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ
ግንቦት 26/2017 ዓ.ም ማይጠምሪ -ጎንደር- ኢትዮጵያ